ፈልግ

የዐብይ ጾም ወቅት እምነት ፣ ተስፋ እና ፍቅር የሚታደስበት ወቅት ነው! የዐብይ ጾም ወቅት እምነት ፣ ተስፋ እና ፍቅር የሚታደስበት ወቅት ነው! 

የዐብይ ጾም ወቅት እምነት ፣ ተስፋ እና ፍቅር የሚታደስበት ወቅት ነው!

የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በምትከተለው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ የዐብይ ጾም ረቡዕ እለት የካቲት 10/2013 ዓ.ም ላይ ግንባርን በዐመድ የመቀባት ሥነ ስርዓት ከተፈጸመ በኋላ በይፋ መጀመሩ የሚታወስ ሲሆን ለመጪዎቹ አርባ ቀናት በጸሎት፣ በጾም እና ምጽዋዕት በመስጠት የሚፈጸመው ጾም እግዚኣብሔርን የሚያስደስት ጾም ይሆን ዘንድ፣ ለጿሚው ሰው ደግሞ መንፈሳዊ ጸጋ የሚያስገኝለት ጾም ይሆን ዘንድ፣ እንዲሁም የፋሲካን በዓል ዋና ትርጉሙን በጠበቀ መልኩ ለማክበር ይቻል ዘንድ መንፈሳዊ ዝግጅት የሚደረግበት ወቅት መጀመሩ ይታወሳል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ወደ ፋሲካ በዓል በሚያመራው በዚህ የዝግጅት ወቅት እና በእዚህ በዐብይ ጾም ወቅት ከሚመጣጠኑ እና ከተያያዙ ጭብጦች በመጀመር የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስን ሀሳቦችን እናቀርብላችኋለን።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የዓብይ ጾም ወቅት ተሞክሮ ለመለማመድ ያስችለን ዘንድ የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ የ2021 ዓ.ም (እ.አ.አ.) ዐብይ ጾም መልእክታቸውን ይፋ ባደረጉበት ወቅት የዐብይ ጾም ወቅት “ሕይወቱን በመስቀል ላይ የሰጠውን የክርስቶስን ተስፋ መቀበል” ማለት ነው ማለታቸው ይታወሳል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ እ.አ.አ ለ2021 ዓ.ም በዐብይ ጾም መልእክታቸው ላይ “ዐብይ ጾም ለማመን ፣ እግዚአብሔርን በሕይወታችን ለመቀበል እና እርሱ በመካከላችን እንዲኖር” የምንፈቅድበት ጊዜ ነው ማለታቸው የሚታወስ ሲሆን እርሱ “ራሱን አዋረደ፣ ለሞትም ያውም በመስቀል ላይ ለመሞት እንኳ ራሱን ታዛዢ አደረገ” እኛም ይህንን የምናስታውስበት ወቅት ነው ማለታቸው ይታወሳል።

ይህ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሱ መልዕክት እነዚህ ቃላት የመታሰቢያ ልኬትን የሚያመለክቱ ብቻ ሳይሆኑ እምነትን ፣ ተስፋን እና ምጽዋትን ለማድረግ ያስችለን ዘንድ ሕይወታችንን የምናድስበት አመቺ ጊዜ እንኳን ዛሬ እንዲኖረን ይጋብዙናል። ሁሉም እንዲከተሉት እና እንዲያድጉበት የተጠየቁት "በኢየሱስ ክርስቶስ ውስጥ እኛ እግዚአብሔር 'ሁሉን አዲስ የሚያደርግበት' የአዳዲስ ጊዜ ምስክሮች መሆናችንን በመገንዘብ ነው” ብለዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በሊቀ ጵጵስና ዘመናቸው ሁሉ ወደ ፋሲካ የሚወስደውን የጉዞ ትርጉም ብዙ ጊዜ ገልጸዋል፣ አብራርተውማል። በየካቲት 14/2013 ዓ.ም ላይ ቅዱስነታቸው በቫቲካን በሚገኘው የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡ ምዕመናን በእለቱ ቅዱስ ወንጌል ላይ ተንተርሰው ባደረጉት አስተንትኖ የሚከተለውን ብለው ነበር . . . “በዐብይ ጾም ወቅት መንፈስ ቅዱስ እኛንም እንደ ኢየሱስ ወደ በረሃ ይመራናል … በረሃ ቁሳዊ የሆነ  ቦታ ማለት አይደለም ፣ ነገር ግን እኛ የምንሆንበት ነባራዊ ልኬት ነው፣ በጸጥታ እና በዝምታ የእግዚአብሔርን ቃል የምንሰማበት ምናባዊ የሆነ” ስፍራ ነው ማለታቸው ይታወሳል።

