ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስቾስ በባንግላደሽ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ወቅት ሕሙማንን ሲጎበኙ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስቾስ በባንግላደሽ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ወቅት ሕሙማንን ሲጎበኙ 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ መዋዕለ ንዋይን ለሕክምና ድጋፍ ጭምር ማዋል እንደሚያስፈልግ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ዘንድሮ ለ29ኛ ጊዜ የተከበረውን ዓለም ዓቀፍ የሕሙማን ቀን ምክንያት በማድረግ መልዕክት ማስተላለፋቸው ታውቋል። ቅዱስነታቸው በዚህ መልዕክታቸው “መዋዕለ ንዋይን ለሕሙማን ሕክምና ድጋፍ ማፍሰስ፣ የጤና አግልግሎትን ለሁሉ ማዳረስ ከሚለው መሠረታዊ መርህ ጋር የተቆራኘ እና የጋራ ጥቅምን የሚመለከት ጉዳይ ነው” ካሉ በኋላ፣ ሕመም በበሽታ የሚሰቃዩ ሰዎች ዋና ምልክት ቢሆንም በማኅበረሰቡ መካከል የተረሱትን፣ የተገለሉትን፣ ፍትህ የጎደላቸው እና መሰረታዊ መብቶቻቸውን የተነፈጉትንም እንደሚያካትት አስረድተዋል። በማቴ. ወንጌል ምዕ. 23:8 “እናንተ ግን መምህራችሁ አንድ ብቻ ስለሆነና ሁላችሁም ወንድማማቾች ስለሆናችሁ” የሚለውን በመጥቀስ፣ የተቸገሩትን መርዳት፣ የኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር ምሳሌ፣ በኃጢአት ለቆሰሉት ሰዎች በሙሉ ርኅራሔ የሚገለጽበት የመልካም ሳምራዊ ተግባር ነው” ብለዋል።

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ፣ ዘንድሮ ለ29ኛ ጊዜ የተከበረውን ዓለም አቀፍ የሕሙማን ቀን በማስመልከት ያስተላለፉት መልዕክት ትርጉም ሙሉ ይዘት እንደሚከተለው ይቀርባል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

"የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ!

ዘንድሮ ጥር 3/2013 ዓ. ም ለ29ኛ ጊዜ የተከበረው ዓለም አቀፍ የሕሙማን ቀን፣ ወደ ሉርድ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጸሎት በምናቀርበት ዕለት የሚከበር በመሆኑ፣ በዚህ ዕለት ለሕሙማን ልዩ ትኩረትን ሰጥተን የምናስታውስበት፣ የሕክምና አገልግሎትን በመስጠት ላይ የሚገኙ የጤና ባለሞያዎችን፣ ዕርዳታን በመስጠት የሚንከባከቧቸውን ቤተሰቦች እና መላውን ማኅበረሰብ በጸሎት የምናስታስውስበት ዕለት ነው። በተለይም ደግሞ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ስቃይ የደረሰባቸውን እና በስቃይ ውስጥ የሚገኙትን በጸሎት የምናስታውስበት ዕለት ነው። ድሆችን እና ከኅብረትሰቡ መካከል ከተገለሉት ጋር ያለኝን አንድነት እና ቤተክርስቲያንም የምትሰጠውን ልባዊ ፍቅር ማረጋገጥ እፈልጋለሁ።

ይህንን ዝግጅት ከእዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ!

1.       ዘንድሮ የሚከበረው ዓለም አቀፍ የሕሙማን ቀን መሪ ሐሳብ፣ በማቴ. 23:1-12 ላይ እንደተጠቀሰው፣ የሚሰብኩትን በተግባር መግለጽ የተሳናቸውን ሰዎች ግብዝነት ኢየሱስ ክርስቶስ ተመልክቶ እንደነቀፋቸው የሚገልጽ ነው። እምነታችን በባዶ ቃላት የተሞላ ከሆነ፣ ለሌሎች ሕይወት የማንጨነቅ፣ የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ ለማቅረብ የማንጥር ከሆነ፣ በቃል የምንመሰክረው የሃይማኖት መግለጫ ከምንመራበት ሕይወት ጋር የማይጣጣም መሆኑን ያረጋግጣል። ይህ በሚሆንበት ጊዜ የሚያጋጥመን አደጋ ከፍተኛ ነው። ኢየሱስም ወደ ጣዖት አምልኮ የመውደቅ አደጋን አስመልክቶ ጠንከር ባሉ ቃላት የተናገረው ለዚህ ነው፥ “እናንተ ግን መምህራችሁ አንድ ብቻ ስለሆነና ሁላችሁም ወንድማማቾች ስለሆናችሁ” (ማቴ. 23:8) በማለት ይናገረናል።

