ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በግፍ የተገደሉ 21 ክርስቲያኖች የኢየሱስ ምስክሮች መሆናቸውን ገለጹ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ከስድስት ዓመት በፊት በእስላማዊ መንግስት ታጣቂዎች የተገደሉ 21 ሰማዕታትን ትናንት የካቲት 9/2013 ዓ. ም. በጸሎታቸው አስታውሰዋል። ቅዱስነታቸው በቪዲዮ መልዕክታቸው “እነዚህ በግፍ የተገደሉ ክርስቲያኖች ወንድሞቻችን ናቸው” በማለት ገልጸዋቸዋል። እ.አ.አ የካቲት 15/2015 ዓ. ም. 21 ክርስቲያኖች በእስላማዊ መንግስት ታጣቂ ኃይሎች ሲገደሉ የሚያሳይ አስደንጋጭ የቪዲዮ ምስል በመላው ዓለም ተሰራጭቶ እንደ ነበር ይታወሳል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ከስድስት ዓመታት በፊት በቁጥር 20 የግብጽ ኮፕት ኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች እና አንድ ጋናዊ ክርስቲያን ወጣት፣ ሊቢያ ውስጥ በስርጥ ከተማ ባሕር ዳርቻ እንዲንበረከኩ ተደርገው በመሣሪያ ታጣቂ አሸባሪዎች መገደላቸው ይታወሳል። ክርስቲያኖቹ በመሣሪያ ታጣቂዎች የተገደሉት እምነታቸውን እንዲክዱ በተጠየቁ ጊዜ “አሻፈረን”! በማለታቸው መሆኑ ይታወሳል። በወቅቱ የክርስቲያኖቹ መገደል የተረዱት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በቪዲዮ አማካይነት በላኩት የሐዘን መግለጭ መልዕክታቸው “ለእምነታቸው ሲሉ ሞትን በመምረጥ ምስክርነታቸውን የገለጹት ክርስቲያኖች በውሃ እና በመንፈስ የተጠመቁ ቀጥሎም በደም የተጠመቁ ናቸው” በማለት መናገራቸው ይታወሳ። የግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ብጹዕ ወ ቅዱስ ተዋድሮስ እ.አ.አ ከ2015 ጀምሮ የሟቾችን ስም በቤተክርስቲያናቸው የሰማዕታት መዝገብ ውስጥ ማስገባታቸው ይታወሳል። ር. ሊ. ጳጳሳት ፍራንችስኮስም “በግፍ የተገደሉት እነዚያ ክርስቲያኖች የእኛም ቅዱሳን፣ የመላው ክርስቲያን ወገኖች ቅዱሳን፣ ሕይወታቸውን በበጉ ደም ያጠቡ፣ ታማኝ የእግዚአብሔር ሕዝብ ወገን ናቸው” ማለታቸው ይታወሳል። 

ከአነስተኛ እምነት ውስጥ ትልቁ ስጦታን ማግኘት

ከስድስት ዓመት በፊት ር. ሊ. ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቪዲዮ አማካይነት የላኩት መልዕክት ጭብጥም ሕይወታቸውን በመሰዋት የኢየሱስ ክርስቶስ ምስክሮች የሆኑት በእምነት ጽናት መሆኑ የሚያመለክት ነበር። ቅዱስነታቸው በመልዕክታቸው “ሕይወታቸውን ለሞት አሳልፈው የሰጡት እነዚያ ክርስቲያኖች፣ እንደ እኛ ሰው፣ ሕይወታችወን በሥራ ለመለወጥ፣ ወላጆቻቸውን ለመደገፍ የወጡ ናቸው” በማለት መናገራቸው ይታወሳል።  

