ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ ለቫቲካን ሬዲዮ 90 ኛ ዓመት የምስረታ በዓል መልካም ምኞታቸውን ገለጹ።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለቫቲካን ሬዲዮ ሰራተኞች መልእክት ማስተላለፋቸው የተገለጸ ሲሆን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ይህንንን መልእክት ያስተላለፉት የቫቲካን ሬዲዮ የተመሰረተበትን 90ኛ አመት የካቲት 05/2013 ዓ.ም ባከበረበት ወቅት እንደ ነበረ ተገልጿል።
የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን
“ውድ ወንድሞች እና እህቶች ፣ መልካም የምሥረታ በዓል እንዲሆንላችሁ እመኛለሁ” በማለት በቪዲዮ ያስተላለፉትን መልእክት የጀመሩት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እነዚህን የሰላምታ ቃላት በመጠቀም ለቫቲካን ሬዲዮ ሰራተኞች በሙሉ ላለፉት ዘጠና አመታት ያህል በሬዲዮ የሚሰጠው አገልግሎት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ላበረኩቱት ሰዎች ሁሉ ቅዱስነታቸው ምስጋና አቅርበዋል።
ከተለያዩ የአለም ክፍሎች የተውጣጡ ኢትዮጲያን እና ኤርትራን ጨምሮ በስልሳ ዘጠኝ አገራት ቋንቋ የሚሰራጩ ዝግጅቶችን የቫቲካን ሬዲዮ ለዓለም ሕዝብ ተደራሽ እያደረገ እንደ ሚገኝ ያስታወሱት ቅዱስነታቸው በቫቲካን ሬዲዮ ውስጥ ለሚሰሩ ሰራተኞች እያከናወኑት ለሚገኘው ሥራ እና በፍቅር ለሚፈጽሙት ተግባር ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
“የታሪካችንን መታሰቢያ ማቆየታችን እና ያለፉ ጊዜያትን በመናፍቅ መኖር ሳይሆን ለወደፊቱ እንድንገነባ ለተጠራነው ዓለማ መትጋት እጅግ በጣም አስፈላጊ” መሆኑን ቅዱስነታቸው በቪዲዮ ባስተላለፉት መልእክት አክለው ገልጸዋል።
እውነትን መረዳትና ማሰራጨት
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ የሬዲዮን ሰፊ ተደራሽነት በማመስገን መልእክታቸውን የቀጠሉ ሲሆን “ሬዲዮ መልካም የሆነ ባህሪ አለው ፤ ቃሉን ወደ ሩቅ ቦታዎች ድረስ የማስተላለፍ ችሎታ አለው” ያሉት ቅዱስነታቸው ዛሬ ለቴክኖሎጆ ምስጋና ይገባውና መልእክቶች በድምጽ ብቻ ሳይሆን በምስሎች እና በጽሑፍ ቃል ጭምር መተላለፍ የሚችሉበት ወቅት ላይ ደርሰናል ብለዋል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የቫቲካን ሬዲዮ ሰራተኞችን እውነትን ለማሰራጨት እንዲተጉ አበረታቷቸዋል።
መልእክታችንን ለዓለም ለማስተላለፍ ይቻል ዘንድ በድፍረት እና በፈጠራ ችሎታ በታገዘ መልኩ ወደፊት ለመጓዝ መጣር እንደ ሚገባ፣ እናም የነገሮችን እውነት እንድናይ የሚረዳን የግንኙነት ዓይነት እንዲገነቡ” ለቫቲካን ሬዲዮ ሰራተኞች ቅዱስነታቸው ጥሪ አቅርበዋል።
ወደ ሩቅ ቦታዎች መልእክቶችን ማስተላለፍ
የቫቲካን ሬዲዮ እ.አ.አ የካቲት 12/1931 ዓ.ም በወቅቱ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በነበሩት ፒየስ 11ኛ እንደ ተመሰረተ ይታወሳል። በወቅቱ የነበሩት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮ 11ኛ የሊቀ ጳጳሳቱን ድምፅ እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ለማድረስ ይቻል ዘንድ የሬዲዮ ጣቢያ እንዲመሰርት ለአቶ ጉሌሊሞ ማርኮኒን ቅዱስነታቸው ጥያቄ በማቀረባቸው የተነሳ የተቋቋመ የሬዲያ ጣቢያ እንደ ሆነም ይታወቃል።
ጉልየልሞ ማርኮኒ 1866-1929 ዓ.ም ድረስ የኖረ የጣልያን አገር ተወላጅ መሀንዲስ ሲሆኑ በ1885 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ ስለ ሠሩት የሬዲዮ ጣቢያ ፈጠራ ይታወሳሉ። የሬዲዮ ቴክኖሎጂ ብዙ ተመራማሪዎች የተሳተፉበት እና ብዙ ጊዜ የወሰደ ጥረት ነው እንጂ ያንድ ሰው ድንገተኛ ፈጠራ አይደለም። ሆኖም አንዳንድ ተመራማሪዎች ከሌሎች በተለየ መልኩ ጉልህ አስተዋጾ ስላደረጉ በታሪክ ተጠቃሽ ናቸው፣ ከነዚህ ውስጥ ቶማስ ኤድሰን፣ ኒኮላ ቴስላ እና ጉልየልሞ ማርኮኒ ዋናዎቹ ናቸው። በ1885 ዓ.ም. ኒኮላ ቴስላ እንዴት መልዕክትን ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ያለ ሽቦ ማስተላለፍ እንደ ሚቻል አሳየ ። ከዚያ በኋላ ተመራማሪዎች፣ አንዱ ያንዱን ስራ በማሻሻል በ1887 ዓ.ም. ማርኮኒ ያለ ሽቦ መልዕክትን ከአንድ ቦታ ወደሌላ ሩቅ ቦታ የሚያስተላልፍ ስርዓት በተጨባጭ በመገንባት (2.4 ኪሎ ሜትር) በአየር ሞገድ መጓዝ የሚችል የፈጠራ ተግባር ማበርከቱ የሚታወስ ሲሆን ከአንድ አመት በኋላ ደግሞ ከእንግሊዝ አገር ለሬዲዮ የፈጠራ መብት ስርትፍኬት በማግኘት አሁን ድረስ ስሙ ተጠቃሽ ነው። በ1889 ዓ.ም ማርኮኒ የመጀመሪያውን የሬዲዮ ማሰራጫ እንግሊዝ አገር ውስጥ በመክፈት እንዲሁም የራዲዮን ማምረቻ ፋብሪካ በማቋቋም ስሙ ከራዲዮ ፈጠራ ጋር እንዲቆራኝ እየተዘከረ ይኖራል።