ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በእዚህ የገና በዓል በባህር ላይ ለሚሰሩ መርከበኞች እንጸልይ አሉ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በታኅሳስ 12/2013 ዓ.ም “100 የገና በዓል ትዕይንቶች” የተሰኘውን ዐውደ ርዕይ በሮሜ ከተማ የሚገኙ ምዕመናን እንዲጎበኙ ጋብዘው በእዚህ በአስቸጋሪው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት በባህር ላይ በመጓዝ በመሥራት ላይ ለሚገኙ መርከበኞች ጸሎት ማድረጋቸው ተገልጿል።

የእዚህ ዜና አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ይህንን የተናገሩት ትላንት ታኅሳስ 11/2013 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ በእለቱ በተነበበው ቅዱስ ወንጌል ላይ አሰትንትኖ ካደረጉ በኋላ “ የእግዚአብሔር መልአክ ማርያምን ያበሰረበት” የብስራተ ገብርኤል ጸሎት ከደገሙ በኋላ ባስተላለፉት መልእክት እንደ ነበረ የተገለጸ ሲሆን ቅዱስነታቸው በወቅቱ ኮቪድ-19 በተባለው ወረርሽኝ ምክንያት ወደ ቤታቸው መመለስ ለማይችሉ በርካታ የባህር ላይ መርከበኞች ጸሎት እንዳደረጉላቸውም ተዘግቧል።

ቅዱስነታቸው በመልእክታቸው አክለው እንደ ገለጹት የሥራ ውላቸው ሳይታደስላቸው በአሁኑ ወቅት በዓለም ዙሪያ በባህር ላይ የሚገኙ ወደ 400,000 የሚጠጉ የባህር ላይ ሠራተኛ መርከበኞች እንደ ሚገኙ አክለው ገልጸዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሱ “እነዚህን ሰዎች እና በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ የሚገኙ ሰዎች የሚገጥሟቸውን ፈተና ሁሉ በትዕግስት ማለፍ እንዲችሉ እንድታፅናና የባህር ዳርቻ ኮከብ የሆነችው ድንግል ማርያምን እጠይቃለሁ ፣ እናም መንግስታት እነዚህ በባሕር ላይ በመርከቦች ውስጥ የሚሰሩ ሰዎች ወደሚወዷቸው ቤተሰቦቻቸው እንዲመለሱ ሁሉም ምዕመን ጸሎት እንዲያደርጉ እጠይቃለሁ” ብለዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በእዚህ የጎሮጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ በመጪው አርብ እለት በሚከበረው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል መንፈሳዊ ዝግጅት ማድረግ ስለሚገባ ለእዚህ ዝግጅት የሚሆን በቂ ጊዜ ምዕመናን እንዲመደቡ ጥሪ አቅርበዋል። ሁሉም ምዕመን በአቅራቢያችን በተለያዩ ምክያቶች ለሚሰቃዩት ሰዎች ትኩረት በመስጠት እና ስለ ገና በዓል በማሰላሰል ማክበር እንደ ሚገባ አክለው ገልጸዋል።

“የሚሠቃየው ወንድም የትም ይሁን የት ከእኛ አንዱ ነው። እርሱ በግርግም ውስጥ የሚገኘው ኢየሱስ ነው ፤ የሚሠቃየው ኢየሱስ ነው ” ብለዋል ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ። እዚያ ውስጥ በችግር ውስጥ ባለው ወንድም ውስጥ በመግባት እርሱን መርዳት ማለት ኢየሱስን እንደ መርዳት ይቆጠራል ብለዋል።

100 የገና በዓል ትዕይንቶች ኤግዚቢሽን

በተጨማሪም በዚህ ዓመት በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ቅጥር ግቢ ስር የተቀመጠውን “100 የገና በዓል ትዕይንቶች” ዐውደ ርዕይን እንዲጎበኙ በሮማ ውስጥ የሚገኙትን ምዕመናን ጋብዘዋል። ሰዎች ኢየሱስ እንዴት እንደ ተወለደ ለማሳየት በኪነ-ጥበብ በኩል እንዴት እንደሚፈልጉ ለመረዳት በአከባቢው በቫቲካን ቅጥር ግቢ ውስጥ የሚገኘውን ኢየሱስ የተወለደበትን ሁኔታ የሚያሳዩ የገና በዓል ትዕይንቶች እንድትጎበኙ እጋብዛችኋለሁ ብለዋል። እነዚህ የገና በዓል ትዕይንቶች በእምነታችን ውስጥ ትልቅ የሆነ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ የሚሰጡ ናቸው በማለት አክለው ገልጸዋል።

የቫቲካን “100 የልደት ትዕይንቶች” ዐውደ ርዕይ በየቀኑ በሮም ሰዓት አቆጣጠር ከጥዋቱ 4 ሰዓት እስከ ምሽቱ 2 ሰዓት ድረስ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ በሚገኘው ቅጥር ግቢ ለጎብኚዎች ክፍት እንደ ሚሆን ተገልጿል።ኤግዚቢሽኑን ከታህሳስ 13 እስከ ጥር 10/2013 ዓ.ም ድረስ ለጎብኚዎች ክፍት እንደሚሆን ተገልጿል።

20 December 2020, 12:16