ፈልግ

ቅዱስ ዮሴፍ ቅዱስ ዮሴፍ  

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ መጪው ጊዜ “የቅዱስ ዮሴፍ ዓመት” እንዲሆን አወጁ!

በላቲን ቋንቋ “Patris corde” በአማርኛው በግርድፉ ሲተረጎን “የአብ ልብ” በሚል አርእስት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በሕዳር 29/2013 ዓ.ም ይፋ ባደረጉት ሐዋርያዊ መልዕእክት ቅዱስ ዮሴፍ “የአለም አቀፋዊቷ ቤተክርስቲያን የበላይ ጠባቂ” መሆኑ የታወጀበት የ150 ኛ ዓመት የምስረታ በዓል የሚያስታውስ ሐዋርያዊ መልእክት እንደ ሆነም ተገልጿል። ይህንን ቅዱስ ዮሴፍ  “የአለም አቀፋዊ ቤተክርስቲያን የበላይ ጠባቂ” መሆኑ የታወጀበት የ150 ኛ ዓመት የሚዘክር በዓል ከሕዳር 29/2013-ሕዳር 29/2014 ዓ.ም ደረስ እንድከበር ቅዱስነታቸው የወሰኑ ሲሆን ጊዜውም “የቅዱስ ዮሴፍ ዓመት” ተብሎ እንዲጠራ ቅዱስነታቸው አውጀዋል።

ይህንን ዝግጅት ከእዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ!

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

በላቲን ቋንቋ “Patris corde” በአማርኛው በግርድፉ ሲተረጎን “የአብ ልብ” በሚል አርእስት በቅርቡ ይፋ የሆነው ሐዋርያዊ መልእክት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ ቅዱስ ዮሴፍን እንደ ተወዳጅ፣ ርህሩህ እና አፍቃሪ፣ ታዛዥ ፣ ተቀባይ የሆነ አባት እንደሆነ የሚገልጽ ሐዋርያዊ መልእክት ሲሆን በተጨማሪም የፈጠራ ችሎታ ያለው፣ ብርቱ የሆነ ጥላ ከለላ መሆን የሚችል አባት እንደ ሆነም ገልጸዋል።

ሐዋርያዊ መልእክቱ ከእዚህ ቀደም የነበሩት ብፁዕ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፒየስ 9 ኛ “ቅዱስ ዮሴፍ የአለም አቀፋዊ ቤተክርስቲያን ጠባቂ” መሆኑ የታወጀበት የ 150 ኛ ዓመት የምስረታ በዓል የሚዘክር ነው። ዓመቱን ለማክበር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “የቅዱስ ዮሴፍ ዓመት” በማለት የጎሮጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ  በሕዳር 29/2013 ዓ.ም “የጽንሰታ ማርያም” አመታዊ በዓል በተከበረበት ወቅት ቅዱስነታቸው ያወጁት “የቅዱስ ዮሴፍ ዓመት” ሲሆን ይህ አመት እስከ ሚቀጥለው ሕዳር 29/2014 ዓ.ም ድረስ ለአንድ አመት ያህል የሚከበር በዓል ነው።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በላቲን ቋንቋ “Patris corde” በአማርኛው በግርድፉ ሲተረጎም “የአብ ልብ” በሚል አርእስት በቅርቡ ያፋ ባደረጉት ሐዋርያዊ መልእክት ዳራ ውስጥ “ኮቪድ -19” ወረርሽኝ የተካተተበት ሲሆን ይህንን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በተመለከተ በሐዋርያዊ መልእክቱ ውስጥ እንደ ተጠቀሰው ወረርሽኙ የብርሃን እይታ ክብር ርቋቸው የነበሩ ቢሆኑም በትዕግሥት የተቀመጡ እና በየቀኑ ተስፋ የሚያደርጉ “ተራ” ተብለው የተፈረጁ ሰዎች አስፈላጊነት በበለጠ በግልጽ እንድንረዳ ረድቶናል በማለት ገልጸዋል።  በዚህ ውስጥ “ብዙም ያልተሰተዋለው ሰው በዕለት ተዕለት ሕይወቱ በአስተዋይነት እና ምስጢራዊ በሆነ መልኩ ንቁ ተሳትፎ ሲያደርግ” የነበረውን ቅዱስ ዮሴፍን እነዚህ “ተራ” ተብለው የፈረጁ ሰዎች በእዚህ ረገድ እርሱን እንደ ሚመስሉ የገለጹ ሲሆን ሆኖም ቅዱስ ዮሴፍ አንዳደርገው እነርሱም “በመዳን ታሪክ ውስጥ ተወዳዳሪ የማይገኝለት ሚና” እንደ ሚጫወቱ ቅዱስነታቸው በሐዋርያዊ መልእክታቸው አክለው ገልጸዋል።

