ፈልግ

የመለኮታዊ ምሕረት፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ምስል የመለኮታዊ ምሕረት፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ምስል  

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፥ “ልባችንን ለመሐሪው ኢየሱስ መክፈት ያስፈልጋል” አሉ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ እሑድ የካቲት 14/2013 ዓ. ም ካቀረቡት ሳምንታዊ የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ በመቀጠል በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተገኙት ምዕመናኑ ጋር ሆነው የብስራተ ገብርኤል ጸሎት ደግመዋል። ከጸሎት ሥነ-ሥርዓቱ በመቀጠል የመሐሪው ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ምስል የታየበትን ዘጠና ዓመት በማስተውስ መልዕክት አስተላልፈዋል። በመልዕክታቸውም “ወደ መላው ዓለም የደረሰው መልካም ዜና ሌላ ሳይሆን፣ እኛን ለማዳን ሞቶ ከሞት የተነሳው የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ነው” በማለት አስረድተዋል። በፖላንድ አገር የሚገኘውን ቅዱስ ሥፍራን በማስታወስ የሚከተለውን መልዕክት አስተላልፈዋል፥

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ከዛሬ ዘጠና ዓመት በፊት እግዚአብሔር በቅድስት ፋውስቲና ኮዋልስካ አማካይነት ልዩ የመለኮታዊ ምሕረት መልዕክቱን ልኮልናል። ይህን መልዕክት የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ወደ መላው ዓለም እንዲደርስ አድርገዋል። ይህ መልዕክት እኛን ለማዳን ሞቶ፣ ከሞት የተነሳው የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል፣ የአባቱን ምህረት የሚሰጠን በመሆኑ ልባችንን ከፍተን ‘ጌታ ሆይ! አንተ መታመኛዬ ነህ’ እንበለው”።

ዓመቱ እ. አ. አ. የካቲት 22/1931 ዓ. ም. ነበር።  በፖላንድ አገር የምሕረት እናት ብጽዕት ድንግል ማርያም ገዳም አባል ለሆነች ቅድስት ፋውስቲና ኮዋልስካ የኢየሱስ ክርስቶስ መልክ ተገልጦላት ነበር። ቅድስት ፋውስቲና ይህን ታሪክ በማስመልከት በማስታወሻ ደብተሯ ባሰፈረችው ጽሑፍ “ኢየሱስ ክርስቶስ ነጭ ልብስ ለብሶ፣ በአንድ እጁን ሲባርክ፣ በሌላኛው እጅ በደረት ላይ ያለውን ልብሱን ሲነካ ሁለት ትላልቅ የብርሃን ጨረሮች ፣ አንድ ቀይ እና ሌላውን ሐመር ሲወጡ ተመልክቼአለሁ፤ በዝምታም ዓይኖቼን ወደ ጌታ በማቅናት አተኩሬ ማየት ጀመርኩ፤ ነፍሴም በፍርሃት እና በታላቅ ደስታም ተሞላች፤ ከትንሽ ጊዜ በኋላ ኢየሱስም እንዲህ አለኝ፥ ‘የሚታይሽን ምስል በመከተል አንድ ሥዕል ሳዪ፣ በስተ ግርጌውም ‘ኢየሱስ ሆይ! አንተ መታመኛዬ ነህ’ በማለት ከጻፍሽ በኋላ ይህ ስዕል በመጀመሪያ በጸሎት ቤታችሁ ውስጥ፣ ከዚያም ቀጥሎ በመላው ዓለም እንዲከበር እፈልጋለሁ’ የሚል መልዕክት መስማቷን በጽሑፍ ገልጻለች። በእህት ፋውስቲና መሪነት የተሳለ ታዋቂው የመሐሪ ኢየሱስ የመጀመርያው ምስል በፖላንድ ውስጥ በክራኮቪያ-ዣጊኒኒኪ ከተማ በሚገኝ በመለኮታዊ ምህረት ቤተክርስቲያን ውስጥ በክብር ተቀምጦ ይገኛል።

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከተለያዩ አካባቢዎች ለመጡት ነጋዲያን፣ ወጣቶች እና የ “ታሊታ ኩም” ዓለም አቀፍ ገዳማዊያት ማኅበር አባላት ሰላምታቸውን አቅርበው፣ ገዳማዊያቱ የጀመሯቸውን የመልካም ተግባር እቅዶች በደስታ እንዲያከናውኑ አደራ ካሏቸው በኋላ፣ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት በሙሉ ሰላምታቸውን አቅርበው ሲያበቁ፣ ምዕመናኑ በጸሎታቸው እንዲያስታውሷቸው ከጠየቁ በኋላ መልካም ዕለተ ሰንበትን ተመኝተው፣ በቡራኬ ወደ ቤታቸው ሸኝተዋቸዋል።  

23 February 2021, 15:19