“የሚሰብኩትን በተግባር መግለጽ ለተሳናቸው ግብዞች” (ማቴ. 23:3) ኢየሱስ ክርስቶስ ያቀረበው ትችት፣ የአንድ አባት ልጆች እና ወንድማማቾች እንዳንሆን በሚያደርገን በግብዝነት ኃጢአት ውስጥ እንዳንወድቅ ሁል ጊዜ እና በሁሉም ሥፍራ የሚያግዘን የምክር ቃል ነው።

ለወንድሞቻችን እና እህቶቻችን የሚያስፈልጋቸውን ዕርዳታ ከማቅረባችን በፊት ከግብዝነት ሕይወት ነጻ እንድንሆን ኢየሱስ ክርስቶስ ይጠይቀናል። በተረጋጋ መንፈስ ማድመጥ እንድንችል፣ ከሰዎች ሁሉ ጋር መልካም ግንኙነት እንዲኖረን እና ስቃያቸውን በመካፈል በርህራሄ ልብ እንድንመለከታቸው ያስፈልጋል።

ለሕመም በምንጋለጥበት ጊዜ አቅመ ደካሞች መሆናችንን እና የሌሎች ሴዎች እገዛ ይበልጥ እንደሚያስፈልገን እንገነዘባለን። ይህም በእግዚአብሔር የምንመካ መሆናችንን እንድናውቅ ያደርገናል። በሕመም በምንወድቅበት ጊዜ በፍርሃት ልባችን ይጨነቃል፤ ጤናችን በእጃችን ስላልሆነ፣ ምንም ያህል ብንጨነቅ ልናደርግ የምንችለው ነገር ስለሌለ አቅመቢስ እንሆናለን (ማቴ. 6፡27) ።

ሕመም በእምነታችን ወደ እግዚአብሔር ዘንድ ስለምናቀርበው የሕይወት ትርጉም እንድናውቅ ይጋብዘናል። ለሕይወታችን የሚሆን ጥልቅ እና አዲስ አቅጣጫን በምንፈልግበት ጊዜ ፈጣን መልስ ላናገኝ እንችላለን። ከዘመዶቻችን እና ከጓደኞቻችንም ቢሆን የምንፈልገውን እገዛ ሁል ጊዜ ላናገኝ እንችላለን።

2.      በብሉይ ኪዳን መጽሐፍ ውስጥ ተጽፎ የሚገኘውን የኢዮብ ታሪክ በዚህ ረገድ ማየት ይቻላል። የኢዮብ ሚስት እና ወዳጆች፣ በመከራው ጊዜ በቅርብ ሆነው አላገዙትም። ይልቁን ወቀሳን በማቅረብ ብቻውን ሆኖ እንዲጨነቅ አድርገውታል። ይህም ኢዮብ ጥፋተኛ እና የተሳሳተ መሆኑን እንዲያውቅ አድርጎታል።

ሆኖም ለከባድ ድክመቱ ሁሉ ግብዝነትን በመጥላት ለእግዚአብሔር እና ለሌሎች ሰዎች ሲል የሐቀኝነት መንገድ መከተልን መርጧል። ጩኸቱን ሳይታክት ወደ እግዚአብሔር በማቅርቡ መልስ በማግኘት፣ አዲስ አድማስን መመልከት ችሏል። ኢዮብ ስቃይን የተቀበለው ለቅጣት ወይም ከእግዚአብሔር እንዲለይ ሳይሆን የእግዚአብሔርን ይቅር ባይነት ለማሳየት ነው። የኢዮብ ልብ ከቆሰለ በኋላ ተፈውሷል። ከዚያ በኋላም የሚከተለውን ህያው እና ልብ የሚነካ ኑዛዜ ለጌታ እንዲህ በማለት አቅርቧል፥ “እኔ እስከ አሁን ስለ አንተ የማውቀው፣ ሰዎች የነገሩኝን በመስማት ብቻ ነበር፤ አሁን ግን በዓይኖቼ አየሁህ”። (ኢዮብ 42:5)

