ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ እ.አ.አ በተገባደደው በ2020 ዓ.ም ያከናወኑት አበይት ተግባራት

በታኅሳስ 22/2013 ዓ.ም በምገባደደው የጎርጎሮሳዊያኑ 2020 ዓ.ም ውስጥ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ያከናወኗቸውን አብየት ተግባራት በመዳሰስ እንደ ሚከተለው ወደ እናንተ እናቀርባለን፣ ተከታተሉን። የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የማሕበርሰብ ክፍሎች ዘንድ ይህ በታኅሳስ 22/2013 ዓ.ም የምገባደደው የ2020 ዓ.ም በዓለም ዙሪይ ከፍተኛ ውጥረት የነገሰበት አመት እንደ ነበረ የሚታወቅ ሲሆን በተለይም ደግሞ በኮቪድ 19 (የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ) ምክንያት የዓለማችን ሕዝቦች ለከፍተኛ ሞት፣ ችግር፣ ሥራ አጥነት የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ ወዘተ ለመሳሰሉ ችግሮች ሰላባ መሆናቸው ይታወቃል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ይህ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በተንሰራፋበት በእዚህ የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የማሕብረሰብ ክፍሎች ዘንድ በመገባደድ ላይ በሚገኘው 2020 ዓ.ም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ይህንን ችግር በጸሎት ኃይል መጋፈጥ እንዲቻል የራሳቸውን ጥረት ማደረጋቸው የሚታወስ ሲሆን በኮቪድ -19 ምክንያት በዓለም አቀፍ ደረጃ በጤና ላይ ከፍተኛ አደጋ በተጋረጠበት የአውሮፓዊያኑ 2020 ዓ.ም ዓለምአቀፍ እንቅሰቃሴ እንዲገታ በተደረገበት በእዚህ ወቅት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ሁልጊዜም ለጸሎት ኃይል ምስጋና በማቅረብ በጋራ ችግሮችን መጋፈጥ እንደ ሚቻል ያላቸውን እምነት የገለጹበት አመት ነበር።

ይህን ዝግጅት ለማዳመጥ ከእዚህ ቀጥሎ ያለውን "ተጫወት" የሚለውን ምልክት ይጫኑ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በመጋቢት 29/2012 ዓ.ም እሁድ እለት ከቫቲካን በቀጥታ የቪዲዮ መልእክት ባስተላለፉበት ወቅት በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የመጀመርያው በቤት ውስጥ የመቆየት አስገዳጅ ሕግ በታወጀበት ወቅት ወረርሽኙን ለመከላከል በማሰብ የተሰመረው ቀይ የመለያያ መሥመር በተመለከተ መናገራቸው ይታወሳል።  በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት የተጫነብን ከቤት አለመውጣት አስቸኳይ ህግ የማይቀር ጉዳይ እንደ ሆነ ገልጸው ነበር። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በወቅቱ “የእግዚአብሔር መልአክ ማርያምን ያበሰረበት ጸሎት” ከደገሙ በኋላ  “ይህ ዛሬ የእግዚአብሔር መልአክ ማርያምን ያበሰረበትን ጸሎት የምናደርገው እንግዳ በሆነ መልኩ ነው፣ እናተ ታዩኛላችሁ፣ እኔም ግን አላያችሁም፣ በጸሎቴ ከእናንተ ጋር ነኝ” ማለታቸው ይታወሳል።

ልማዳዊ በሆነ መልኩ አንድ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘወትር እሁድ እለት በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ በእለቱ ቅዱስ ወንጌል ላይ የሚያደርጉትን አስተንትኖ እና የእግዚአብሔር መልአክ ማርያምን ያበሰረበት “የብስራተ ገብርሄል ጸሎት” ለመድገም በርካታ መንፈሳዊ ነጋዲያን፣ ምዕመናን እና የአገር ጎብኚዎች በቫቲካን እንደ ሚገኙ ይታወቃል። ነገር ግን ከመጋቢት 29/2012 ዓ.ም ጀመሮ በመላው አለም በተለይም በጣሊያን ተንሰራፍቶ በነበረው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ሕዝቡ ከቤት አንዳይወጣ በሚደነግገው አስገዳጅ ሕግ ምክንያት በቫቲካን የሚገኘው የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ጭር ብሎ መቆየቱ ይታወሳል።

የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ የዓብይ ጾም ወቅት ጊዜ ዓርብ መጋቢት 18/2012 ዓ.ም የመስቀል መንገድ በሚደረግበት ወቅት በኢትዮጵያ የሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ 2 ሰዓት ላይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ደጃፍ ላይ ሆነው ወደ ቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ በመመልከት ጸሎታቸውን አሳርገዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የዓለማችን ስጋት የሆነው ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እንዲቆም በማለት ወደ እግዚአብሔር ጸሎት አቅርበው ነበር። የሰው ልጅ በሙሉ ከሚገኝበት ፈተና መውጣት እንዲችል ምዕመናን በጽኑ እምነት ተስፋን በመያዝ ሕይወታቸውን አንዲገፉ ጥሪ አቅርበው ነበር። ቅዱስነታቸው በተመሳሳይ ቀን ዓርብ መጋቢት 18/2012 ዓ. ም. በኢትዮጵያ የሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ 2:00 ላይ፣ ከሮም ከተማ እና ከመላው የዓለም ሕዝብ ጋር በመንፈስ አንድ በመሆን እና መተባበር የቅዱስ ቁርባን ቡራኬ ጸሎት አቅርበው “ከቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ደጃፍ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቡራኬ ይድረሳችሁ” በማለት ቡራኬ መስጠታቸው ይታወሳል።

ቅዱስነታቸው አክለውም ምዕመናን ሰብዓዊ ፍራቻ እንዳይኖራቸው እና በጌታ ማመናቸውን እንዲቀጥሉ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል፣ እንዲህም ብለው ነበር “እኛ መልህቅ አለን፣ መልህቃችን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ነው፣ በመስቀሉ ድነናል፣ እኛ መሪ አለን በመስቀሉ ተዋጅተናል። እኛ ተስፋ አለን በመስቀሉ ውስጥ ምንም እና ማንም ከቤዛው ፍቅሩ እንዳይ እንድንፈወስ እና እንድንታቀፍ አድርጎናል” ማለታቸው ይታወሳል።

የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ፣ ጸሎት ፣ ፈውስ እና ብፅዕና ላይ ያተኮሩ ነበሩ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዘወትር ረቡዕ እለት በቫቲካን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እንደ ሚያደርጉ ይታወቃል። በወቅቱ በከፍተኛ ደረጃ በተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በቤት ውስጥ የመቀመጥ እና ከቤት ያለመውጣት አስገዳጅ ሕግ ምክንትያ ቅዱስነታቸው ላልተወሰን ጊዜ ዘወትር ረቡዕ እለት የሚያደርጉትን የጠቃላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ አቋርጠው ነበር።

በመጀመርያ ደረጃ ከጥር እስከ የካቲ ወር 2012 ዓ.ም ደረስ በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ አምስት ላይ በተጠቀሰው እና ኢየሱስ በተራራው ላይ በሰበከው ስብከት ጭብጥ ዙሪያ ላይ በተከታታይ የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ማድረጋቸው ይታወሳል። “ምሕረት የሚያደርጉ ብፁዓን ናቸው፤ ምሕረትን ያገኛሉና በዚህ የተራራው ስብከት ክፍል ውስጥ አንድ ልዩ የሆነ ነገር አለ፣ ይህም ብቸኛው የደስታ ምንጭ ምህረት ማደረግ እንደ ሆነ ይናገራል። ምህረት የማደረግ ተመክሮ ያላቸው ሰዎች እነርሱም በፊናቸው ምሕረት ያገኛሉ። የይቅር ባይነት ዋና ገጽታ በዚህ የተራራው ላይ ስብከት ውስጥ የተገለጸ ብቻ ሳይሆን፣ ነገር ግን በተለያየ የቅዱስ ወንጌል ክፍል ላይ በተደጋገሚ ተገልጹዋል። ደግሞስ እንዴት ሊሆን ይችላል? ምሕረት የእግዚአብሔር ልብ ነው!” ማለታቸው ይታወሳል።

በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ከነሐሴ ወር መግቢያ ጀምሮ “ዓለምን መፈወስ” በሚል ጭብጥ ዙሪያ በተከታታይ የሚሰጥ የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ መጀመራቸው የሚታወስ ሲሆን በተለይም ረቡዕ ዕለት በነሐሴ 13/2012 ዓ.ም ላይ ባደረጉት አስተምህሮ  የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ክትባት የማግኘት አስፈላጊነት በማስታወስ “የኮቪድ 19 ቫይረስ ለመከላከል የሚሰጠው ክትባት ቅድሚያ የሚሰጣቸው ሐብታም የሆኑ አገሮች ከሆኑ፣ ይህ ክትባት የዚህ ወይም የዚያ ብሔር ንብረት ከሆነ እና ዓለም አቀፋዊ ካልሆነ፣ ለሁሉም የሰው ልጆች የማይዳረስ ከሆነ በጣም ያሳዝናል” ማለታቸው ይታወሳል። “የበሽታው ወረርሽኝ ከሁሉም በላይ የእኩልነት ተግዳሮት የሆኑትን ማህበራዊ ችግሮች አጋልጧል እንዲሁም አስከፊ እንደ ሆኑ አሳይቷል። አንዳንድ ሰዎች በቤታቸው ሁነው ሊሠሩ ይችላሉ ፣ ይህ ግን ለብዙዎች የማይቻል ነው። የተወሰኑ ልጆች ምንም እንኳን የተሳትፎ ችግሮች ቢኖሩም ፣ መደበኛ ትምህርት ማግኘታቸውን ሊቀጥሉ ይችላሉ ፣ ይህ ግን በአጋጣሚ ለብዙዎች በድንገት የተከሰተ ወረርሽኝ በመሆኑ ብዙዎች እድሉን ለማግኘት ይቸገራሉ። አንዳንድ ኃያላን አገራት ቀውሱን ለመቋቋም ገንዘብ መስጠት ይችላሉ ፤ ይህ ግን የወደፊቱን ማሕበረሰብ ባለ እዳ ያደርጋል” ማለታቸው ይታወሳል።

በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ ከጥቅምት ወር 2013 ዓ.ም ጀምሮ በጽሎት ዙሪያ ላይ በተከታታይ ያደረጉትን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ በአዲስ መልክ ጀምረው እንደ ነበረ የሚታወስ ሲሆን “ጸሎት የእምነት እስትንፋስ ነው” ማለታቸው ይታወሳል። ይህም በጣም ትክክለኛ የሆነ አገላለፅ ነው። ጸሎት “በእግዚአብሔር ከሚያምኑና እና ከሚታመኑ ሰዎች ልብ እንደሚወጣው ጩኸት ነው፣ ጸሎት ዓለምን ይፈውሳል” ማለታቸው ይታወሳል፣ “ያዕቆብ ከእግዚአብሔር ጋር ያደርገው ትግል የጸሎት ተምሳሌት ነው” ማለታቸው ይታወሳል።

በአጠቃላይ በእዚህ በተገባደደው የጎርጎሮሳዊያኑ 2020 ዓ.ም ውስጥ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በተለያዩ ጭብጦች ዙሪያ ላይ በአጠቃላይ 46 የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮዋኦችን ማደረጋቸው ይታወሳል።

የብስራተ ገብርኤል ጸሎት

በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አክብሮ በመስጠት ከሚደረጉ ጸሎቶች መካከል የእግዚአብሔር መልአክ ማርያምን ያበሰረበት “የብስራተ ገብርኤል” ጸሎት አንዱ እንደ ሆነ የሚታወቅ ሲሆን በማስከተ በፋሲካ በዓል ወቅት አንስቶ እስከ በዓለ አምሳ ወይም ጴራቅሊጦስ ድረስ የሚደገመው “የሰማይ ንግሥት ሆይ ደስ ይበልሽ” የተሰኘው ጸሎት ደግሞ ሁለተኛው ነው። በእዚህም መሰረት የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የማሕበረሰብ ክፍሎች ዘንድ በተገባደደው በ2020 ዓ.ም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ እነዚህን “የብስራተ ገብርኤል” ጸሎት እና እንዲሁም “የሰማይ ንግሥት ሆይ ደስ ይበልሽ” የተሰኙትን ጸሎቶች ዘወትር እሁድ እና በታላላቅ መንፈሳዊ በዓላት ወቅት 58 ጊዜ ከምዕመና ጋር በመቀባበል መድገማቸው ተገልጿል።