የተወደደ ፣ ርህሩህ ፣ ታዛዥ አባት

ቅዱስ ዮሴፍ በእውነቱ “የእርሱን አባትነት በግልጽ አሳይቷል” ይህንንም ያሳየው ራሱን ለቤተሰቡ በፍቅር በማቅረብ “በቤቱ ውስጥ በጥበብ እያደገ ለሄደው መሲህ አገልግሎት የተሰጠ ፍቅር ነው” በማለት የቀድሞው ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ ስለ ቅዱስ ዮሴፍ መናገራቸውን በመጥቀስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በእዚህ ሐዋርያዊ መልእክታቸው አክለው ገልጸዋል።

እናም “በብሉይ እና በአዲስ ኪዳን መካከል ባለው መንታ መንገድ” ላይ ሚና ስለነበረው ቅዱስ ዮሴፍ “በክርስቲያኖች ዘንድ ሁል ጊዜ እንደ አባት ተከብሯል” (አንቀጽ ቁ. 1) በማለት ይህ ሐዋርያዊ መልእክት ይገልጻል። በእርሱ ውስጥ  “ድክመታችንን እንድንቀበል የሚረዳን ኢየሱስ እግዚአብሔርን በርህራሄ የተሞላ ፍቅር አየ” ምክንያቱም በብዙ ፍርሃቶች ፣ ድክመቶች እና ውድቀቶች ቢኖሩብንም እንኳን አብዛኞቹ በእርሱ መለኮታዊ እቅዶች ውስጥ የሚገኙ በመሆናቸው እርሱ አያሳፍረንም የሚል እንድምታ የያዙ አንቀጾች የሚገኙበት ሐዋርያዊ መልእክት ነው። “ከከሳሾቹ ወጥመዶች የሚያድነን ርህራሄ ፍቅር ብቻ ነው” በማለት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በእዚህ ሐዋርያዊ መልእክታቸው የገለጹ ሲሆን በተለይም “እውነቱን እና ርህራሄውን የምንለማመደው” የእግዚአብሔርን ምህረት የእርቅ ምስጢር በሆነው በምስጢረ ንስሃ አማካይነት ብቻ ነው-ምክንያቱም “እግዚአብሔር እውነት መሆኑን እናውቃለን አያወግዘንም ነገር ግን ይልቁኑ ይቀበለናል፣ ይቀርበናል ፣ ይደግፈናል እንዲሁም ይቅር ይለናል ”(አንቀጽ ቁ. 2) የሚሉ ጭብጦች በሐዋርያዊው መልእክቱ ውስጥ በስፋት ተገልጿል።

ቅዱስ ዮሴፍ እግዚአብሔርን በሚገባ ይታዘዝ የነበረ አባት ነው - በእሽታው አማካኝነት ማርያምን እና ኢየሱስን በመንከባከብ እንዲሁም ልጁ “የአባቱን ፈቃድ እንዲፈጽም” ያስተምረው ነበር። የኢየሱስን ተልእኮ እንዲያገለግል በእግዚአብሔር የተጠራው  ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እንደተናሩት “በእውነትም የመዳን ታሪክ አገልጋይ ነው” (አንቀጽ ቁ.3) በማለት “በደህንነት ታሪክ ታላቅ ምስጢር ውስጥ ተባባሪ” (አንቀጽ ቁ. 3) ነበር በማለት ይገልጻል።

