ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በቫቲካን ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በቫቲካን  

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ እ.ኤ.አ. 2021 ዓ.ም ለሁሉም የወንድማማችነት እና የሰላም አመት እንዲሆን እመኛለሁ አሉ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እ.ኤ.አ. በጥር 1/2021 ዓ.ም  ለሚከበረው 54 ኛው የዓለም የሰላም ቀን ባስተላለፉት መልእክት በዓለም ላይ ሰላም የማስጠበቅ ባህልን ለማዳበር የቤተክርስቲያኗን ማህበራዊ አስተምህሮ እንደ “አቅጣጫ መጠቆሚያ መሳርያ” ሆኖ ሊያገለግል እንደ ሚችል የገለጹ ሲሆን በተጨማሪም “የመንከባከብ ባሕል” እንዲጎለበት መሥራት ያስፈልጋል ማለታቸው ተገልጿል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለካቶሊክ ቤተክርስቲያን የዓለም የሰላም ቀን ባስተላለፉት መልእክት በግለሰቦች፣ በማኅበረሰቦች ፣ በሕዝቦችና በብሔሮች መካከል “የወንድማማችነት ፣ የፍትህ እና የሰላም መንገድ” ላይ በመራመድ ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ እና እያንዳንዱ ግለሰብ “የእንክብካቤ ባህል” እንዲያዳብሩ ጥሪ አቅርበዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት “እንክብካቤ የማድረግ ባህል ከሌለ ሰላም ሊኖር አይችልም” ሲሉ በጥር 1/2021 ዓ.ም ለሚከበረው 54 ኛው የዓለም የሰላም ቀን ከቫቲካን ባስተላለፉት መልእክት አስገንዝበዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በመልእክታቸው “የሁሉንም ክብርና በጎነትን ለመጠበቅና ለማጎልበት ፣ እንክብካቤን እና ርህራሄን ለማሳየት ፈቃደኛ ለመሆን ፣ ለእርቅና ለሰላም ለመስራት እና እርስ በእርስ መከባበርን እና ተቀባይነትን ለማስፈን የጋራ ፣ ደጋፊ እና ሁሉን አቀፍ ቁርጠኝነት” እንዲኖር ጥሪ አቅርበዋል፣ በተጨማሪም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የቤተክርስቲያን ማህበራዊ አስተምህሮ መርሆዎች በሰላም መንገድ ላይ እንደ አቅጣጫ መጠቆሚያ መሳሪያ መጠቀም እንደ ሚቻል አክለው ገልጸዋል።

እ.ኤ.አ. በ 1967 ዓ.ም በወቅቱ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳስ በነበሩት ቅዱስ ጳውሎስ ስድስተኛ አማካይነት የተጀመረው የመጀመሪያው የዓለም የሰላም ቀን እ.ኤ.አ. በጥር 1/ 1968 ዓ.ም በይፋ መጀመሩ ይታወሳል፣ በተመሳሳይ ቀንም የጎርጎሮርሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ በጥር 1 ቤተክርስቲያን እንዲሁ የእግዚአብሔር እናት የሆነችውን የማርያምን ታላቅ በዓል እንደ ምታከብር ይታወቃል።

ለሀገራት እና ለመንግስት መሪዎች ፣ ለዓለም አቀፍ ድርጅቶች መሪዎች ፣ ለሐይማኖት መሪዎች እና ለተለያዩ ሃይማኖት ተከታዮች እንዲሁም መልካም ፈቃድ ላላቸው ወንዶችና ሴቶች የተላከው “የእንክብካቤ ባህል የሰላም መንገድ ነው” በሚል መሪ ቃል ቅዱስነታቸው መልእክት ማስተላለፋቸው ተገልጿል።

