ፈልግ

ቅዱስ የእግዚአብሄር ቃል መጽሐፍ ቅዱስ ቅዱስ የእግዚአብሄር ቃል መጽሐፍ ቅዱስ 

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ ሁሉም ምዕመን መጽሐፍ ቅዱስን በየቀኑ እንዲያነቡ ጥሪ አቀረቡ።

በጥር 16/2013 ዓ.ም እለተ ሰንበት ላይ የእግዚአብሔር ቃል ለየት ባለ ሁኔታ የሚከበርበት እለት እንደ ሆነ የሚታወቅ ሲሆን ይህ በዓለ በቫቲካን በተከበረበት ወቅት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ባስተላለፉት መልእክት ሁሉም ክርስቲያኖች በኪሳቸው መጽሐፍ ቅዱስ እንዲይዙ እና በየቀኑ ጥቂት ጥቅሶችን እንዲያነቡ ማሳሰባቸው ተገልጿል።

አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ቤተክርስቲያን የእግዚአብሔርን ቃል ለየት ባለ ሁኔታ በማስታወስ ለሁለተኛ ጊዜ ባከበረችው እለተ ሰንበት ላይ ይህንን የእግዚአብሔር ቃል ለየት ባለ ሁኔታ ከፍተኛ ክብር ተሰጥቶ እና የእግዚአብሔርን ቃል አዘውትሮ ማንበብ አስፈልጊ እንደ ሆነ የሚገለጽበት እለተ ሰንበት ቤተክርስቲያን ስታከብር ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ምዕመናን ቅዱሳት መጻሕፍትን በተቻለ መጠን እንዲገዙ እና በተደጋጋሚ እንዲያነቧቸው ለምዕመናን ሁሉ ጥሪ አቀርበዋል።

በእሁዱ ጥር 16/2013 ዓ.ም  ቅዱስነታቸው በቫቲካን እንደ ተለመደው በእለቱ ቅዱስ ወንጌል ላይ ያደረጉትን አስተንትኖ ካገባደዱ በኋላ ባስተላለፉት መልእክት እንደ ገለጹት   “በዘመናችን ካሉት ታላላቅ ስጦታዎች መካከል አንዱ በቤተክርስቲያን እና በምእመናን ሕይወት ውስጥ የቅዱሳት መጻሕፍትን እንደገና መመርመር ነው” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት አክለውም “ከመቼውም ጊዜ በላይ መጽሐፍ ቅዱስ በተለያዩ ቋንቋዎች፣ በድምጽ እና በምስል በተደገፈ መልኩ ዲጂታል በሆነ ሁኔታ ለሁሉም ተደራሽ ሆኗል ያሉት ቅዱስነታቸው ይህንን እድል ተጠቅመን መጽሐፍ ቅዱስን ሁሌም ቢሆን ማንበብ ይኖርብናል” ብለዋል።

ክርስቶስ እና ቅዱሳን መጽሐፍት

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በተጨማሪ እንደ ገለጹት የ 5 ኛው ክፍለ ዘመን ታላቁ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር እና የቤተክርስቲያኗ ዶክተር የሆኑት ቅዱስ ጀሮም “ቅዱሳት መጻሕፍትን ችላ የሚል ሁሉ ክርስቶስን ይንቃል” ብለው እንደ ነበረ አስታውሰዋል።

እናም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት አክለውም ፣ በተቃራኒው ደግሞ እውነት ነው “ቅዱሳት መጻሕፍትን ለመረዳት አእምሮን የከፈተው ሥጋ የለበሰው ክርስቶስ መሆኑን የገለጹ ሲሆን ቃል ሥጋ የሆነው እና ከሙታን ተንስቶ ወደ ሰማይ የወጣው እርሱ ቅዱሳን መጽሐፍትን በሚገባ ለመረዳት እንችል ዘንድ አእምሮዋችንን የሚከፍተው እርሱ ነው ብለዋል።

የእግዚአብሔርን ቃል በይበልጥ የምንረዳው በስርዐተ አምልኮ ወቅት እና ብቻችንን ወይም በቡድን ሆነን ስንጸልይ ነው ብለዋል።

የወንጌል ደስታ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ምእመናንን ቅዱሳት መጻሕፍትን እንዲያዳምጡ ለማስተማር የሚሹትን ብዙ ምዕመናን አመስግነዋል፣ “ወንጌልን በማሰራጨት የሚገኘውን ደስታን በጭራሽ አንጣ” ብለዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በመቀጠል ሁሉም ሰው በቅርጽ አነስተኛ የሆነ የቅዱስ ወንጌል መጽሐፍ በኪሳቸው ወይም በሻንጣቸው እንዲይዙ በተደጋጋሚ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል። እናም በየቀኑ ቢያንስ ሦስት ወይም አራት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን እንድናነብ ቅዱስነታቸው አጥብቀው አሳስበዋል።

24 January 2021, 18:34