ፈልግ

በጣሊያን ውስጥ ለኮቪድ-19 ወረርሽኝ ተጠቂዎች የሚሰጥ የሕክምና አገልግሎት በጣሊያን ውስጥ ለኮቪድ-19 ወረርሽኝ ተጠቂዎች የሚሰጥ የሕክምና አገልግሎት 

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ የተቸገረን መርዳት ከግለኝነት ስሜት የሚወጣበት መንገድ መሆኑን ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በቫቲካን የስነ-ሕይወት ጥናት ጳጳሳዊ አካዳሚ ፕሬዚደንት ለሆኑት ለብጹዕ አቡነ ቪንቼንሶ ፓሊያ በላኩት መልዕክት፣ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት በሥራ መስክ ሕሙማንን ሲረዱ ሕይወታቸውን ያጡ የሕክምና ዶክተሮችን፣ ነርሶችን እና ሌሎች የጤና ባለ ሞያዎችን አስታውሰዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው በሕክምና አገልግሎት ላይ ተሰማርተው በኮቪድ -19 ወረርሽኝ ተጠቅተው በሞት የተለዩን የሕክምና ዶክተሮች፣ ነርሶች እና የጤና ባለሞያዎች በሙሉ “ለጋስ” እና “ጀግና” ናቸው በማለት ገልጸዋቸዋል። ቅዱስነታቸው ይህን መልዕክት ለብጹዕ አቡነ ቪንቼንሶ ፓሊያ የላኩት በጣሊያን ውስጥ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ተጠቅተው ሕይወታቸውን ያጡትን የሕክምና ባለ ሞያዎች ለማስታወስ በተወሰነለት ዕለት መሆኑ ታውቋል። የመታሰቢያ ሥነ-ሥርዓቱ የተካሄደው በጣሊያን ውስጥ የኮሮና ቫይረስ ለመጀመሪያ ጊዜ የታየበትን አንደኛ ዓመት ለማስታወስ ሲሆን፣ ሥነ-ሥርዓቱን ያዘጋጀው በቫቲካን የስነ-ሕይወት ጥናት ጳጳሳዊ አካዳሚ መሆኑ ታውቋል።

የህብረተሰቡ ፈተና

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው፣ ሕይወታቸውን ለሞት አደጋ አሳልፈው የሰጡ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን የጤና ባለሞያዎች መልካም ምሳሌነት ከሁላችንም በኩል ከፍተኛ ምስጋናን እንድናቀርብላቸው እና እንድናስብ አድርጎናል ብለው፣ በዚህ የሕይወት መስዋዕትነት፣ መላው ኅብረተሰብ ከራስ ወዳድነት ወጥቶ ለጎረ ቤቱ ያለውን ፍቅር በተለይም የደከሙትን በመርዳት ምስክርነቱን በተግባር እንዲያሳይ የሚያደርግ ተግባር ነው ብለዋል።

ከግለኝነት ለመውጣት የሚያግዝ መንገድ ነው

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በማከልም፣ በዚህ አስፈሪ ወቅት በሆስፒታሎች እና በጤና ተቋማት ውስጥ የህክምና መገልገያ መሣሪያዎችን በመጠቀም የሕክምና አገልግሎታቸውን በመስጠት ላይ ያሉት የጤና ባለሞያዎች መልካም ምሳሌነት፣ ከግለኝነት እና ከራስ ወዳድነት ስሜት በመውጣት፣ ዕርዳታን ለሚሹ ዕርዳታን ማቅረብ፣ የራስን ሕይወት ለሞት አሳልፎ ለመስጠት የሚያስችል እውነተኛ ስሜት በሰው ልብ ውስጥ መኖሩን ያመለክታል ብለዋል። ቅዱስነታቸው በመጨረሻም፣ በመታሰቢያ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ለተገኙት በሙሉ መንፈሳዊ አንድነታቸውን በመግለጽ ሰላምታቸውን እና ቡራኬአቸውን ልከውላቸዋል። 

23 February 2021, 18:02