ከወረርሽኙ ትምህርት መውሰድ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “ግዙፍ የኮቪድ -19 የጤና ቀውስ” እንደ የአየር ንብረት ፣ የምግብ ፣ የምጣኔ ሀብት እና የስደት ያሉ በጥልቀት እርስ በርሳቸው የተዛመዱ ቀውሶችን እንዴት እንዳባባሱ ለብዙዎች ታላቅ ሀዘን እና ስቃይ መንስኤ እንደ ሆኑ በመልእክታቸው አክለው ገልጸዋል። ለኮቭድ -19 ክትባት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ እና ለታመሙ ፣ ለድሆች እና ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ ሰዎችን ለመንከባከብ የሚያስፈልጉ አስፈላጊ ቴክኖሎጅዎች ተደራሽ እንዲያደርጉ በእዚህ ረገድ የፖለቲካ አመራሮች እና የግሉ ዘርፍ ጥረት እንዲያደርጉ ለመጠየቅ አጋጣሚውን ተጠቅመዋል።

ከወረርሽኙ ጎን ለጎን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በተለያዩ የብሔረተኝነት ዓይነቶች ፣ በዘረኝነት እና ከመጠን በላይ የሆነ ጥላቻ እንዲሁም ሞትን እና ጥፋትን ብቻ የሚያመጡ ጦርነቶች እና ግጭቶች መኖራቸውን ልብ ሊባል እንደ ሚገባ የገለጹ ሲሆን እነዚህ እና ሌሎች ተመሳሳይ ችግሮች እርስ በርሳችን መተሳሰብ እና የበለጠ በወንድማማችነት መንፈስ የተሞላ ህብረተሰብ ለመገንባት በምናደርገው ጥረት አከባቢያችን እና መልካ ምድራችንን መንከባከብ አስፈላጊነት አጉልተው ገልጸዋል። ስለሆነም “የእንክብካቤ ባህል የሰላም መንገድ ነው” በዘመናችን የተንሰራፋውን ግድየለሽነት ፣ ብክነት እና የግጭት ባህልን ለመዋጋት መንገድ ነው ብለዋል።

የቤተክርስቲያኗ እንክብካቤ ባህል ዝግመተ ለውጥ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ከመጀመሪያው የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ እስከ ኢየሱስ ድረስ የቤተክርስቲያኗ የእንክብካቤ ባህል ዝግመተ ለውጥን ከመጀመሪያዋ ቤተክርስቲያን አንስቶ እስከ ዘመናችን ድረስ ያለውን ወቅት እንደ ሚያካትት በመልእክታቸው ገልጸዋል።

ዓለም ከተፈጠረ በኋላ እግዚአብሔር “እንዲንከባከበው እና ​​እንዲጠብቀው” ለአዳም ዓለምን አደራ ሰጠው። ቃየን ለእግዚአብሔር “እኔ የወንድሜ ጠባቂ ነኝ?” በማለት በሰጠው ምላሽ ወንድሙን አቤልን ከገደለ በኋላ ሁላችንም አንዳችን ለሌላው ጠባቂዎች መሆናችንን ለማስታወስ የተሰጠ ምላሽ ነው። እግዚአብሔርን ለቃየል የሚያደርገው ጥበቃ ምንም እንኳን ጥፋት ቢኖርም በእግዚአብሔር አምሳል እና መልክ የተፈጠረውን ሰው የማይነካውን ክብር ያረጋግጣል። በኋላም እለተ ሰንበትን የተለየ ቀን አድርጎ በመውሰድ ለድሆች ማህበራዊ ስርዓትን እና አሳቢነት ወደ ነበረበት ለመመለስ ያተኮረ ሲሆን ከእዚያም በመቀጠል ለምድር ፣ ለባሪያ እና ባለዕዳ ለሆኑ ሰዎች እረፍ ለመስጠት የመሰረተው እለት ነው ሲሉ ገልጸዋል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ መልእክታቸውን ሲቀጥሉ ይህ ሁሉ የሚያሳየው “ሁሉም ነገር እርስ በእርሱ የተገናኘ መሆኑን እና ለራሳችን ሕይወት እና ከተፈጥሮ ጋር ያለን ግንኙነት እውነተኛ እንክብካቤ ማድረግ ከወንድማማችነት ፣ ከፍትህ እና ለሌሎች ታማኝነት የማይለይ መሆኑን ያሳያል” ብለዋል።