የእግዚአብሔርን ፈቃድ መቀበል

በተመሳሳይ መልኩም ቅዱስ ዮሴፍ “ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ማርያምን ስለተቀበላት ተቀባይ የሆነ አባት” ነው  ምክንያቱም  - ዛሬም ቢሆን አስፈላጊ የሆነው ምልእክት ይህ እንደሆነ የገለጹት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በእዚህ ሐዋርያዊ መልእክት ውስጥ እንደ ተናገሩት “በሴቶች ላይ የስነልቦና ፣ የቃል እና የአካል ጥቃቶች በግልጽ በሚታዩበት በዚህ ዓለም ውስጥ” የቅዱስ ዮሴፍን ታሪክ ማሳትወስ ተገቢ ነው ብለዋል። ነገር ግን የማርያም እጮኛ የነበረው ቅዱስ ዮሴፍ እንዲሁ በጌታ በመተማመን በሕይወቱ ሊኖሩ የማይገባቸውን ክስተቶች እንኳን የሚቀበል ፣ “የራሱን ሀሳብ ወደ ጎን በመተው” እና እራሱን ከራሱ ታሪክ ጋር የሚያስታርቅ ቅዱስ እንደ ነበረ በስፋት ተገልጿል።

የቅዱስ ዮሴፍ መንፈሳዊ ዳራ ወይም ጎዳና “በቃል ብቻ የሚገልፅ አይደለም፣ ነገር ግን ሁኔታዎችን የሚቀበል ነው” ይህ ማለት ደግሞ “እሱ ስልጣኑን ለቀቀ” ማለት አይደለም። ይልቁንም እሱ “በድፍረት እና በንቃት ይጠባበቅ ነበር” ምክንያቱም “በመንፈስ ቅዱስ የፅናት ስጦታ” እና በተስፋ በመሞላት በሁሉም ተቃርኖዎች ፣ ተስፋ መቁረጦች እና ብስጭቶች” ውስጥ የነበረ ቢሆንም እንኳን ህይወቱን እንዳለ ተቀብሎታል። በቅዱስ ዮሴፍ አማካይነት እግዚአብሔር በተግባር “አትፍሩ!” የሚለን ሲሆን ምክንያቱም “እምነት ለደስታ ሆነ ለሐዘን ለእያንዳንዱ ክስተት ትርጉም ይሰጣል” እንዲሁም “እግዚአብሔር ድንጋያማ ከሆነ መሬት ውስጥ አበባ እንዲበቅል ማድረግ ይችላል” እንድንል ያደርገናል የሚሉ ጭብጦች በእዚህ ሐዋርያዊ መልእክት ውስጥ ተካተዋል። ቅዱስ ዮሴፍ “አቋራጭ የሆኑ መንገዶችን አልፈለገም ነበር፣ ነገር ግን በእውነተኛ ዓይን ነገሮችን ፊት ለፊት ተጋፈጠና እሱ የግል ሀላፊነትን ተቀበለ”።  በዚህ ምክንያት “ያለምንም ልዩነት ሌሎችን እንደነሱ እንድንመለከት እና እንድንቀበል እንዲሁም ለደካሞች ልዩ በሆነ መልኩ አሳቢ መሆናችንን እንድናሳይ ያበረታታናል” (አንቀጽ ቁ.4) እንደ ተጠቀሰው።

በድፍረት የተሞላ፣ የፍቅር ማስሌ የሆነ አባት

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በላቲን ቋንቋ “Patris corde” በአማርኛው በግርድፉ ሲተረጎም “የአብ ልብ” በሚል አርእስት በቅርቡ ያፋ ባደረጉት ሐዋርያዊ መልእክት የቅዱስ ዮሴፍን “በፈጠራ ችሎታ የተሞላ ድፍረትን” ጎላ አድርገው አሳይተዋል፣ “በተለይም ችግሮች በሚያጋጥሙን ወቅት ችግሮችን እንዴት መቋቋም እንደ ምንችል መንገዱን የሚገልጥልን ነው”። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በእዚህ ሐዋርያዊ መልእክታቸው አክለው እንደ ገለጹት “የናዝሬቱ አናጺ” በመለኮታዊ ጥበቃ በመተማመን አንድ ችግርን ወደ አዲስ አጋጣሚ መለወጥ ችሏል። በቤተሰቡ ውስጥ ያጋጠሙት “ተጨባጭ ችግሮች” በዓለም ላይ ያሉ ሌሎች ቤተሰቦች በተለይም ደግሞ ስደተኛ የሆኑ ቤተሰቦች ችግሮቻቸውን እንዴት መቋቋም እንደ ሚችሉ ትምህርት የሰጠ ክስተት እንደ ሆነ አክለው ገልጸዋል።