የዐብይ ጾም ጉዞ እምብርት

በጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር መሰረት የላቲን ሥርዐተ አምልኮ በምትከተለው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ የዐብይ ጾም ረቡዕ እለት የካቲት 10/2013 ዓ.ም ላይ ግንባርን በዐመድ የመቀባት ስርዓት በይፋ በተጀመረበት ወቅት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ መስዋዕተ ቅዳሴ ባሳረጉበት ወቅት ባሰሙት ስብከት “ዐብይ ጾም ሕይወታችንን በሙሉ ፣ መላ ሕይወታችንን የሚያካትት ጉዞ ነው” ማለታቸው ይታወሳል። አክለውም . . .

የምንጓዝበትን ጎዳና እንደገና ለማጤን ፣ ወደ ቤታችን የሚወስደንን መስመር ለመፈለግ እና የሁሉም ነገር ምንጭ ከሆነው ከእግዚአብሄር ጋር ያለንን ጥልቅ ግንኙነት እንደገና መልሰን የምንጎናጸፍበት ጊዜ ነው። ዐብይ ጾም ስለምንከፍለው ትንሽ መስዋእትነት ብቻ ሳይሆን ልባችን ወዴት እንደሚመራን ማወቅ እንድንችል የሚረዳን ወቅት ነው። ይህ የዐብይ ጾም የሕይወታችን ሁሉ እምብርት ነው።

ባልፈው አመት የካቲት 18/2012 ዓ. ም በዐብይ ጾም ወቅት ቅዱስነታቸው በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡ ምዕመናን በእለቱ ቅዱስ ወንጌል ላይ ተንተርሰው ባደርጉት አስተንትኖ የሚከተለውን ብለው ነበር . . .