አብ ለሰው ልጆች ያለው ፍቅር አሉ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በመልእክታቸው ደቀ መዛሙርቱ እንዲሁ እንዲያደርጉ በሚጠይቀው በኢየሱስ ውስጥ ከፍተኛውን መገለጥ ያገኛል ያሉ ሲሆን የጥንት ክርስቲያኖች ኢየሱስ ባስተማራቸው መልኩ የነበራቸውን ያካፈሉ እና የተቸገሩትን በመንከባከብ ቤታቸውን ለሁሉም ሰዎች ክፍት ያደርጉ እንደነበረ ቅዱስነታቸው አክለው ገልጸዋል።

ዛሬ ቤተክርስቲያኗ “ለእያንዳንዱ ሰብዓዊ ፍላጎት እፎይታ የሚሰጡ ብዙ ተቋማት አሏት - ሆስፒታሎች ፣ የድሆች መንከባከቢያ ጣቢያዎች፣ ወላጅ አልባ ሕፃናት የሚጠለሉበት ስፍራዎች፣ የስደተኛ መጠሊያ ጣቢያዎች የመሳሰሉ ተቋማት ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን በተቻላት አቅም በመርዳት ላይ እንደ ምትገኝ ገልጸዋል።

የቤተክርስቲያኗ ማህበራዊ አስተምህሮ የእንክብካቤ “ሰዋሰው”

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ መልእክታቸውን ሲቀጥሉ በአባቶች ነፀብራቅ እና በእምነት ላይ በሚገኙ ምስክሮች በበጎ አድራጎት የበለፀገው ይህ የቤተክርስቲያን እንክብካቤ የማድረግ ባህል “የቤተክርስቲያኗ ማህበራዊ አስተምህሮ ልብ” ውስጥ የሚገኝ እንደ ሆነ የገለጹ ሲሆን እርሳቸው እንዳሉት ይህ እንክብካቤ የማድረግ ባሕል “ሰዋሰው” ሆኖ ሊያገለግል ይችላል ያሉ ሲሆን እያንዳንዱን ሰው ክብር ከፍ ለማድረግ በቁርጠኝነት በመሥራት ለድሆች እና ለአደጋ ተጋላጭዎች ቅርብ በመሆን የጋራ ጥቅምን ማስጠበቅ እና ለምድራችን ጥበቃ ማድረግ አስፈላጊ እንደ ሆነ አክለው ገልጸዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ እንደሚሉት  ክርስቲያናዊ ፅንሰ-ሀሳብ ሰባዊነትን በተመለከተ ሲገልጽ የተሟላ እና የተቀናጀ  የሰው ሐብት ልማት እውን ማድረግን እንደ ሚያበረታታ የገለጹ ሲሆን “ሰው ሁል ጊዜ የሚያመለከተው ግለሰባዊነትን ብቻ ሳይሆን ዝምድናን ጭምር ነው፣ ይህም ማግለልን ሳይሆን አቃፊ መሆንን ያረጋግጣል፣ ልዩ እና የማይገረሰስ የሰው ልጅ መብት ማስከበር ማለት ነው እንጂ ሰውን መበዝበዝ ማለት አይደለም ብለዋል። “እያንዳንዱ ሰብዓዊ ፍጡር በራሱ ወይም በራሱ ጥቅም ውስጥ ገብቶ መኖር አይችልም፣ ለእሱ ወይም ለእርሷ ጠቅም ብቻ የሚውል መሣሪያ አይደለም” ብለዋል።

በቤተክርስቲያኗ ማህበራዊ መርሆዎች “እንደ አቅጣጫ መጠቆሚያ መሳርያ በመጠቀም” በእዚህ መሠረት እያንዳንዱ ማህበራዊ ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሕይወት ለጋራ ጥቅም አገልግሎት ሲሰጥ ሙሉ ፍፃሜውን ያገኛል ፣ ይህም ሰዎች ፍፃሜያቸውን በበለጠ እና በቀላሉ እንዲያገኙ ያስችላቸዋል ብለዋል።

