ፈልግ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እና የአል-አዝሃር ታላቁ ኢማም አህመድ አል-ታይየብ እ.አ.አ በ2019 ዓ.ም በአቡዳቢ በተገናኙበት ወቅት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እና የአል-አዝሃር ታላቁ ኢማም አህመድ አል-ታይየብ እ.አ.አ በ2019 ዓ.ም በአቡዳቢ በተገናኙበት ወቅት  

የሰብዓዊ የወንድማማችነት ቀን አከባበር የአንድነት ፍላጎትን ጎላ አድርጎ ያሳያል መባሉ ተገለጸ!

ሐሙስ ጥር 27/2013 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሰው ልጆች አንድነት የሚዘከርበት በበይነ መረብ አማካይነት የተከናወነ ስብሰባ እና የሽልማት ስነ ስርዓት ላይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እና የአል-አዝሃር ታላቁ ኢማም አህመድ አል-ታይየብ የወንድማማችነት እና የአብሮነትን አስፈላጊነት አጉልተው መናገራቸው ይታወሳል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሀፊ  አቶ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ እና የሞሮኮ እና የፈረንሳይ ጥምር ዜግነት ያላቸው የመብት ተሟጋች የሆኑት ወይዘሮ ላቲፋ ቤን ዛያቲን እንዲሁ እ.አ.አ የ2021 ዓ.ም የሰብዓዊ ወንድማማችነት የዛይድ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ሐሙስ ጥር 27/2013 ዓ.ም የተከበረው የመጀመሪያ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ የወንድማማችነት ቀን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስን ጨምሮ በርካታ ታዋቂ ግለሰቦች የተካፈሉበት እንደ ነበረ የተገለጸ ሲሆን ይህ በበይነ መረብ አማካይነት የተደረገው ስብሰባ ከአቡዳቢ ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድን ጨምሮ የአል-አዝሃር ኢማም ፣ አሕመድ አል-ታይየብ ፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬስ እና ሌሎች ግለሰቦችም ስብሰባውን ታድመዋል።

የበዓሉ አንዱ ክፍል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ እና የሞሮኮ-ፈረንሳዊ ጥምር ዜግነት ያላቸው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች እና የኢማድ የወጣቶች እና የሰላም ማህበር መስራች ላቲፋ ቤን ዛያቲን እ.አ.አ የ 2021 ዓ.ም  ዛይድ የሰብዓዊ ወንድማማችነት አመታዊ ሽልማት እንደ ተበረከተላቸውም ይታወሳል።

በሰብዓዊ ፍጡር ወንድማማችነት ላይ በከፍተኛ ሁኔታ አዎንታዊ የሆኑ ተግባራትን የሚያከናውኑ እና ስብዓዊ ወንድማማችነት በመላው ዓለም እንዲገነባ ጠንክረው ለሚሰሩ ሰውች የሚሰጠው የዛይድ ሽልማት ለሰላም አብሮ መኖር ሁኔታዎችን ለማጎልበት ቁርጠኛ ለሆኑ ግለሰቦች ዕውቅና ይሰጣል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮም ሆኑ አሕመድ አል-ታይብ በአቡዳቢ እ.ኤ.አ. የካቲት 4 /2019 ዓ.ም ባደረጉት ታሪካዊ ስብሰባ ላይ ሰብዓዊ ወንድማማችነት በተመለከተ በቀረበው ሰንድ ላይ መፈረማቸው የሚታወስ ሲሆን የሰነዱን ዓላማ እውን ለማድረግ የተቋቋመ ከፍተኛ የሰብዓዊ ወንድማማችነት ጉዳይ ላይ የሚሰራ ከፍተኛ ኮሚቴ እንዲፈጠርም አነሳስቷል።

የሰላም እና የወንድማማችነት በዓል

የሰብዓዊ ወንድማማችነት ከፍተኛ ኮሚቴ ዋና ፀሐፊ የሕግ ባለሙያ የሆኑት መሐመድ አብደል ሰላም የበዓሉን አከባበር አስፈላጊነት ሲገልጹ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰጠው ውሳኔ የካቲት 4 ቀን - የሰብዓዊ ወንድማማቸነት ሰነድ የተፈረመበትን ቀን - እንደ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ወንድማማቾች ቀን ሆኖ እንዲከበር መወሰኑን ገልጸዋል።

ወጣቶች እንዲያልሙ ፣ ተስፋ እንዲኖራቸው እንዲሁም “በፈገግታ ስለ መጪው ጊዜ እንዲያስቡ” እለቱ እንደ ሚረዳቸው የገለጹ ሲሆን አክሎም ሁላችንም ወንድማማቾች በመሆናችን ይህ የወንድማማችነት መንፈስ በተግባራ ይገለጽ ዘንድ ጥሪ አቅርበዋል።