ከዚህ አንፃር ቅዱስ ዮሴፍ “በጦርነት ፣ በጥላቻ ፣ በስደት እና በድህነት ምክንያት የትውልድ አገራቸውን ለቀው እንዲወጡ የተገደዱት ሁሉ ልዩ ረዳታቸው ነው” ብለዋል። የኢየሱስ እና የማሪያም ጠባቂ እንደመሆኑ መጠን ቅዱስ ዮሴፍ የእናትነት እና የክርስቶስ አካል ምስል የሆነችው “የቤተክርስቲያኗ ጠባቂ”  ካልሆነ በስተቀር ሌላ ነገር ሊሆን አይችልም።  “ስለሆነም  ሁሉም ድሆች ፣ ችግረኞች ፣ በመከራ ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ወይም የሚሞቱ ሰዎች ፣ ሁሉም እንግዶች ፣ ሁሉም እስረኞች ፣ አቅመ ደካሞች ሁሉ ቅዱስ ዮሴፍ ጥበቃ የሚያደርግላቸው” ሰዎች ናቸው። “ከቅዱስ ዮሴፍ” አሉ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሐዋርያዊ መልእክታቸው “እኛ ቤተክርስቲያንን እና ድሆችን መውደድ መማር አለብን” (አንቀጽ ቁ. 5) ብለዋል።

የሥራ ዋጋን ፣ ክብርን እና ደስታን የሚያስተምር አባት

ቅዱስ ዮሴፍም “ለቤተሰቡ የሚያስፈልገውን ለማሟላት በሐቀኝነት የሠራ አናጺ” የነበረ ሰው ሲሆን እርሱም “ደግሞም የራሳችን ድካም ፍሬ የሆነውን እንጀራ መብላት ምን ያህል ዋጋ እንዳለው፣ ክብርና ደስታ እንደ ሚሰጥ” ያስተምረናል በማለት የሚገልጹ ጭብጦች ተካተውበታል። ይህ የቅዱስ ዮሴፍ የባህርይ ገጽታ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ እንዳሉት  በተወሰነ ደረጃ ደህንነታቸው በተጠበቀ ሀገሮች ውስጥ እንኳን “አስቸኳይ ማህበራዊ ጉዳይ” የሆነው ሥራን የሚደግፍ አቤቱታ ለማቅረብ እድል ይሰጣቸዋል በማለት የገለጹ ሲሆን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ አክለው እንደ ገለጹት “የተከበረ ሥራን አስፈላጊነት የማድነቅ አዲስ ፍላጎት አለ ፣ ከእነዚህም ውስጥ ቅዱስ ዮሴፍ አርአያ የሚሆን ረዳታችን ነው” ብለዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ሥራ  “በደህንነት ምስጢር  ውስጥ ለመሳተፍ ፣ የመንግሥቱን መምጣት ለማፋጠን ፣ ችሎታዎቻችንን እና ክህሎቶቻችንን ለማዳበር እና በህብረተሰብ እና በወንድማማች ኅብረት ውስጥ ለማገልገል የሚያስችል አጋጣሚ ነው” እንደ ሆነ ገልጸዋል። የሚሰሩ ሰዎች “ከእራሱ ከእግዚአብሄር ጋር በመተባበር እና በሆነ መንገድ በዙሪያችን ያለው ዓለም ፈጣሪዎች ይሆናሉ” ሲል ገልጸዋል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደ ገለጹት አዲስ መደበኛ ሁኔታዎችን መልሶ ለማምጣት ይችላ ዘንድ “ሁሉም ሰው የሥራን ዋጋ ፣ አስፈላጊነት እና ጠቃሚነት እንደገና እንዲያሳውቁ” በእዚህ ሐዋርያዊ መልእክት ያበረታታሉ። በተለይም በኮቪ -19 በተስፋፋው ወረርሽኝ ምክንያት እየሰፋ ከመጣው የሥራ አጥነት አንጻር ሊቃነ ጳጳሳቱ ሁሉም ሰዎች “ቅድሚያ የምሰጧቸውን ነገሮች መልሰው እንዲገመግሙ” እንዲሁም ማንም ወጣት ፣ ማንም ሰው ፣ ቤተሰብ ያለ ሥራ መቆየት እንደሌለባቸው ጽኑ እምነታቸውን እንዲገልጹ ጥሪ አቅርበዋል! (አንቀጽ ቁ. 6)