የዐብይ ጾም ወቅት ለእግዚአብሔር ቃል ቦታ የምንሰጥበት ወቅት ነው። ቴሌቪዥናችንን አጥፍተን መጽሐፍ ቅዱስን የሚንከፍትበት ወቅት ነው። ከተንቀሳቃሽ ስልክ ጋር ያለንን ቁርኝት አስወግደን ከቅዱስ ወንጌል ጋር የምንገናኝበት ወቅት ነው። በልጅነቴ እኛ ቤት ቴሌቪዥን አልነበረም። ነገር ግን ሬዲዮ የማዳመጥ ልምድ ነበረን። ነገር ግን እርሱንም ቢሆን በዐብይ ጾም ወቅት ማዳመጥ እናቆማለን።  እራሳችንን ከሞባይል ስልክ አላቀን ከወንጌል ጋር የምንገናኝበት ወቅት ነው። አላስፈላጊ ቃላትን ፣ ወሬዎችን ፣ አሽሙሮችን፣ ሐሜትን በመተው ከ“ጌታ” የምንነጋገርበት ወቅት ነው። ለልባችን ጤንነት የሚሆን መልካም ስነ-ምዕዳር የምንፈጥርበት ወቅት ነው። ልባችንን የምናጸዳበት ወቅት ጭምር ነው።  አሁን የምንኖርበት ሁኔታ ብዙ የቃላት ጥቃቶች የሚፈጸሙበት፣ በብዙ አፀያፊ እና ጎጂ ቃላት በተበከለ አካባቢ ውስጥ ነው። ዛሬ ስድብ እንዲያው እንደ ቀላል ነገር አድርገን “መልካም ቀን” ብሎ እንደመናገር አድርገን ቆጥረን ቀለል አድርገን እንሳደባለን። እኛ ባዶ በሆኑ ቃላት፣ በማስታወቂያዎች እና በስውር በምናስተላልፋቸው መልእክቶች ተሞልተናል። ስለ እያንዳንዱ ሰው ሁሉንም ነገር ለመስማት እንፈልጋለን። በዚህ የተነሳ ልባችንን ወደ ዓለማዊ መንፈስ ውስጥ እንከተዋለን። ይህንን ለመፈወስ የሚያስችለን ግን ዝምታ ነው። የምናገረውን የጌታን ድምፅ ፣ የሕሊናን ድምጽ ፣ መልካም የሆነ ድምጽ ለመለየት እንታገላለን። ኢየሱስ በምድረ በዳ ውስጥ ሲጠራን አስፈላጊ ያልሆኑ ድምጾችን በመተው አስፈላጊ የሆኑ ድምጾችን ብቻ እንድንሰማ ይጋብዘናል። ኢየሱስ በምደረ በዳ ለፈተነው ዲያቢሎስ-“ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣው ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም” (ማቴ. 4፡ 4) በማለት ምላሽ ሰጥቷል። የእግዚአብሔር ቃል ከሚያስፈልገን እንጀራ በላይ የሆነ ቃል ነው። ከእግዚአብሔር ጋር መነጋገር አለብን ፣ መጸለይ አለብን። ምክንያቱም የልብን ዝንባሌ ወደ ብርሃን በማምጣት ልባችን እንዲፈወስ የሚያደርገው እግዚአብሔር ነው። ከጌታ ጋር በጸጥታ በመነጋገር መልስ እንድናገኝ ስለሚያደርገን ሕይወትን ይሰጣል፤ ምድረ በዳ የሆነውን ያለመልማል።

በየካቲት 18/2012 ዓ.ም ላይ ቅዱስነታቸው ባደረጉት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ “የዐብይ ጾም ወቅት እግዚአብሔር በፍቅር እንዲመለከተን የምናደርግበት እና ሕይወታችንን የምንቀይርበት የጸጋ ወቅት ነው” ማለታቸው ይታወሳል።

በየካቲት 27/2011 ዓ.ም ዐብይ ጾም በተጀመረበት ወቅት “በእውነተኛ ልብ እግዚኣብሔርን እንዳናመልክ ልባችንን በመጥፎ ነገሮች በመሙላት ከእግዚኣብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት የሚያበለሹብንን ጣዖታት፣ ገንዝብ እና ምድራዊ የሆን የማያቋርጡ ፍላጎቶቻችንን በማስወገድ በዚህ የዐብይ ጾም ወቅት ልባችንን ከክፉ ነገሮች የምናጸዳበት የጸጋ ወቅት ነው ሊሆን ይገባል፣ የዐብይ ጾም ወቅት የህይወት አቅጣጫን ዳግም ለማግኘት እድል የሚሰጠን ወቅት ነው” ማለታቸው ይታወሳል።

በጥር 7/2010 ዓ.ም. የጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ምዕመናን ዘንድ የተጀመረውን የዐብይ ጾም አስመልክተው ቅዱስነታቸው በሮም ከተማ ውስጥ በሚገኘው በቅድስት ሳቢና ባዚላክ ተገኝተው ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ባሰሙት ስብከት የሚከተለውን ማለታቸው ይታወሳል . . .

