ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በቅዱስ ጳውሎስ ባዚሊካ ውስጥ ለክርስቲያኖች አንድነት የቀረበውን የመዝጊያ ጸሎት ሥነ-ሥርዓት ሲመሩ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በቅዱስ ጳውሎስ ባዚሊካ ውስጥ ለክርስቲያኖች አንድነት የቀረበውን የመዝጊያ ጸሎት ሥነ-ሥርዓት ሲመሩ 

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ አንድነትን በማሳደግ፣ ለሚሰቃዩት በሙሉ ፍቅርን እንድንገልጽላቸው አሳሰቡ

ከጥር 10/2013 ዓ. ም. ጀምሮ ሲካሄድ የቆየው 54ኛ ዙር የክርስቲያኖች አንድነት የጸሎት ሳምንት ጥር 17/2013 ዓ. ም. መፈጸሙ ተገለጸ። ሮም በሚገኘው በቅዱስ ጳውሎስ ባዚሊካ ውስጥ በተካሄደው የመዝጊያ ሥነ-ሥርዓት ላይ የልዩ ልዩ አብያተ ክርስቲያናት መሪዎች እና ተወካዮች የተገኙ ሲሆን፣ በዕለቱ የተደረገውን የጸሎት ሥነ-ርዓት ር. ሊ. ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መርተዋል። ቅዱስነታቸው የክርስቲያኖችን አንድነት በሚመለከት የቅዱስ ወንጌል ንባብ ላይ በማስተንተን ስብከታቸውን አቅርበዋል።

ክቡራት እና ክቡራን፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በዕለቱ ያደረጉትን ስብከት ሙሉ ይዘቱን ተርጉመን እንደሚከተለው አቅርበነዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

"ኢየሱስ ክርስቶስ፣ “በፍቅሬ ኑሩ” (ዮሐ. 15:9) በማለት ከወይን ግንድ እና ቅርንጫፎቹ  ጋር በማመሳሰል ሚያቀርብልን ጥሪ ወንጌላት ለእኛ ከሰጡን ጥሪዎች መካከል የመጨረሻው ነው።  በዮሐ. 15:1 ላይ “እውነተኛ የወይን ግንድ እኔ ነኝ” ያለው ጌታችን በቃሉ ታማኝ፣ እኛ ኃጢአተኞች የተለያየን ብንሆንም ፍቅሩ አላጎደለብንም።  የወይን ግንዳችን በሆነው በኢየሱስ ላይ የተደገፍን እኛ ቅርንጫፎቹ ፍሬን ማፍራት የምንችለው በእርሱ አንድ ስንሆን ነው። በዛሬው ዕለት ሦስት ክፍሎች ያሉትን ውድ አንድነታችንን በኅብረት እንመለከታቸዋለን። የወይኑን ዛፍ ምሳሌ በምናስብበት ጊዜ በአንድ ግንድ ውስጥ የሚገኙትን ሦስት ክፍሎች እንመለከታለን።

የመጀመሪያው ደረጃ በጥልቀት የሚገኘው በኢየሱስ ክርስቶስ መኖር ነው። አንድነትን ለማምጣት የምናደርገው የእያንዳንዳችን ጉዞ የሚጀምረው ከኢየሱስ ነው። በዛሬው ፈጣን እና ውስብስብ በሆነው ዓለማችን ከብዙ አቅጣጫዎች በሚጎትቱን ነገሮች የተነሳ አንድነታችንን በቀላሉ ልናጣው እንችላለን። ብዙዎች ተለዋዋጭ በሆነ ሕይወት ውስጥ መገኘታቸው ቋሚ እና የተረጋጋ በሆነ መሠረት ላይ እንዳይቆሙ ከማድረግ በላይ በውስጣቸው የመበታተን ስጋትን ፈጥሮባቸዋል። ኢየሱስ በእርሱ ውስጥ በመቆየት የሚመጣውን የመረጋጋት ምስጢር ያሳየናል። ከዮሐ. ምዕ. 15፡1-7 እና  9-10 የተጻፈው ጥቅስ ስለዚህ ጉዳይ በተደጋጋሚ ሰባት ጊዜ ያስረዳል። ኢየሱስ ያለ እርሱ ምንም ማድረግ እንደማንችል ያውቃል (ዮሐ. 15፡5)።  በእርሱ ለመኖር እንዴት እንደምንችል ምሳሌን በመስጠት አሳይቶናል። በየቀኑ መጸለይ ጸጥ ወዳለ ሥፍራ ይሄድ ነበር። ውሃ በሕይወት ለመኖር እንደሚያግዘን ሁሉ ጸሎትም እንደዚሁ ያስፈልገናል። ከኢየሱስ ጋር ለመኖር  በግል የምናቀርበው የውዳሴ እና የምስጋና ጸሎት እጅግ አስፈላጊ ነው።

