ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ የጸሎት ኃይል የወቅቱን እውነታና ልብን ሊለውጥ እንደሚችል አስገነዘቡ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በየወሩ ለወሩ የሚሆን የጸሎት ሐሳብ በቪዲዮ መልእክት ይፋ እንደሚያደርጉ ይታወቃል። በዚህም መሠረት ለታኅሳስ ወር እንዲሆን በማለት ባቀረቡት የጸሎት ሐሳብ፣ ጸሎት የወቅቱ እውነታን እና ልባችንን ሊለውጠው እንደሚችል አስገንዝበው “በጸሎት አማካይነት ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ያለንን ግንኙነት ማሳደግ እንችላለን” ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ጸሎት ወደ እግዚአብሔር ዘንድ ያቀርበናል

የጎርጎሮሳዊያኑ 2020 ዓ. ም. በሚገባደድበት የታኅሳስ ወር ወስጥ የመላዋ ካቶሊካዊ ቤተክርስቲያን ምዕመናን የሚተባበሩበትን የቅዱስነታቸውን የጸሎት ሃሳብ በቪዲዮ ምስል ይፋ ያደረገው ዓለም አቀፍ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የጸሎት ጥሪ አስተባባሪ ጽ/ቤት መሆኑ ታውቋል። ቅዱስነታቸው፣ ዓለማችን በኮቪድ-19 ወረርሽኝ እየተሰቃየ በሚገኝበት በያዝነው ዓመት፣ ጸሎት ከእግዚአብሔር ጋር መነጋገር የምንችልበት እና የኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወት ምስጢር የሚታይበት መንገድ መሆኑን አስረድተዋል። በጸሎት ሕይወት አማካይነት ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ጥልቅ እና የግል ግንኙነትን እንዲኖረን፣ ልባችንንም መለወጥ እንችላለን። በጸሎት በኩል ኢየሱስን ማድመጥ፣ ማስተንተን፣ ከእርሱ ጋር በመነጋገር፣ ሕይወታችንን መለወጥ እንችላለን። ጸሎት ወደ እግዚአብሔር ዘንድ እንድንደርስ የሚመራን መንገድ ነው።

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በኮቪድ-19 ወቅት ያቀረቡት ጸሎት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የጸሎት ሰው መሆናቸውን ዓለም አቀፉ የጸሎት ጥሪ አስተባባሪ ጽ/ቤት ዘንድሮ በተለያዩ ጊዜያት ባዘጋጀው የቪዲዮ ምስል ገሃድ አድርጓል። ከእነዚህም መካከል የኮቪድ-19 ወረርሽን በማስመልከት በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ምዕመናን ባልተገኙበት ሥፍራ ያካሄዱት የጸሎት ስነ-ስርዓት፣ በሮም ከተማ መካከል “ኮርሶ” ጎዳና ያደረጉት የቅዱስ ማርቼሎ የፍኖተ መስቀል ስነ-ስርዓት እና በሮም ከተማ ወደሚገኝ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ታላቁ ባዚሊካ በመሄድ የሮም ከተማ ሕዝብ ጠባቂ ወደ ሆነች እመቤታችን ቅድስት ማርያም ያቀረቡት ጸሎት የሚታወስ ነው።

የኢየሱስ ክርስቶስ የጸሎት ሕይወት

ለር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ጸሎት በጊዜ እና በቦታ ወይም በውስጣዊ አስተንትኖ ብቻ የተገደበ አይደለም። “በጸሎት ኃይል እውነታን እና ልባችንንም መለወጥ እንችላለን” በማለት ቅዱስነታቸው በቪዲዮ መልዕክታቸው አስረድተዋል። “ጸሎት ሁል ጊዜ ለውጥን ያመጣል። ብዙ ነገሮችን መሥራት ብንችልም ነገር ግን ያለ ጸሎት ፍሬ የለውም” ብለዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጥቅምት 25/2013 ዓ. ም. ባቀረቡት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የጸሎት ሕይወት ማስተማራቸው ይታወሳል። ኢየሱስ ክርስቶስ አገልግሎቱን ዘወትር በጸሎት ኃይል ያከናውን ነበር። በደከመው ጊዜም ለጸሎት ወደ ተለየ ሥፍራ ይሄድ እንደነበር አራቱ ወንጌላት ይገልጻሉ። እነዚህ ሁሉ በጸሎት በኩል ስለምናደርጋቸው ግንኙነቶች እንድናስታውስ የሚያግዙን ምልከታዎች ናቸው። ምልከታዎቹ ኢየሱስ ክርስቶስ ከድሆች እና ከሕመምተኞች ጋር በነበረ ጊዜም ከአባቱ ጋር የሚያደርገው ግንኙነቶች ያላቋረጡ መሆኑን ይገልጻሉ።

ጸሎት ለቤተክርስቲያን ተልዕኮ ዋና መሠረት ነው

ዓለም አቀፍ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የጸሎት ጥሪ ባሁኑ ጊዜ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የተለያዩ አገራት ካቶሊካዊ ምዕመናንን የሚያገናኝ ነው። “Click to Pray” በሚል መጠሪያ የሚታወቅ የጸሎት መድረክን ጨምሮ ሌሎችም መድረኮች ለቤተክርስቲያን ተልዕኮ ሰፊ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ። ለዘንድሮ ታኅሳስ ወር የተዘጋጀው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የጸሎት ሃሳብ፣ ዓለም አቀፉ የጸሎት ሕብረት የተመሠረተበትን 175ኛ ዓመት የሚያስታስ በመሆኑ በዚህ ወቅት ምዕመናን በጸሎት እንዲተጉ የሚያሳስብ ነው።

የር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ዓለም አቀፍ የጸሎት ጥሪ እና የቅዱስ ቁርባን ወጣቶች እንቅስቃሴ ጽ/ቤት አስተባባሪ የሆኑት ክቡር አባ ፍሬደሪክ ፎርኖስ በበኩላቸው፣ ዓለም አቀፍ የጸሎት ሕብረት ምስረታ 175ኛ ዓመት ታላቅ በዓል የሚከበርበት ወቅት መሆኑን ገልጸዋል። በዓሉን ምክንያት በማድረግ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከ5000 ምዕምናን በላይ በተገኙበት በቅዱስ ጳውሎስ ስድስተኛ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ውስጥ የጸሎት ስነ-ስርዓት መፈጸማቸው አስታውሰው፣ በዚህ የጸሎት ስነ-ስርዓት ላይ ባስተላለፉት መልዕክት “ጸሎት እና የቤተክርስቲያን ተልዕኮ የማይነጣጠሉ ናቸው” ማለታቸውን አስታውሰዋል። የቤተክርስቲያን ተልዕኮ ዓለማችንን የሚያጋጥሙ ችግሮች ለማስወገድ የሚጥር በመሆኑ፣ ችግሮች ሊወገዱ የሚችሉት በጸሎት ኃይል ብቻ መሆኑን ገልጸው፣ ጸሎት ለቤተክርስቲያን ተልዕኮ ዋና መሠረት መሆኑን አስረድተዋል። ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው መጨረሻ “ብዙዎች ጸሎትን በጸጥታ ሆነው የሚያስተነትኑበት ጊዜ ብቻ አድረገው ቢመለከቱትም፣ የጸሎትን ትርጉም በጥልቀት ለተረዱት ግን የሕይወታቸው መሠረት ነው” ማለታቸውን ክቡር አባ ፍሬደሪክ ፎርኖስ አስታውሰዋል። ጸሎት በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ወደ እግዚአብሔር ዘንድ የሚያደርሰን፣ ሌሎችን እንድናፈቅር የሚያደርገን መሆኑንም ቅዱስነታቸው አስረድተዋል። የጸሎት መልስ ቢዘገይም ፍሬው እጅግ ብዙ መሆኑን ገልጸዋል። በቅዱስ ወንጌል እንደተጠቀሰው . . . አንዱ ሠላሳ፣ አንዱ ስልሳ፣ አንዱም መቶ ፍሬን ያፈራል (ማር. 4፡20)። ጸሎት የቤተክርስቲያን ተልዕኮ ፍሬያማ የሚሆንበት በመሆኑ፣ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የግል ግንኙነት በመፍጠር፣ ዘወትር ከቅዱስ ቃሉ እየተመገብን የጸሎት ሕይወትን ማሳደግ እንዳለብን ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው አደራ ብለዋል።   

10 December 2020, 13:16