ፈልግ

ር.ሊ.ጳ. ፍራንቸስኮስ የገና በዓል ሁላችንም ወንድማማቾች እና እህተማማቾች እንደሆንን ያስታውሰናል አሉ!

በታላላቅ መንፈሳዊ በዓላት በተለይም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደበት ቀን በሚከበርበት በገና በዓል እለት እና እንዲሁም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን በተነሳበት የፋሲካ በዓል እለት ልማዳዊ በሆነ መልኩ አንድ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በላቲን ቋንቋ “Urbi et Orbi” በአማሪኛው “ለከተማው (ሮም) እና ለዓለም”  የተሰኘ መልእክት በዓላቱን አስመልክተው መልእክት እንደ ሚያስተላልፉ ይታወቃል። በእዚህም መሰረት የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የማሕበረሰ ክፍሎች ዘንድ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደበት ቀን በታኅሳስ 16/2013 ዓ.ም የተከበረበትን የገና በዓል እለት ምክንያት በማድረግ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ ከቫቲካን መልእክት ማስተላላፋቸው የተገለጸ ሲሆን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ሁላችንም ወድማማች እና እህተማማቾች መሆናችንን ያስታውሰናል ማለታቸው ተገልጿል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በላቲን ቋንቋ “Urbi et Orbi”  በአማርኛው “ለከተማው (ሮም) እና ለዓለም”  ለተሰኘ መልእክታቸው ለእዚህ አመት የገና በዓል የመረጡት መሪ ቃል “ሕፃን ተወልዶልናልና፤ ወንድ ልጅ ተሰጥቶናል” (ኢሳ 9፡6) የሚለው እንደ ነበረ የተገለጸ ሲሆን ይህ የሊቀ ጳጳሱ የገና መልእክት ጭብጥ ሐሳብ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሁሉም የሰው ልጆች ሲል እንዴት እንደተወለደ ያመለክታል “እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ሲል አንዲያ ልጁን እንዴት እንደ ሰጠ” የሚያሳይ መልእክት እንደ ነበረ ተዘግቧል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በእዚህ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በተከበረበት የወቅት በላቲን ቋንቋ “Urbi et Orbi”  በአማርኛው “ለከተማው (ሮም) እና ለዓለም”  በተሰኘ የተለመደው መልእክታቸው  የተስፋ እና የመጽናናት ቃላት በተመለከተ ሲናገሩ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ሁል ጊዜ የተስፋ ምንጭ ነው በማለት የገለጹ ሲሆን “ይህ ሕጻኑ ኢየሱስ ለእኛ ሲል ያለምንም ድንበር፣ ልዩነት ወይም ማንንም ሰው ሳያገል ተወልዶልናል” ብሏል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በዚህን ዓመት በላቲን ቋንቋ “Urbi et Orbi”  በአማርኛው “ለከተማው (ሮም) እና ለዓለም”  የተሰኘ መልእክታቸውን ያስተላለፉት መልእክት እንደ ተለመደው እና ዘወትር እንደ ሚያደርጉት በቫቲካን ከሚገኘው የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ሳይሆን በእዚህ በአንዳንድ የአውሮፓ አገራት እንዲሁም በጣሊያን በአዲስ መልክ እንደ ገና በተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽ ምክንያት በሽታው እንዳይዛመት በተጣለው ገደብ ሰበብ የተነሳ በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ አዳራሽ ውስጥ እንደ ነበረ ተገልጿል።

ሁላችንም ወንድማማቾች እና እህተማማቾች ነን

ከየአህጉሩ ፣ ከእያንዳንዱ ቋንቋ እና ባህል የምንመጣ ቢሆንም በራሳችን ማንነቶች እና ልዩነቶች አኳኸን ለሕጻኑ ለክርስቶስ ምስጋና ይግባውና  “ሁላችንም እርስ በርሳችን ወንድማማቾች እና እህተማማቾች ልንባል እንችላለን” በማለት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ አፅንዖት ሰጥተው ተናግረዋል። በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት እየተባባሱ ለመጡት እንደ ሥነ ምህዳራዊ ቀውስ፣ ከባድ የኢኮኖሚ እና ማህበራዊ ችግሮች ያሉ በታሪክ ውስጥ በአሁኑ ወቅት የሚገጥሙንን ግዙፍ ፈተናዎች ለመፍታት ይህ መሰረታዊ እውነታ ማለትም ሁላችንም ወንድማማቾች እና እህተማማቾች መሆናችንን መገንዘብ የምንችለው ቁም ነገር ሊሆን ይገባል ብለዋል።