ጸሎት በልባችን ውስጥ የሚገኙትን ፣ ተስፋ እና ፍርሃትን ፣ ደስታ እና ሀዘንን ሁሉ በጌታ ልብ ውስጥ ለማስቀመጥ የሚያግዝ መንገድ ነው። ከሁሉም በላይ በጸሎት ከኢየሱስ ጋር ከሆንን፣ በእርሱ ፍቅር ውስጥ መኖርን እንለማመዳለን። ቅርንጫፍ ለማደግ ጠቃሚ የሆኑ ነገሮችን ከግንድ እንደሚያገኝ ሁሉ ሕይወታችን ሕልውናውን የሚያገኘው ከኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ይህም በግል ጥረታችን የተነሳ፣ በኢየሱስ ላይ በመሆን የምናገኘው የመጀመሪያው የአንድነት ጸጋ ሥራ ነው።

ሁለተኛው ደረጃ ከክርስቲያኖች ጋር የምናደርገው አንድነት ነው። እኛ የአንድ ወይን ቅርንጫፎች በመሆናችን፣ በእያንዳንዳችን የሚፈጸም መልካም ሆነ መጥፎ ተግባር ወደ ሌሎች በቀላሉ ይደርሳል። በመንፈሳዊ ሕይወት በእግዚአብሔር በምንኖርበት መጠን ወደ ሌሎች እንቀርባለን፤ እንዲሁም ወደ ሌሎች በምንቀርብበት መጠን በእግዚአብሔር  እንኖራለን። ይህ ማለት እኛ እርስ በርሳችን ብንፋቀር እግዚአብሔር በእኛ ይኖራል፤ ፍቅሩም በእኛ ፍጹም ይሆናል (1ኛ ዮሐ. 4፡12)።  ወደ ፍቅር  ሊመራን የሚችል ጸሎት ብቻ ነው። አለበለዚያ አድካሚ እና አሰልቺ ሥነ-ስርዓት ሆኖ ይቀራል። በብዙ ክፍሎች ተዋቀረው በጥምቀት አንድ ከሆኑ በርካታ ሰዎች ጋር መገናኘት የምንችለው በኢየሱስ ስጋ አማካይነት ብቻ ነው። አምልኮአችን እውነተኛ ከሆነ፣ የእኛ አባል ባይሆኑም በክርስቲያኖች አንድነት ውስጥ ሆነው ኢየሱስን ከሚከተሉት ጋር በፍቅር ማደግ እንችላለን። 

ባልንጀሮቻችንን መውደድ ቀላል እንዳልሆነ እንገነዘባለን። ምክንያቱም ጥፋቶቻቸው እና ጉድለቶቻቸው ያለፉ ቁስሎችን ስለሚያስታውሱን ነው። በዚህን ጊዜ እውነተኛው የወይን ግንድ፣ የአባታችን እግዚአብሔር እገዛ ከእኛ ጋር ይሆናል (ዮሐ. 15፡1)። ምን ማድረግ እንዳለበት እርሱ ያውቃል። በእኔ ላይ ያለውን የማያፈራ ቅርንጫፍ ሁሉ አባቴ ቆርጦ ይጥለዋል፤ የሚያፈራውን ቅርንጫፍ አብዝቶ እንዲያፈራ ገርዞ ያጠራዋል (ዮሐ. 15፡2)። እግዚአብሔር ቅርንጫፎችን ቆርጦ የሚከረክመው ሌሎችን እንዳንወድ የሚያደርገንን፣ ወደ ተሳሳተ መንገድ የሚወስደንን ፍሬ እንዳናፈራ እና በራሳችን ብቻ ተወስነን እንዳንቀር ስለሚፈልግ ነው። ስለዚህ በሌሎች ሰዎች ላይ ያለንን ጭፍን የጥላቻ መንፈስን፣ ከሌሎች ጋር አንድነት እንዳይኖር የሚያደርጉ ዓለማዊ አስተሳሰቦችን እግዚአብሔር ከእኛ ልብ እንዲያርቅልን እንለምነዋለን። በዚህ መንገድ በእግዚአብሔር ፍቅር  ታጥበን ከጸዳን ፣ በዘመናችን ከወንጌል የሚያዘናጉንን ምድራዊ መሰናክሎችን እና እንቅፋቶችን ማሸነፍ እንችላለን።