ቅዱስነታቸውን እነዚህን ጽሎቶች ከደገሙ በኋላ በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ በተለይም በከፍተኛ ደረጃ በሰው ሰራሽ እና በተፈጥሮ አደጋዎች የተነሳ ችግር ውስጥ የሚገኙ የማሕበረሰብ ክፍሎችን በተመለከተ መልእክት እንደ ሚያስተላልፉ የሚታወቅ ሲሆን በተለይም ደግሞ በሐምሌ 12/2012 ዓ.ም “የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ፍጻሜውን የሚገልጽ ምልክቶች በማይታዩበት በዚህ ዘመን በበሽታው ለሚሰቃዩ ሁሉ እንዲሁም በኢኮኖሚያዊ እና በማህበራዊ ችግሮች ምክንያት ለሚሰቃዩ ሁሉ ቅርብ መሆኔን ማረጋገጥ እፈልጋለሁ” ማለታቸው ተገልጿል። “በተለይም በጦርነቶች እና በግጭት ሁኔታዎች የተነሳ እየተሰቃዩ ለሚገኙ ሰዎች ሐሳቤ ከእነርሱ ጋር እንደ ሆነ ለመግልጸ እፈልጋለሁ” በማለት መልእክታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው “በቅርቡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባስተላለፈው ውሳኔ መሠረት አስፈላጊውን የሰብአዊ ርዳታ ለመስጠት አስፈላጊ የሆኑትን ሰላምና ደህንነት ማስገኘት በሚችል መልኩ በዓለም አቀፍ ደረጃ አስቸኳይ የተኩስ አቁም አማጅ እንዲተገበር በድጋሜ እጠይቃለሁ” ማለታቸው ይታወሳል።

በቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት የተደርገው መስዋዕተ ቅዳሴ

በእዚህ በተገባደደው የጎርጎሮሳዊያኑ 2020 ዓ.ም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በቫቲካን በሚገኘው የቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት ከመጋቢት 9 እስከ 18/2012 ዓ.ም በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ምዕመናን ወደ ቤተክርስቲያን መምጣት ባለመቻላቸው ምክንያት እርሳቸው ያሳረጓቸው መስዋዕተ ቅዳሴዎች በቀጥታ በቪዲዮ የተላለፉ መሆናቸው ይታወሳል። በእያንዳንዱ መስዋዕተ ቅዳሴ መግቢያ ላይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ለተለያዩ የማሕበረሰብ ክፍሎች ማለትም ህመምተኞች፣ ከእዚህ ዓለም በሞት ለተለዩ ሰዎች፣ የጤና ባለሙያዎች፣ በማረምያ ቤት ለሚገኙ ሰዎች፣ አዛውንቶች፣ ቤተሰቦች፣ ወረርሽኙ ሳይበግራቸው በሥራ ላይ ለነበሩ ሰዎች፣ አርቲስቶች እና እንዲሁም ለቤተክርስቲያን አባቶች እና የመንግሥት ባለስልጣናት ሳይቀር ወረርሽኙን ለመግታት ይችላ ዘንድ አስፈልጊውን እና ከባድ ምርጫዎች ገቢራዊ እንዲሆኑ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል። የመጨረሻው በቀጥታ ስርጭት የተላለፈው መስዋዕተ ቅዳሴ አየር ላይ የዋለው በግንቦት 18/2012 ዓ.ም ጠዋት ላይ ነበር። ያ ቀን የቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ መቶኛ አመት የልደት በዓል የተከበረበት እለት የነበረ ሲሆን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ሕይወት ውስጥ ሦስት መሰረታዊ ነገሮችን እናገኛለን ያሉ ሲሆን እነዚህም  “የመልካም እረኛ ዱካዎች - ጸሎት ፣ ለሰዎች ቅርበት መሆን፣ ለፍትህ እና ፍቅር መሥራት” የሚሉት እንደ ነበሩ መናገራቸው ይታወሳል።

ሁላችንም "ወንድሞች ነን"

የሰው ልጅ የነበረውን ማህበራዊ ሕይወት የሚለያይ አስገዳጅ በሆነ መልኩ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በተከሰተው ማሕበራዊ ርቀት በከፍተኛ ሁኔታ በተንጸባረቀበት በተገባደደው የጎርጎሮሳዊያኑ 2020 ዓ.ም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ “ሁላችንም ወንድማማቾች ነን” በሚል አርእስት ሦስተኛውን ጳጳሳዊ መልእክት እ.ኤ.አ. በጥቅምት 4 /2020 ዓ.ም ይፋ ማደረጋቸው ይታወሳል። ይህ በጣሊያነኛ ቋንቋ “fratelli tutti” ሁላችንም ወንድማማቾች ነን የተሰኘው ጳጳሳዊ መልእክ አጠቃላይ ይዘቱን እንደሚከተለው አናቀርብላችኋለን ተከታተሉን።

1.     አጠቃልይ መረጃ

“ሁላችንም ወንድማማቾች ነን” በሚል አርእስት በወንድማማችነት እና ማሕበራዊ ወዳጅነት ላይ ያተኮረ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ጳጳሳዊ መልእክት ነው።

ስለምን ይናገራል?

·        በላቲን ቋንