ፈልግ

ቬነዙዌላዊያን በቫቲካን በሚገኘው ቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ላይ ለጸሎት ተገኝተው ቬነዙዌላዊያን በቫቲካን በሚገኘው ቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ላይ ለጸሎት ተገኝተው 

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የቬነዙዌላን ሕዝብ በጸሎታቸው አስታወሱ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በቬነዙዌላ የሜሪዳ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የዋና ከተማዋ ካራካስ ሐዋርያዊ አስተዳዳሪ ለሆኑት ለብጹዕ ካርዲናል ባልዳዛር ፖራስ ካርዶሶ በላኩት የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክት፣ በዚህ ወቅት በኮቪድ-19 ወረርሽኝ እና በድህነት ከተጎዳው ከቬነዙዌላ ሕዝብ ጎን ሆነው በጸሎት የሚያስታውሷቸው መሆኑን ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቅዱስነታቸው ከዚህ በፊትም አገሪቱ የምትገኝበትን የፖለቲካ፣ የኤኮኖሚ እና የማኅበራዊ ቀውሶችን በማስታወስ በጸሎት የረዷቸው መሆኑ ሲታወስ፣ በዛሬው መልዕክታቸው በመጨረሻዎቹ ዓመታት ውስጥ የቬነዙዌላ ሕዝብ የገባበትን ከፍተኛ ሰብዓዊ፣ ማኅበራዊ እና ኤኮኖሚያዊ ቀውስ አስታውሰው፣ ከዚህም በተጨማሪ በአገሪቱ እየተስፋፋ በሄደው በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት የሚሰቃየውን ሕዝብ በጸሎታቸው የሚያስታውሱ መሆኑን ገልጸዋል።

የሚሰቃየውን ሕዝብ በእግዚአብሔር አባታዊ ፍቅር ማገዝ

“እግዚአብሔር ብርታትን እና መረጋጋትን መስጠቱን ይቀጥል” ያሉት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ “እግዚአብሔር በርኅሩኅ ልቡ በኮቪ-19 ወረርሽኝ፣ በጉልበተኞች ልብ መደንደን እና በድህነት ምክንያት ለሚሰቃይ ታማኝ እና ቅዱስ ሕዝብ መጽናናትን ይሰጣል” ብለዋል።   

የእመቤታችን፣ የቅዱስ ዮሴፍ እና የቅዱስ ባልዳዛር ጥበቃ

የእግዚአብሔር ትህትና በተገለጠበት የኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀት፣ ዓለምን የጋረገው ጨለማ በብርሃን እንደሚሸነፍ በቬነዙዌላ የሜሪዳ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የካራካስ ሐዋርያዊ አስተዳዳሪ ለብጹዕ ካርዲናል ባልዳዛር በላኩት መልዕክት ገልጸው፣ ካርዲናሉ ለሚያበረክቱት ሐዋርያዊ አገልግሎት እና ለግል ሕይወት የእግዚአብሔርን ብርታት በጸሎታቸው ጠይቀው፣ የእመቤታችን፣ የቅዱስ ዮሴፍ እና የቅዱስ ባልዳዛርን ጥበቃ ተመኝተውላቸዋል።

ካርዲናል ፓሮሊን እና ብጹዕ አቡነ ፔኛ ደስታቸውን ገልጸውላቸዋል

ከር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የደስታ መግለጫ መልዕክት ጋር፣ ከዚህ በፊት በቬነዙዌላ የቅድስት መንበር እንደ ራሴ የነበሩት እና ባሁኑ ጊዜ የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን ደስታቸውን ገልጸዋል። ለብጹዕ ካርዲናል ባልዳዛር የደስታ መግለጫ መልዕክት ከላኩት መካከል፣ የቫቲካን መንግሥት ተጠባባቂ ዋና ጸሐፊ ቬነዙዌላዊው ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ኤድጋር ፔኛ ፓራ መሆናቸው ታውቋል።

የቬነዙዌላ ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ

ብጹዕ ካርዲናል ባልዳዛር ፖራስ ካርዶሶ በያዝነው ሳምንት ውስጥ የተካሄደውን የቬነዙዌላ ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ስብሰባን በበይነ መረብ መከታተላቸው ታውቋል። ብጹዓን ጳጳሳቱ በጉባኤያቸው አገራቸው የሚገኝበትን ሁኔታ ከማጤናቸው በተጨማሪ፣ አምና በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ለሌላ ጊዜ እንዲዛወር በተደረገው እና ዘንድሮ ሊካሄድ በታቀደው ሁለተኛው ብሔራዊ የምክር ቤት ሐዋርያዊ ጉባኤን በተመለከተ ተወያይተዋል። ሰኞ ጥር 3/2013 ዓ. ም. በሚደረገው የጉባኤው መዝጊያ ዕለት የቬነዙዌላ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ሐዋርያዊ ማሳሰቢያ ይፋ እንደሚያደርግ ይጠበቃል።

09 January 2021, 14:38