3.      ሕመም በርካታ ገጽታዎች አሉት። ሕመም የታመሙት ሰዎች ዋና ምልክት ቢሆንም የተረሱትን፣ የተገለሉትን፣ ፍትህ የጎደላቸው እና መሠረታዊ መብቶቻቸውን የተነፈጉትንም ያካትታል (ሁሉም ወንድማማቾች ናችሁ ቁ. 22)። የወቅቱ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በእኛ የጤና አጠባበቅ ሥርዓቶች ውስጥ ያሉትን ልዩነቶች ይበልጥ ከማጉላቱም በላይ ሕሙማንን ለመርዳት ያለን አቅም ውስን መሆኑንም ግልጽ አድርጎታል። አረጋዊያን፣ አቅመ ደካሞች እና ለአደጋ የተጋለጡት ሰዎች ሁል ጊዜም ቢሆን በቂ እንክብካቤን አያገኙም ወይም እኩል ተደራሽነት የላቸውም። ይህ የሚሆነው የተሳሳተ የፖለቲካ ውሳኔን በመውሰድ፣ የተፈጥሮ ሃብትን በፍትሃዊ መንገድ ካለመጠቀም እና ሃላፊነትን በአግባቡ ካለመወጣት የተነሳ ነው።

መዋዕለ ንዋይን ለሕሙማን ሕክምና አገልግሎት እና ጤና ድጋፍ ማፍሰስ፣ የጤና አግልግሎትን ለሁሉ ማዳረስ ከሚለው መሠረታዊ መርህ ጋር የተቆራኘ፣ የጋራ ጥቅምን የሚመለከት ጉዳይ ነው። የኮቪድ-19 ወረርሽኝም ቢሆን፣ የጤና ባለሞያዎች፣ በጎ ፈቃደኞች፣ ካህናት፣ ገዳማዊያን እና ገዳማዊያት፣ የታመሙትን በማገዝ፣ በማጽናናት፣ ቤተሰቦቻቸውንም በሙያዊነት መንገድ በመርዳት፣ ራስን አሳልፎ በመስጠት፣ ሃላፊነትን በመውሰድ እና የጎረቤት ፍቅርን በትጋት እና በቸርነት ማሳየታቸውን ጉልህ አድርጎታል። ወደ አደባባይ ወጥተው በግልጽ ያልታዩ በርካታ ወንዶች እና ሴቶች፣ ፊታቸውን ወደ ሌላ አቅጣጫ ከመመለስ ይልቅ ያላቸውን ሁሉ እንደ ጎረቤት እና እንደ ቤተሰብ አባል ከሚያዩአቸው ጋር መካፈልን መርጠዋል።

እንዲህ ዓይነቱ ቅርበት ለታመሙት እና በስቃይ ላይ ለሚገኙት ድጋፍን እና መጽናናትን የሚሰጥ ውድ ቅባት ነው። ክርስቲያን እንደመሆናችን፣ የተቸገሩትን መርዳት፣ የኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር ምልክት፣ በኃጢአት ለቆሰሉት ሰዎች በሙሉ ርኅራሔ የሚገለጽበት የመልካም ሳምራዊ ተግባር ነው። በመንፈስ ቅዱስ ሥራ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ከተባበርን፣ እንደ መሐሪ አባት ይቅር ባዮች እንድንሆን፣ በተለይም አቅመ ደካማ እና እየተሰቃዩ ያሉ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችንን ለመውደድ ተጠርተናል (ዮሐ. 13:34-35)። ወደ ተቸገሩት የምንቀርበውም በግል ብቻ ሳይሆን በማኅበር ተሰባስበን ነው። በክርስቶስ ያለን ወንድማዊ ፍቅር፣ ፈውስ የሚገኝበትን ኅብረት፣ ማንንም ወደ ጎን ሳይል በተለይም ዕርዳታን የሚፈልጉትን የሚያቅፍ ነው።

በዚህ ላይ መጥቀስ የምፈልገው ጉዳይ ቢኖር፣ በተለያዩ መንገዶች ጎረቤቶቻችንን በማገዝ ተጨባጭ አገልግሎት የሚገለጽበት ወንድማዊ አንድነት አስፈላጊነትን ነው። ማገልገል ማለት አቅመ ደካማ ለሆኑ ቤተሰቦች፣ ማኅበረሰቦች እና ሕዝቦች እንክብካቤን ማድረግ ማለት ነው (እ.አ.አ መስከረም 20/2015 የተደረገ የሃቫና ስብከት)። በዚህ አገልግሎት ሁላችንም የግል ፍላጎትን እና ምኞት፣ ስልጣንን ወደ ጎን በማድረግ፣ እርዳታ የሚጠይቁትን መመልከት ያስፈልጋል። አገልግሎት ማለት የተቸገሩትን መመልክት፣ መንካት፣ ቅርበታችንን እንዲሰሙ ማድረግን እና አንዳንድ ጊዜም ጭንቀታቸውን በመጋራት እገዛ ማድረግን ይጠይቃል። አገልግሎት በጭራሽ ርዕዮተ አለም  ሳይሆን ሰዎችን ማገልገል ይመለከታል።