“ሕይወታቸውን ለሞት አሳልፈው በመስጠት የኢየሱስ ክርስቶስ ምስክሮች ሆነዋል። አንገታቸውን በጎራዴ ሲቀሉ “ጌታ ኢየሱስ ሆይ”! በማለት የኢየሱስን ስም ከፍ አድርገው አሰምተዋል። እውነት ነው፤ እነዚህ ሰዎች ሕይወታቸውን ያጡበት መንገድ፣ በባህር ዳርቻ ላይ ጥለው መሄዳቸው አሳዛኝ ነገር ነው። በሌላ ወገን ደማቸው የፈሰሰበት ያ ስፍራ የተቀደሰ ነው። በተጨማሪም በምስኪንነታቸው፣ ባለው አነስተኛ እምነት የተነሳ አንድ ክርስቲያን ሊያገኝ የሚችለውን ታላቅ ስጦታን አግኝተዋል፤ ይህም ሕይወቱን ለእኛ ሲል አሳልፎ የሰጠው የኢየሱስ ክርስቶስ ምስክርነት ነው”።  ማለታቸው ይታወሳል። 

የሰማዕታቱ እናቶችን እናመሰግናለን

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በቪዲዮ መልዕክታቸው፣ እነዚህን ቆራጥ ወንድሞቻችንን ለሰጠን እግዚአብሔር፣ ደማቸውን በማፍሰስ የኢየሱስ ክርስቶስ ምስክሮች እንዲሆኑ ኃይል ለሆናቸው መንፈስ ቅዱስ እና በእምነት ላሳደጓቸው የእህት ቤተክርስቲያን ብጹዓን ጳጳሳት፣ ካህናት እና የሐይማኖት መምህራን ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል። ቅዱስነታቸው እንዲሁም ልጆቻቸውን በመልካም ስነ-ምግባር እና በእምነት ላሳደጉ የሰማዕታቱ እናቶችም ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል።

ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ መሆኑን ስለ መመስከር

ከስድስት ዓመት በፊት ማለትም እ.አ.አ የካቲት 15/2015 ዓ. ም. በእስላማዊ መንግስት ታጣቂዎች የተገደሉ 21 ክርስቲያኖች መታሰቢያን የግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ብጹዕ ወ ቅዱስ ተዋድሮስ እና የአንግሊካን ኅብረት እና የካንተርቤሪው ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡን ጀስቲን ዌልቢ የተካፈሉት ሲሆን ር. ሊ. ጳጳሳት ፍራንችስኮስም ወንድም ከሆኑት ጳጳሳት ጋር መተባበራቸውን በቪዲዮ መልዕክታቸው ገልጸው፣ በተለይም ውድ እና ታላቅ ወንድም ያሏቸውን የግብጽ ኦርቶዶክስ ፓትሪያርክ፣ ብጹዕ ወ ቅዱስ ታዎድሮስን አስታውሰዋል። በመታሰቢው ዕለት ለመገኘት ፈቃደኛ የሆኑትን የካንተርቤሪውን ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ጀስቲን ዌልቢን አመስግነዋቸዋል። ቅዱስነታቸው በመቀጠልም የእግዚአብሔርን ታማኝ ሕዝብ፣ ምንም እንኳን በኃጢአት ውስጥ ቢገኝም በእምነቱ ታማኝ በመሆን፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ መሆኑን ለሚመሰክሩት በሙሉ ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል።

ር. ሊ. ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መልዕክታቸውን ባጠቃለሉበት ወቅት፣ ሃያ አንዱ ሰማዕታት ጸሎታችንን ወደ እግዚአብሔር ፊት እንዲያቀርቡ ምዕመናን በጸሎት እንዲተባበሩ ጠይቀዋል። ቅዱስነታቸው የ21 ክርስቲያኖች መገደል በተረዱበት ወቅት እ.አ.አ በካቲት ወር 2015 ዓ. ም. በቫቲካን በሚገኝ ቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ውስጥ ባሳረጉት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት፣ እግዚአብሔር በሰማዕትነት እንዲቀበላቸው በማለት መጸለያቸው ይታወሳል።      

16 February 2021, 12:35