የአንግሊካን የካንተርበሪ ሊቀ ጳጳስ ጀስቲን ዌልቢ በሰብዓዊ ወንድማማችነት ላይ የሚያተኩረው በአቡዳቢ የተፈረመው ሰነድ አስፈላጊነት ላይ ሲናገሩ “አንድ ላይ ምን ማድረግ እንደምንችል የሚያመለክት እና እርስ በእርስ በመተባበር እንድንኖር  ጥሪ የሚያደርግ አነቃቂ ሰነድ ነው” ብለዋል።  አክለውም “ልናመጣው ባስብነው የወዳጅነት መንፈስ ላይ ዋና እና ትልቁን ሚና የሚጫወተው የወንድማማችነት መንፈስ ነው” በማለት አብረን እንድንሰራ እንደዚህ ዓይነት ወዳጅነት እንድናዳብር እንደ ሚጸልዩ ገልጸዋል።

የአውሮፓ ሕብረት ካውንስል ፕሬዝዳንት ቻርለስ ሚካኤል በበኩላቸው እንደ ገለጹት “ከሩቅ ባየነው ቁጥር ልዩነቶቻችንን በበለጠ ሁኔታ እናያለን ፣ ነገር ግን ዐይን ውስጥ እየተያየን ስንሄድ ነፀብራቃችንን እናያለን - የጋራ ሰብአዊነታችን እንገነዘባለን ” ብለዋል። አክለውም “መወያየት መግባባት እንዲፈጠር ያደርጋል ፣ መግባባት የመቻቻል መንፈስን ያነሳሳል ፣ መቻቻል ወደ መከባበር ይመራል፣ ይህ በጎ ሰንሰለት ሰላምን እና ወንድማማችነትን እውን ማድረግ ይችላል” በማለት ተናግረዋል።

የእውነት ድምፆች ለሰዎች ተስፋን ያመጣሉ

የሕግ ባለሙያ የሆኑት አብዱል ሰላም ለርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ እና ለታላቁ ኢማም ንግግሮች ላይ ተመስርተው እንደ ተናገሩት የሰብዓዊ ወንድማማችነት ከፍተኛ ኮሚቴው ተስፋን የሚያነቃቃ እንደ ሆነ የገለጹ ሲሆን ለሰው ልጆች አንድነት እና ወንድማማችነት የሚያደርጉትን ጥረት አድንቀዋል። ዓለም ለመጀመሪያ ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሰብዓዊ የወንድማማችነት ቀንን ስታከብር የተሰማቸውን ከፍተኛ ደስታ ገልጸዋል።

“ሁል ጊዜም እውነትን የሚናገር ድምጽዎ ለሁሉም ሰዎች ተስፋን ያመጣል” በማለት የተናገሩት አብዱል ሰላም “በተመሳሳይ ጊዜ በዓለም ዙሪያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በተመሳሳይ መንገድ እንዲራመዱ ያበረታታል። በዚህ ረገድ እነዚህ ድምፆች ጎልተው እንደ ሚወጡ ያላቸውን እምነት” የገለጹ ሲሆን የዛይድ ሽልማት ለሰብዓዊ ወንድማማችነት በተወከለው በዚህ ዓለም አቀፍ ተነሳሽነት አድናቆት እንዳላቸው ገልጸዋል።

የካቲት 4-ለዓለም የማስጠንቀቂያ ደወል

ታላቁ ኢማም አሕመድ አል-ታይየብ የሰብዓዊ የወንድማማችነት ሰነድ በትብብር፣ ጦርነቶች እንዲቆሙና መቻቻልና መግባባት እንዲሰፍን እንደሚጠይቅ አጉልተው የገለጹ ሲሆን የዚህ ዓለም አቀፍ ቀን ዓመታዊ በዓል “ለዓለም እና ለመሪዎች የማንቂያ ደወል” እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልፀው “የሰብዓዊ ወንድማማችነት መርሆዎች እንዲጠናክሩ” አሳስበዋል።

ታላቁ ኢማም ከሌሎች የሰላም ደጋፊዎች ጎን ለጎን ለሰላም መስራቱን ለመቀጠል ያላቸውን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል ፣ የሰብዓዊ ወንድማማችነት ሰነድ በሕይወት እውን እንዲሆን ቁርጠኝነት እና “ሁሉም ሰዎች መብት ያላቸው ወንድማማቾች ናቸው” የሚል ጽኑ እምነት እንዳላቸው የገለጹ ሲሆን በመካከላችን ያለው ልዩነት ቢኖርም በሰላም ለመኖር ” መጣር እንደ ሚኖርብን ተናግረዋል።