እንደ አባት በማርያምና ​​በኢየሱስ ላይ ያተኮረ ነበር

ከአባትነቱ ጥላ ፍንጭ በመውሰድ  የፖላንዳዊው ጸሐፊ ጃን ዶብራኪንስኪ መጽሐፉ ውስጥ የጠቀሰውን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዋቢነት የገለጹ ሲሆን ቅዱስ ዮሴፍ የኢየሱስ አባት መሆኑን  “የሰማያዊ አባት ምድራዊ ጥላ” በማለት ገልፀዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ አክለው በሐዋርያዊ መልእክታቸው እንደ ገለጹት “አባቶች አልተወለዱም ፣ ነገር ግን የተፈጠሩ ናቸው” ብለዋል። አንድ ሰው ልጁን ወደ ዓለም በማምጣቱ ብቻ አባት ሊሆን አይችልም፣ ነገር ግን ያንን ልጅ የመንከባከብ ኃላፊነት በመወጣት ጭምር ነው አባትነቱን ሊያረጋግጥ የሚችለው ብለዋል። እንደ አለመታደል ሆኖ በዛሬው ህብረተሰብ ውስጥ ልጆች “ብዙውን ጊዜ ሕይወትን እና እውነታን የሚያስተምሯቸው ወላጆችን በማጣታቸው የተነሳ ወላጅ አልባ ሆነው ሲኖር ይታያሉ። ልጆች አሉ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ልጆች እንደሚሉት እነሱን ለመቆጣጠር የማይሞክሩ አባቶችን ይፈልጋሉ፣ ይልቁንም “እራሳቸውን የመወሰን ፣ ነፃነትን የማጣጣም እና አዳዲስ ዕድሎችን የመፈለግ ችሎታ” እንዲኖራቸው አሳዳጊ ወላጆች ያስፈልጓቸዋል ብለዋል።

ይህ ቅዱስ ዮሴፍ  “በጣም ንፁህ” አባት ተብሎ የተገለጸበት ስሜት ሲሆን”  ይህም የበላይ ሆኖ መግዛት ከሚለው ሐሳብ በተቃራኒ ጎራ የሚገኝ ነው። ቅዱስ ዮሴፍ አሉ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “ልዩ በሆነ ነፃነት እንዴት መውደድ እንደሚቻል ያውቅ ነበር። እሱ ራሱን የነገሮች ማዕከል በጭራሽ አላደረገም። እሱ ስለራሱ አላሰበም፣ ይልቁንም በማርያምና ​​በኢየሱስ ሕይወት ላይ አተኩሯል” የሚሉ አንቀጾች ይንጸባረቁበታል።

ቅዱስ ዮሴፍ የነበረው ደስታ እውነተኛ በሆነ መልኩ ራስን ስጦታ አድርጎ ማቅረብን ያካተተ ነበር፤ “በእርሱ ውስጥ መቼም ቢሆን ብስጭትን አናይም፣ ነገር ግን መተማመንን ብቻ ነው የምንመለከተው” ሲሉ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በእዚህ ሐዋርያዊ መልእክታቸው ገልጸዋል። በትዕግሥት ያሳየው ዝምታ ተጨባጭ የመተማመን መግለጫዎች ቅድመ ዝግጅት ነበር። ስለሆነም ቅዱስ ዮሴፍ “አባቶችን በሚፈልግ” በዛሬው የአባገነንነት መንፈስ በሚታይበት አለማችን ውስጥ በተለይም በእኛ ጊዜ አርአያ የሆነ ምሳሌ ሆኖ ጎልቶ ይታያል፣ “ስልጣን ከአምባገነንነት፣ አገልግሎት ከአገልጋይነት ፣ መወያየት ከጭቆና ጋር ማያያዝ ፣ በጎ አድራጎትን ከድህነት አስተሳሰብ ጋር፣ ኃይልን ከጥፋት ጋር በማዝመድ ግራ የሚጋቡትን የማህበረሰብ” ክፍሎች የቅዱስ ዮሴፍ ሕይወት ምሳሌ ይሰጣቸዋል።