ሦስተኛው ደረጃ ሰፊው እና መላውን ሰብዓዊ አንድነት የሚመለከት ነው። ይህን በተመለከተ የመንፈስ ቅዱስን ሚና ማስታወስ እንችላለን። የወይኑ ግንድ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ እርሱ ሁሉንም የቅርንጫፍ ክፍሎችን ሊደርስ ይችላል። መንፈስ ቅዱስ በሚፈልገው አቅጣጫ ወደ አንድነት ጎዳና ይመራናል። የሚወዱንን እና የምናውቃቸውን ብቻ መውደድ ሳይሆን፣ ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳስተማረን፣ ሁሉንም መውደድ እንድንችል መንፈስ ቅዱስ ያግዘናል፤ ጠላቶቻችን ያደረሱብንን በደል ይቅር እንድንል ያስችለናል፤ በፍቅር እንድናድግ ይገፋፋናል።  ወዳጆቻችንን፣ መንፈሳዊ እሴቶቻችንን እና ሀሳቦቻችንን የሚጋሩትን ብቻ ሳይሆኑ በስቃይ ሕይወት ውስጥ የሚገኙ ድሆችን እና እግዚአብሔር ለሚራራላቸው ሁሉ የደግነት ተግባራትን ለማከናወን እንደተጠራን መንፈስ ቅዱስ ያሳስበናል። የጸጋዎች ሁሉ ባለቤት የሆነው መንፈስ ቅዱስ፣ የሚጠሉንን ጭምር እንድንወድ ይርዳን። ምክንያቱም ቅዱስ ወንጌል ፍሬን የሚያፈራው በንጹህ ፍቅር ከራስ ወዳድነት ነጻ ስንሆን ነው። ዛፍ በፍሬው ይታወቃል፤ የወይኑ ግንድ ከሆነው ከኢየሱስ ጋር መሆናችን የሚታወቀው ፍቅርን በነጻ ስንገልጽ ነው።

ተጨባጭ ፍቅርን ከወንድሞቻችን እና ከእህቶቻችን ጋር፣ ኢየሱስ ክርስቶስ አንድነትን ካጸናው መላው ሰብዓው ፍጥረት ጋር እንድንለዋወጥ መንፈስ ቅዱስ ያስተምረናል (ማቴ. 25:31-45)። ፍቅርን እርስ በእርስ በመለዋወጥ፣ ወንድማማቾች መሆናችንን ከማወቅ በላይ በኅብረት የምናድግ መሆናችንን እናውቃለን። መንፈስ ቅዱስ ምድራችንን ወደ መልካም ገጽታ በመለወጥ፣ ለጋራ መኖሪያ ቤታችን ጥንቃቄን እና እንክብካቤን እንድናደርግ፣ የጋራ ቤታችንን እንድንንከባከብ፣ ውድ የሆኑ የተፈጥሮ ጸጋዎች በከንቱ እንዳይባክኑ፣ በማኅበራዊ ሕይወት ውስጥ ቆራጥ እና ትክክለኛ ውሳኔዎችን እንድናደርግ ያሳስበናል።

መንፈስ ቅዱስ የክርስቲያኖችን ውህደት የሚያጠናክሩ መንገዶችን በማሳየት በዛሬው ዕለት በኅብረት እንድንጸልይ አስችሎናል። በኅብረት ካካበትነው ልምድ በሚመነጭ የጋራ ድምጽ ወደ እግዚአብሔር ዘንድ ጸሎታችንን እያቀረብን፣ በዚህ ሳምንት ውስጥ በጋራ ለክርስቲያኖች አንድነት ጸሎታቸውን ያቀረቡትን እና ወደፊትም ጸሎታቸውን ሳያቁርጡ ለሚያቀርቡት በሙሉ ምስጋናዬን አቀርብላቸዋለሁ። ከልዩ ልዩ አብያተ ክርስቲያናት የመጡትን እና ከክርስቲያናዊ ማኅበረሰብ የተወከሉ፣ ከኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ለመጡት ወጣቶች፣ በቅድስት መንበር የክርስቲያኖች አንድነት ማጠናከሪያ ጳጳሳዊ ምክር ቤት በሚሰጠው ነጻ የትምህርት ዕድል፣ ሮም በሚገኝ ጳጳሳዊ ዩኒቨርስቲዎች ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ለሚገኙት የምሥራቅ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ተማሪዎች፣ መምህራን እና ዘንድሮ ወደ ሮም መምጣት ሳይችሉ ቀርተው በማኅበራዊ ሚዲያ በኩል የጸሎት ሥነ-ሥርዓቱን ሲከታተሉ ለቆዩት የቦሴይ ክርስቲያኖች አንድነት ተቋም ተማሪዎች በሙሉ ወንድማዊ ሰላምታዬን አቀርብላቸዋለሁ። ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ! እኛ ሁላችን የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን በልባችን እንድናውቅ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አንድ ሆነን በአንድ ቤተሰብ ውስጥ እንደ ወንድማማቾች እና እህትማማቾች መኖር እንድንችል መንፈስ ቅዱስ ይርዳን። ቅድስት ሥላሴ በመካከላችን ፍቅራዊ ኅብረትን በመጨመር አንድነታችንን ያሳድግልን።"

25 January 2021, 18:50