በዚህ ረገድ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ እንደሚሉት ኮቪድ -19 በተባለው ወረርሽኝ ሁላችንም ተሰባሪ እና ግራ የተጋባን በአንድ ጀልባ ውስጥ ሆነን እንደ ምንቀዝፍ እንድንረዳ አድርጎናል ያሉ ሲሆን ሁላችንም አንድ ላይ እንድንሰለፍ ተጠርተናል ማንም ሰው በራሱ ጥረት ብቻ መዳን እንደ ማይችል ተረጋግጧል ብለዋል።

የቤተክርስቲያኗ ማህበራዊ መርሆች እንዲሁ ሁላችንም በእውነት ለሁሉም ተጠያቂ ስለሆንን ለሌሎች ተጨባጭ የሆነ ህብረት እንድናሳይ እንደ ሚያሳስቡ የገለጹት ቅዱስነታቸው እርሳቸው ይፋ ባደረጉት በላቲን ቋንቋ  ላውዳቶ ሲ “ውዳሴ ለአንተ ይሁን” በተሰኘው ጳጳሳዊ መልእክት ውስጥ እንደ ሰፈረው ደግሞ የፍጥረታትን ሁሉ እርስ በርስ መገናኘት ያጎላል።

ይህ የተቸገሩ የወንድሞቻችንና የእህቶቻችንን ጩኸት እና የምድርን ጩኸት የጋራ ጩኸት መሆኑን በመገንዘብ ለእነሱ እንክብካቤ ማደረግ አስፈላጊ መሆኑን ያሳያል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳቱ በላቲን ቋንቋ ላውዳቶ ሲ “ውዳሴ ለአንተ ይሁን” ጳጳሳዊ መልእክት በመጥቀስ “ልባችን ለሰው ልጆች ርህራሄ ፣ ፍቅር እና አሳቢነት ከሌለው ከተቀረው ተፈጥሮ ጋር ጥልቅ የሆነ የመተባበር ስሜት እውነተኛ ሊሆን አይችልም” ብለዋል። "ሰላም ፣ ፍትህ እና ለፍጥረታት እንክብካቤ ማደረግ በተፈጥሮ የተያያዙ ሦስት ጥያቄዎች ናቸው ፣ ሊነጣጠሉ የማይችሉ ናቸው" ብለዋል።

የቤተክርስቲያን ማህበራዊ አስተምህሮ “አቅጣጫ መጠቆሚያ መሳርያ” ነው

የማባከን ባህላችን በተመለከተ በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጪ መካከል ያለው ልዩነት እየሰፋ በመምጣቱ አሉ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የመንግስት መሪዎችን እና የዓለም አቀፍ ድርጅቶችን ፣ የንግድ መሪዎችን ፣ የሳይንስ ሊቃውንት ፣ አስተባባሪዎችን እና አስተማሪዎችን የቤተክርስቲያኗ ማህበራዊ መርሆዎች እንዲረከቡ አሳስበዋል። የቤተክርስቲያን ማህበራዊ አስተምህሮ “አቅጣጫ መጠቆሚያ መሳርያ” ነው በዓለም አቀፋዊ ሉላዊነት (ግሎባላይዜሽን) ሂደት ውስጥ አንድ የጋራ አቅጣጫን በመጠቆምና “መጻይ ጊዜን የበለጠ ሰብዓዊ ለማደረግ” ችሎታ አለው ብለዋል። በተጨማሪም ይህንን የቤተክርስቲያን ማህበራዊ አስተምህሮ እንደ “አቅጣጫ መጠቆሚያ መሳርያ” አድርጎ በመጠቀም እና በእጅ በመያዝ ብዙ ነባር ማህበራዊ ልዩነቶችን ለማስወገድ ጥረት እንዲያደርግ ጥሪ ያቀርባል።

ሰብአዊ የሆኑ ሕጎች በተለይም በልጆች፣ በወንድ እና በሴቶች ላይ ከፍተኛ ሥቃይ የሚያስከትሉ ግጭቶችና ጦርነቶች ባሉበት ሁኔታ መከበር አለበት፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ መልእክታቸውን ሲቀጥሉ ግጭቶች እንደ አንድ ነገር ከመቆጠር ይልቅ በእውነተኛ ሰላም በአብሮነት እና በወንድማማችነት ለመስራት ልባችንን እና የአስተሳሰባችንን መንገድ መለወጥ አለብን ብለዋል።