እውነተኛ አባቶች በምትኩ “ስለ ልጆቻቸው ሲሉ የራሳቸውን ሕይወት ለመኖር እምቢ ይላሉ” ይልቁንም ነፃነታቸውን ያከብራሉ። በዚህ አባባል ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ እንደ ገለጹት አንድ አባት “ልጆቹ በእርሱ ላይ ጠግኛ መሆናቸውን እና ማንም ሰው ሳያጅባቸው በሕይወት ጎዳናዎች ላይ መጓዝ የማችሉ መሆናቸውን የሚረዳ ከሆነ እርሱ ትክክለኛ አባት ነው በማለት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በአጽንኦት ገልጸዋል፣ አባት መሆን ማለት “ከንብረት ጋር ምንም ግንኙነት የለውም ፣  ይልቁንም ወደ ታላቅ አባትነት “የሰማይ አባት” የሚጠቁም‘ ምልክት ’ነው”  (አንቀጽ ቁ.7) ብለዋል።

ለቅዱስ ዮሴፍ የሚደረግ ዕለታዊ ጸሎት

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በሐዋርያዊ መልእክታቸው መደምደሚያ ላይ እንደ ገለጹት “ከአርባ ዓመት በላይ በየቀኑ የጠዋት ጸሎት በሚያደርጉበት ወቅት ለቅዱስ ዮሴፍ የሚደረገው እና  በአስራ ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን የነበረው በፈረንሳይኛ ቋንቋ የተጻፈ የፀሎት መጽሐፍ የተወሰደ የኢየሱስ እና የማርያም ማሕበር አባላት ጸሎት ይጸልዩ” እንደ ነበረ ተናግረዋል። ይህ ጸሎት አሉ ቅዱስነታቸው አምልኮ እና መተማመንን ይገልጻል፣ አልፎ ተርፎም ቅዱስ ዮሴፍ የገጠመውን ፈታኝ ሁኔታ ይገልጻል፣ በማጠቃለያ ቃላቱ ጸሎቱ እንድህ ይላል “የምወድህ አባቴ ፣ መተማመኔ ሁሉ በአንተ ላይ ነው። እያንዳንዱን ነገር ማድረግ ስለቻልኩኝ አንተን በከንቱ ጠርቼሃለሁ አይባልም፣ እናም ሁሉንም ነገር በኢየሱስ እና በማሪያም ማድረግ ስለምትችል፣ መልካምነትህ እንደ ኃይልህ ታላቅ መሆንህን ያሳየኝ” የሚለውን ጸሎት ለባለፉት 40 አመታት ያህል በእየቀኑ መድገማቸውን ቅዱስነታቸው በሐዋርያዊ መልእክታቸው ገልጸዋል።

በሐዋርያዊ መልእክታቸው ማጠቃለያ ላይ ለቅዱስ ዮሴፍ ሌላ አዲስ ጸሎት አክለዋል፣ ሁላችንም አብረን እንድንጸልይ ቅዱስነታቸው ያበረቱናል። እንዲህም ይላል . . .

የአዳኙ ጠባቂ ፣ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም እጮኛ።

እግዚአብሔር አንድያ ልጁን ለአንተ በአደራ ሰጠ፣

ማርያም በአንተ ላይ መተማመኗን አደረገች፣

ከእናንተ ጋር ክርስቶስ ሰው ሆነ።

የተባረክ ቅዱስ ዮሴፍ ሆይ ለእኛም ራስህን እንደ አባት አድርገህ አሳየን፣

 በሕይወት ጎዳና ላይ ምራን።

እኛ ጸጋን ፣ ምህረትን እና ብርታትን እንድናገኝ አድርገን ከክፉም ሁሉ ጠብቀን።

አሜን!

09 December 2020, 13:58