እግዚአብሔር ይህ ወንድማዊ አንድነት እንዲኖር አድርጓል

እግዚአብሔር አንዲያ ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን በመስጠት ይህ ወንድማዊ አንድነት እውን እንዲሆን ማደረጉን በመግለጽ መልእክታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው እንደ ወንድም እና እህት የምንመኘው እና ​​የምንፈልገው አንድነት፣ እግዚአብሔር እውን እንዲሆን አድርጎታል ያሉ ሲሆን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሱ አክለው እንደ ገለጹት “ልጁን ኢየሱስን በመስጠት በእውነተኛ ፍቅር ላይ የተመሠረተ” ወንድማማችነት ከሌሎች ጋር የምንገናኝባቸው እና የሚሰማቸውን ስቃይ በርኅራሄ እንድንመለከት፣ ሰዎች  “የቤተሰቤ ፣ የጎሳዬ ወይም የሃይማኖቴ አካል ባይሆኑም እንኳ” በችግር ላይ የሚገኙ ማንኛቸውንም ሰዎች መንከባከ እንድንችል ሊያግዘን ነው የመጣው ብሏል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በቤተልሔም የተወለደው ሕጻኑ ኢየሱስ አቅመ ደካሞችን ፣ ሕሙማንን ፣ ሥራ አጥና በወረርሽኙ የተጎዱትን ለመርዳት ልባችንን እንድንከፍት እንዲረዳን እንዲሁም በእዚህ በወረርሽኙ ምክንያት በተደነገገው ከቤት አለመውጣት ፖሊሊ ምክንያት በሴቶች ላይ እየደረሰ በሚገኘው የቤት ውስጥ ጥቃት መከላከል የምንችልበትን ልቦና እንዲሰጠን ልንማጸነው የገባል ብለዋል። በአሁኑ ወቅት በመላው ዓለም ተንሰራፍቶ በሚገኘው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ለመከላከል በሚሰጠው ክትባት እና ህክምና ሁሉም ሰዎች ተደራሽ እንዲሆኑ ለማድረግ ከጤና አጠባበቅ ጀምሮ ዓለም አቀፍ የትብብር መንፈስ እንዲኖር ጥሪ አቅርበዋል።

በመከራ ላይ ለሚገኙ ሰዎች መጸለይ እና ለሰላም መሥራት

“በሁሉም ሰው ውስጥ ፣ የእግዚአብሔር ፊት ሲንፀባረቅ አይቻለሁ፣ እናም በስቃይ ላይ በሚገኙ ሰዎች ውስጥ ጌታ የእኔን እርዳታ ሲለምን አየሁ። በህመም ፣ በድሃ ፣ በስራ አጥነት ፣ በተገለሉ ፣ በስደተኞች ውስጥ ጌታን አየዋለሁ” በማለት በመልእክታቸው ቅዱስነታቸው አክለው ገልጸዋል።

በዓለማችን ያሉትን ብርሃኖች እና ጥላዎች በመመልከት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ጸሎታቸውን በማቅረብ በዓለም ዙሪያ በተለይም በሦሪያ ፣ በኢራቅ እና በየመን በጦርነት ሰለባ የሆኑ ብዙ ሕፃናት ሁሉም ሰዎች በጸሎት በማስታወስ ሁሉም የራሳቸውን ድርሻ እንዲያበረክቱ አበረታተዋል። በተጨማሪም በመላው መካከለኛው ምስራቅ እና ምስራቃዊ ሜድትራንያን የሚገኙ የማሕበረሰብ ክፍሎች ለሰላም እንዲሰሩ በእዚህ ረገድ ቁርጠኛ እንዲሆኑ ቅዱስነታቸው ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን እናም ሕፃኑ ኢየሱስ ተወዳጅ የሆኑ የሶሪያን ሕዝቦችን እዲፈውስ እና ለእርቅ ለሚሰሩ ሰዎች መጽናናትን እንዲያመጣ በተለይም ያዚዲ በመባል የሚታወቁ በኢራቅ የሚገኙ ጎሳዎች እየደረሰባቸው የሚገኘውን ስቃይ እና መከራ እንዲቀንስ መጸለይ እና በተግባር መሥራት ተገቢ ነው ብለዋል።