የጦር መሳሪያዎች እና ሰላም

ከዚህ አንፃር ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ሲናገሩ በመሳሪያ ላይ በተለይም የኑክሌር የጦር መሳሪያዎች አስፈላጊ እንዳልሆኑ የገለጹ ሲሆን አስፈላጊ ለሆኑ ለግለሰቦች ደህንነት ፣ ለሰላም እና ለሁለንተናዊ የሰው ሐብት ልማት እድገት ፣ ድህነትን ለማስወገድ እና ለጤና እንክብካቤ አቅርቦት ቅድሚያ እንዲሰጡ ጥሪ አቅርበዋል። ረሃብን በቋሚነት ለማስወገድ እና ለድሃ አገራት እድገት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማድረግ “ለጦር መሣሪያ እና ለሌሎች ወታደራዊ ወጭዎች በሚውለው ገንዘብ‘ ፈንታ ‘ግሎባል ፈንድ’ ማቋቋም ድፍረት የተሞላበት ውሳኔ ነው” ብለዋል።

ስለሰላም ማስተማር

የእንክብካቤ ባህልን ለማሳደግ የሚረዱ የትምህርት ሂደቶች አፈላጊ እንደ ሆኑ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በመልእክታቸው የገለጹ ሲሆን ይህ የሚጀምረው በቤተሰብ ውስጥ እንዴት መኖር እንደምንችል በምንማርበት እና በጋራ በመከባበር መንፈስ ከሌሎች ጋር እንዴት መዛመድ እንደ ምንችል በመገንዘብ ነው ብለዋል። ትምህርት ቤቶች እና ዩኒቨርስቲዎች ፣ የኮሙኒኬሽን ሚዲያዎች እንዲሁም ሃይማኖቶችና የሃይማኖት መሪዎች የእያንዳንዱን ሰው ፣ የቋንቋ ፣ የጎሳ እና የሃይማኖት ማህበረሰብ እና የእያንዳንዱን ሰው ክብር በማስጠበቅ ላይ የተመሠረተ እሴቶችን እንዲያስተላልፉ ጥሪ ቀርበዋል።

“አሁን ባለው የቀውስ አውሎ ነፋስ በሰፈነበት በእንደዚህ ዓይነት ጊዜ ፣ ​​ወደ ተረጋጋና ጸጥ ወዳለ አድማስ ለመሄድ የሰው ልጅ በሚታገልበት በአሁኑ ወቅት የሰው ልጆችን ክብር ለማስከበር ይችላ ዘንድ የቤተክርስቲያኗ መሠረታዊ ማህበራዊ መርሆዎች አንድ ላይ በመሆን በትክክለኛው ጎዳና ላይ እንድንራመድ ሊያግዙን ይችላሉ ብለዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መልእክታቸውን ሲያጠናቅቁ “ሌሎችን በተለይም በችግር ላይ ያሉትን ሰዎች በፍጹም ችላ ማለት አይገባንም” ያሉ ሲሆን “ይልቁንም እርስ በእርሳችን የምንቀባበል እና የሚተቃቀፍ  ወንድሞች እና እህቶች የተዋቀረ ማህበረሰብ ለመመስረት በየቀኑ በተጨባጭ እና በተግባራዊ መንገዶች መትጋት ይኖርብናል” ብለዋል።

በቤተክርስቲያኗ ማህበራዊ መርሆዎች “እንድ አቅጣጫ መጠቆሚያ መሳሪያ በመጠቀም” በእዚህ መሠረት እያንዳንዱ ማህበራዊ ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሕይወት ለጋራ ጥቅም አገልግሎት ሲሰጥ ሙሉ ፍፃሜውን ያገኛል ፣ ይህም ሰዎች ፍፃሜያቸውን በበለጠ እና በቀላሉ እንዲያገኙ ያስችላቸዋል ብለዋል።

01 January 2021, 19:47