የዐብይ ጾም ወቅት ከክርስትና ሕይወታችን ጋር የማሄዱ ተግባሮቻችንን በማስተካከል እና በመታደስ የጌታን ትንሣሄ በጉጉት የምንጠባበቅበት ወቅት ነው” ማለታቸው ይታወሳል። አክለውም “የዐብይ ጾም ወቅት ፈተናዎችን ነቅሰን የምናወጣበት ወቅት ነው፣ የልብ ምታችን ትርታ በኢየሱስ ቅኝት እንዲመታ የምናደርግበት ወቅት ነው። ይህንን የዐብይ ጾም ወቅት በእዚህ ዓይነቱ እምነት ተሞልተን መፈጸም ይኖርብናል፣ ይህንንም ስናደርግ የክርስቲያኖችን ልብ ብርሃን እንደ ገና እንዲበራ የሚያደርጉትን ለአፍታ ያህል ቆም ማለት፣ መመልከት እና መመለስ የሚሉትን ነገሮች በሕይወታችን መለማመድ ይኖርብናል።

ለአፍታ ያህል ቆም ማለት እዩኝ እዩኝ ከሚያሰኘን መንፈስ እና በሁሉም ዘንድ እንደ ማስታወቁያ ሰሌዳ ከመታየት እንድንቆጠበ ያደርገናል። ሕይወታችንን አንድ ጊዜ ቆም ብሎ መመልከት የሚጠቅመው፣ ኩራትን በማስወገድ፣ የርህራሄ ልብ እንዳይኖረን ከሚያደርጉ ነገሮች በመራቅ፣ በኃጢአትና በስህተት የተጠቁት እና ለተጎዱ፣ ለመጥፋት ከተጋለጡት ጋር በመተባበር ልባዊ ርህራሄ እና አክብሮት እንዲኖረን ያደርገናል።

ሕይወታችንን አንድ ጊዜ ቆም ብለን መመልከት የሚጠቅመው፣ ሁሉን ነገር በቁጥጥራችን ሥር እናድርግ ከሚል ስሜት፣ ሁሉን ነገር እናውቃለን ከሚል ስሜት፣ ሁሉን ነገር ወደ ጥፋት መንገድ ከመምራት እንድንቆጠብ ያግዘናል። ይህን ማድረግ የምንችለው ሕይወትንና መልካም የሆኑ ስጦታዎችን በሙሉ ለሰጠን እግዚአብሔር ምስጋናችንን ማቅረብ ስንችል ነው።

ሕይወታችንን አንድ ጊዜ ቆም ብለን መመልከት የሚጠቅመው፣ የማዳመጥ ችሎታችንን በመቀነስ፣ ፍሬያማ እንዳንሆን በማድረግ እይታችንን ከሚጋርዱን ነገሮች ነጻ እንድንሆን ይረዳናል። ሕይወታችንን ለአንድ አፍታ ቆም ብለን መመልከት መካን እንድንሆን ከሚያደርጉን እና በብቸኝነታችን የተነሳ ከሚፈጠሩት ገንቢ ካልሆኑ ሐሳቦች እና ከራስ ወዳድነት መንፈስ፣ ወንድሞቻችንን እንዳንገናኝ ከሚያደርጉን ጫናዎቻቸውን እና መከራዎቻቸውን ችላ እንድንል ከሚያደርጉን ነገሮች ነጻ እንድንወጣ ያደርገናል።

ሕይወታችንን ለጥቂት ጊዜ ቆም ብለን መመልከት በውስጣችን ያለውን ባዶነት እንድንመለከት፣ ጊዜያዊ እና በነው የሚጠፉ ነገሮችን፣ ከሥር ምሰረታችን ከሚለዩን ነገሮች፣ ነባር ከሆኑ ግንኙነቶች የሚለያየንን፣ እሴቶቻችን ጠብቀን እንዳንሄድ ከሚያደርጉ ነገሮች እና ጉዞዎቻችንን በማስተዋል እንዳንጓዝ የሚያደርጉ ነገሮችን ነቅሰን ለማውጣት ይረዳናል።

24 February 2021, 21:55