4.      “የሕክምና ርዳታ” ውጤታማ እንዲሆን ከተፈለገ፣ የግንኙነት ገጽታ ሊኖረው ይገባል ፣ ምክንያቱም ይህ ለታካሚው ጠቅላላ የሕክምና መንገድን ያመቻቻል። ለዚህ ገጽታ አፅንዖትን መስጠቱ ሐኪሞች ፣ ነርሶች፣ በጎ ፈቃደኞች እና የጤና ባለሞያዎች በሙሉ ሕሙማን በመርዳት አስተማማኝ በሆነ የግል ግንኙነት ሃላፊነት እንዲሰማቸው እና  የፈውስ ጎዳናን እንዲከተሉ ሊረዳቸው ይችላል። ይህም በሕሙማን እና እገዛን ለመስጠት በተሰማሩት ሰዎች መካከል እምነትን፣ አክብሮትን፣ ግልጽነትን እና ዝግጁነትን ለማሳደግ ይረዳል። ከዚህም በተጨማሪ ራስን የመከላከያ አመለካከቶችን ማሸነፍ፣ ለሕሙማን ሊሰጥ የሚገባውን ክብርን፣ የጤና እንክብካቤ ሙያዊነት አገልግሎትን ለመጠበቅ እና ከሕመምተኞች ቤተሰቦች ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲኖር ያደርጋል።

        ይህን የመሰለ ከሕሙማን ጋር የሚኖር ግንኙነት፣ የማያቋርጥ የአገልግሎት ፍላጎት በኢየሱስ ቸርነት የሚገኘውን ጉልበት በማሳደግ፣ እነዚያ በሺህ ዓመታት ውስጥ አቅመ ደካሞችን በማገልገል በቅድስና የኖሩ ወንዶችና ሴቶች ምስክርነት ያሳያል። የኢየሱስ ክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ምስጢር፣ ለሕሙማን እና ለሕክምና ባለሞያዎች ተሞክሮ ሙሉ ትርጉም መስጠት የሚችል የፍቅር ምንጭ ነው። ቅዱስ ወንጌልም በተደጋጋሚ ይህን በግልጽ በማስረዳት፣ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚፈውሰው በአስማት ሳይሆን ነገር ግን የእግዚአብሔርን ስጦታ በሚቀበሉት ሰዎች እምነት እና ምላሽ ነው። ኢየሱስ ብዙን ጊዜ እንደሚለው፥ “እምነትህ አድኖሃል”።

5.      ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ! ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ የሰጣቸው የፍቅር ትዕዛዝ፣ ከሕሙማን ጋር ባለን የጠበቀ ግንኙነት ተጠብቆ ይኖራል።  አንድ ማኅበረሰብ ሰብዓዊ ሕልውና ሊኖረው የሚችለው የሚረጋገጠው፣ በወንድማማችነት የፍቅር መንፈስ በጣም ደካማ ለሆኑት እና ለሚሰቃዩ አባላቱ ውጤታማ በሆነ መንገድ እንክብካቤን ማቅረብ ሲችል ነው። ስለዚህ ማንም ብቸኛ ፣ የተገለለ ወይም የተተወ እንዳይሆን ፣ ይህንን ግብ ለማሳካት እንተጋ።

የታመሙትን ፣ የጤና ባለሞያዎችን እንዲሁም በችግር የተጎዱትን ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን በቸርነት ለሚረዱ በሙሉ አደራ በማለት፣ የምሕረት እናት እና የሕሙማን ፈውስ ለሆነች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አደራ እሰጣለሁ። በፈረንሳይ አገር ሉርድ በሚባል ቅዱስ ሥፍራ እና በዓለም ዙሪያ ካሉ ሌሎች በርካታ መቅደሶች ሁሉ፣ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እምነታችንን እና ተስፋችንን አጠናክራ እርስ በእርሳችን በወንድማማች ፍቅር አንዳችን ሌላውን እንድንከባከብ ትርዳን። ለሁላችሁም ቡራኬዬን በአክብሮት እሰጣለሁ"።

12 January 2021, 12:42