ወንድማማችነት-ለሰው ልጆች አዲስ አስተሳሰብ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ለወንድማማችነት መሰጠትን አስፈላጊነት አጥብቀው ተናግረዋል ፣ ምክንያቱም “ይህ የሰው ልጅ አዲስ አስተሳሰብን የሚጠይቅ ነው” በማለት አጽኖት ሰጥተው የተናገሩ ሲሆን ሁላችንም ወንድማማቾች እና እህተማማቾች እንደሆንን አበክረው ገልጸው “እኛ ለግድየለሽነት ጊዜ የለንም” ምክንያቱም እኛ ወንድሞች እና እህቶች ስለሆንን “ወይም ሁሉምንም ነገር አንድ ላይ እንገነባለን፣ ካልሆነ ደግሞ ሁሉም ነገር ሊፈርስ ይችላል” ብለዋል።

ወንድማማችነት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ቀጠሉ “የተዘረጋ እጅ ማለት ነው። ወንድማማችነት መከባበር ማለት ነው። ወንድማማችነት ማለት በተከፈተ ልብ ማዳመጥ ማለት ነው። ወንድማማችነት ማለት በራሱ እምነት ጽናት ማለት ነው፣ ምክንያቱም አንድ ሰው በእምነቱ ላይ ብቻ ጸንቶ ቢደራደር እውነተኛ ወንድማማችነት አይኖርም ” ብለዋል።

ተግዳሮቶች ቢኖሩም ለአንድነት መሥራት ያስፈልጋል

የዛይድ ሽልማት ተቀባይ እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሀፊ አቶ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ባቅረቡት የምስጋና ንግግር በዓለም ዙሪያ ሰላምን እና ሰብአዊ ክብርን ለማስፈን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እያደገው ላለው ተግባር እውቅና በመሰጠቱ ምስጋናቸውን ገልጸዋል።

በወቅቱ እየተከሰተ ያለው ወረርሽኝ ፣ የአየር ንብረት ለውጥ እና ሌሎች በጦርነት እና በግጭት ፣ በዘረኝነት ፣ በአመፅ አክራሪነት እና አድልዎ ላይ ያሉ የወቅቱ ተግዳሮቶች ቢኖሩም የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ እና የታላቁ ኢማም ሼክ መሐመድ አልጣይብ የሰው ልጆች በአንድነት እንዲሰባሰቡ ግፊት ማደረጋቸውን ገልጸው  በውይይት ውስጥ ሰላምን እና ወንድማማችነትን ለማሳደግ አስፈላጊ የሆነ እርምጃ መጀመሩን ገልጸዋል። አቶ አንቶኒዮ ጉተሬዝ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰውን አንድነት እና ዓለም አቀፋዊ ሰላምን ለማጎልበት የሚደረገውን ጥረት ለማጉላት እና ለመርዳት ፈቃደኛ መሆናቸውን በድጋሚ ገልፀዋል ፡፡

የጥላቻ አጥርን መሰባበር አለብን

ሁለተኛው የ 2021 ዛይድ ሽልማት የክብር ተሸላሚ የሆኑት የሲቪል ማህበረሰብ ተሟጋች እና የኢማድ የወጣቶች እና የሰላም ማህበር መስራች የሆኑት ላቲፋ ቤን ዛያቲን እንዲሁ ለሽልማቱ ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል። እውቅና ስለተሰጣቸው ብዙ ልጆችን “ወደ ጥላቻ” መስመር እንዳይገቡ በመከላከል ሥራቸው ትልቅ እገዛ እንደሚያደርግላቸው ተናግረዋል። ምንም እንኳን ልጃቸውን ቢያጡም እና በጭራሽ የማይድን ጥልቅ ቁስል ውስጥ የገቡ ቢሆንም አሁን ለብዙ ሌሎች ልጆች “ሁለተኛ እናት” ሆነዋል።

አክለውም “ለእያንዳንዱ ልጅ እንደምለው በልባችን ውስጥ ያሉትን መሰናክሎች ማቋረጥ ከቻልን በህብረተሰቡ ውስጥ ያለንን ቦታ እናገኛለን እናም ሁላችንም ወንድማማቾች እንሆናለን። ነገር ግን በእውነቱ እነዚህን መሰናክሎች ማቋረጥ አለብን ብለዋል።

05 February 2021, 14:05