ፈልግ

አዲስ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ባይደን አዲስ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ባይደን  

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ ፕሬዚዳንት ባይደን በአሜሪካ እና በአለም ሰላም እና እርቅን እንዲያሰፍኑ ጥሪ አቀረቡ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለአዲሱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ቢይደን የእንኳን ደስ አሎት መልእክት ማስተላለፋቸው የተገለጸ ሲሆን ቅዱስነታቸው በእዚህ መልእክታቸው አዲሱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ለአሜሪካ እና ለመላው ዓለም ሰላምና እርቅ እንዲያመጡ ጥሪ ማቅረባቸው ተገልጿል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆሴፍ ባይደን የላኩት የእንኳን አደረስዎ መልዕክታቸውን የጀመሩት “በአሜሪካን አርባ ስድስተኛ ፕሬዝዳንት ሆነው በይፋ ሥራዎን በተረከቡበት በእዚህ ወቅት ሁሉን ቻይ የሆነው እግዚአብሔር ጥበብን እንዲሰጥዎ መልካም ምኞቴን እየገለጽኩኝ፣ በሥራዎ ሂደት ውስጥ እግዚአብሔር ጥንካሬን እንዲሰጥዎ በጸሎቴ ከእርሶ ጋር እንደ ምሆን አረጋግጣለሁ” በማለት እንደ ነበረ ተገልጿል።

በጥር 12/2013 ዓ.ም ረቡዕ ዕለት እኩለ ቀን አካባቢ ዲሞክራቶቹ ጆሴፍ አር ባይደን እና ካማላ ሃሪስ ቃለ መሃላ በመፈፀም በቅደም ተከተል 46 ኛ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት እና ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው ቃለ መሃላ ፈጽመዋል። ፕሬዚዳንት ባይደን ወደ ስልጣን የመጡት በአሜሪካ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በአገሪቷ ሕዝቦች መካከል ከፍተኛ መከፋፈል በተከሰተበት ወቅት ነው። ልክ ከሁለት ሳምንታት በፊት እ.ኤ.አ. ጥር 6 ቀን የአሜሪካ ኮንግረስ የፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ውጤቶችን ሲያረጋግጥ ፣ የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ደጋፊዎች በዋሽንግተን ዲሲ በሚገኘው ካፒቶል ሂል ህንፃ በመግባት ሕንፃውን ለብዙ ሰዓታት ተቆጣጥረው ነበር። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እ.ኤ.አ በጥር 10 እሁድ እለት የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ከደገሙ በኋላ በወቅቱ ባስተላለፉት መልእክት ላይ ይህን የኃይል እርምጃ ማውገዛቸው ይታወሳል።

በካፒቶል ሂል ላይ በደረሰው ጥቃት አምስት ሰዎችን ለህልፈተ ሞት የዳረገ ምክንያት በሆነው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዶናልድ ትራምፕን ‘አመፅ በማስነሳት ክስ ተመስርቶባቸው” እንደ ነበረ ይታወሳል። ምንም እንኳን ከእንግዲህ ፕሬዝዳንት ባይሆኑም በክሱ ላይ የሴኔትን ችሎት የማቅረብ እድል ሰፊ እንደ ሆነ የተገለጸ ሲሆን ይህ ክስ ከተሳካ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከእንግዲህ ወዲህ በፕሬዚዳንታዊ ምርጫዎች ላይ እንዳይሳተፉ ሊያደርጋቸው እንደ ሚችል ተገልጿል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ ረቡዕ ዕለት ለፕሬዝዳንት ጆሴፍ ባይደን ባስተላለፉት መልእክት “በእርስዎ መሪነት የአሜሪካ ህዝብ ሀገሪቱን ከመመስረት ጀምሮ ካነሳሷቸው ከፍ ካሉ የፖለቲካ ፣ የስነምግባር እና የሃይማኖት እሴቶች መካከል የአሜሪካን ህዝብ ጥንካሬውን ማስቀጠል ይችላሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ” ብለዋል። አሜሪካ ከተመሠረተችበት እ.አ.አ 1776 ዓ.ም ጀምሮ የ 244 ዓመት ያስቆጠረ ዲሞክራሲ እያጣጣመች እንደ ሆነ ይታወቃል።

አሜሪካ በዓለም ዙሪያ ካሉት በኮሮና ቫይረስ ቀውሶች ከተመቱ አገራት መካከል ዋነኛዋ ስትሆን አዲስ የተመረጡት ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ይህንን ትልቅ የሆነ ቀውስ ለመፍታት ከፍተኛ የሆነ ጥረት ማደረግ እንደ ሚጠበቅባቸው ግልጽ ነው። አሜሪካውያን ይህንን አዲስ የተመረጡት ፕሬዚዳንት ስልጣናቸውን በይፋ ሲረከቡ የሚያሳየውን ዝግጅት በመገናኛ አውታሮች አማካይነት በቀጥታ እንደ ተከታተሉት የተገለጸ ሲሆን በዚህ ወረርሽኝ ወቅት ለሞቱ ሰዎች መታሰቢያ ያካተተ ዝግጅተ መከናወኑም ተገልጿል፣ ለችግረኞች ፍቅር እና ጽናት ላሳዩ ሰዎች እና ድርጅቶች እውቅና እንደተሰጠም ተገልጿል።

እስካሁን ድረስ በአሜሪካ ውስጥ ከኮቪድ -19 ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት 402 ሺህ ሰዎች ሞተዋል - ከ 24 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በቫይረሱ ተይዘው እንደ ሚገኙ የሚወጡ ሪፖርቶች ይፋ አድርገዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “በሰው ልጆች ቤተሰብ ፊት ለፊት የሚታየው ይህ ከፍተኛ ቀውስ አርቆ አሳቢ እና የተባበሩ ምላሾችን በሚጠይቅበት በዚህ ወቅት ፣ ውሳኔዎቻችሁ በእውነተኛ ፍትህ እና ነፃነት የተጎናፀፈ ህብረተሰብን ለመገንባት በሚያስብ ሁኔታ እንዲመሩ እፀልያለሁ ፣ ከማይገረሰሰው የእያንዳንዱ ሰው መብትና ክብር ፣ በተለይም ድሆች ፣ አቅመ ደካሞች እና ድምፅአቸውን ከፍ አድርገው ማሰማት ካልቻሉ ሰዎች ጋር ተባብረው እንዲሰሩ” ጥሪ ማቅረባቸው ተገልጿል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መልእክታቸውን ሲያጠናቅቁ “እኔም በተመሳሳይ በአለም አቀፍ እና በአለም ሀገሮች መካከል መግባባት ፣ እርቅ እና ሰላም እንዲሰፍን ጥረታችሁን እንዲመራው የጥበብ እና የእውነት ሁሉ ምንጭ የሆነውን እግዚአብሔርን እጠይቃለሁ።  በእዚህ መንፈስ በእርስዎ፣ በቤተሰብዎ እና በተወዳጁ የአሜሪካ ህዝብ የተትረፈረፈ በረከቶችን ያገኙ ዘንድ እግዚአብሔርን እለምናለሁ” ካሉ በኋላ ቅዱስነታቸው መልእክታቸውን አጠናቀዋል።

21 January 2021, 12:44