በሊቢያ ሰላም እንዲሰፍን እንዲሁም እስራኤል እና ፍልስጤማውያን ቅሬታዎችን ለመቅረፍ የጀመሩትን ውይይት ለመቀጠል የጋራ መተማመንን እንዲያገኙ መጸለያቸውን እንደ ሚቀጥሉ በመልእክታቸው የገለጹት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ሊባኖሳዊያን ተስፋቸው ተመልሶ በሕይወት ጎዳና ላይ እንዲቀጥሉ እና አገሪቱ ለነፃነት እና በሰላም አብሮ የመኖር ራይዋን በፅናት እንድትቋቋም መሪዎች እያደረጉ የሚገኙትን ጥረት እንዲቀጥሉበት ቅዱስነታቸው አበረታተዋል።

ሌሎች የአለም አካባቢዎችን በተመለከተ ቅዱስነታቸው በመልእክታቸው እንደ ገለጹት በምስራቅ ዩክሬን ናጎርኖ-ካራባህ የተደረገውን የተኩስ አቁም ስምምነት ለማስቀጠል ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ድጋፍ እንዲያደርግ ጸሎታቸው እንደ ሆነ የገለጹ ሲሆን እንዲሁም የትጥቅ ግጭቶች እና የሰብአዊ ቀውስ ባሉባቸው አካባቢዎች ቡርኪናፋሶ ፣ ማሊ ፣ ኒጀር ፣ ኢትዮጵያ ፣ ሞዛምቢክ ፣ ደቡብ ሱዳን ፣ ናይጄሪያ እና ካሜሩንን አስታውሰው ይህ ስቃይ እና ግጭት እንዲፈታ ምኞታቸው እና ጸሎታቸው እንደ ሆነ ቅዱስነታቸው አክለው ገልጸዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ የአሜሪካን አህጉር በተለይም በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የተጎዱትን እንዲሁም በቺሊ እና በቬንዙዌላ በተፈጠረው ውጥረት መረጋጋት እንዲመጣ በጸሎታቸው አስታውሰዋል። በተፈጥሮ አደጋዎች የተጎዱትን በተለይም ፊሊፒንስ እና ቬትናምን አስታውሰዋል። በበርማ የሚገኙትን የሮሂንጊያ ህዝብ ስቃይ ወደ መልካም ሁኔታ እደሚቀየር እና ተስፋቸው እንደ ሚታደስ ተስፋ እንደ ሚያደርጉ ቅዱስነታቸው አክለው ገልጸዋል።

ተስፋን ፣ መፅናናትን እና ርዳታን መስጠት

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ መልእክታቸውን ሲቀጥሉ እየገጠሙን ያሉ ከባድ ችግሮች ቢኖሩም ሕጻኑ ኢየሱስ “ህመም እና ክፋት የመጨረሻ ቃል እንዳልሆኑ ይነግረናል” ሲሉ የገለጹ ሲሆን “በምትኩ ለሚሰቃዩት ተስፋን ፣ መፅናናትን እና እርዳታን ለማምጣት የሚሠሩትን ሰዎችን በዋቢነት” ገልጸዋል። መልካም የሆነ አብነታቸውን አሞካሽተዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በእዚህ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በተከበረበት የወቅት በላቲን ቋንቋ “Urbi et Orbi”  በአማርኛው “ለከተማው (ሮም) እና ለዓለም”  በተሰኘ የተለመደው መልእክታቸው  ማጠቃለያ ላይ እንደ ገለጹት በወረርሽኙ ምክንያት ዛሬ ይህንን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን የልደት በዓል አንድ ላይ ማክበር ያልቻሉ ቤተሰቦችን አስታውሰዋል። ይህ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መወለድ የሚከበረበት የገና በዓል “ቤተሰብ እንደ ሕይወት እና እንደ እምነት መገኛ ፣ እንደ እርስ በእርስ መቀባበያ እና የፍቅር ሕይወት ፣ የውይይት ፣ የይቅርታ እና ለሰው ልጆች ሁሉ የሰላም ምንጭ” እንዲሆን ይረዳን ዘንድ መጸለይ እንደ ሚገባ የገለጹ ሲሆን ይህንን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደበትን የገና በዓል ለሚያከብሩ ሰዎች ሁሉ መልካም የገና በዓል እንዲሆን ከተመኙ በኋላ በላቲን ቋንቋ “Urbi et Orbi”  በአማርኛው “ለከተማው (ሮም) እና ለዓለም”  የተሰኘውን የገናን በዓል አስመልከተው ያስተላለፉትን መልእክት አጠቃለዋል።

25 December 2020, 19:27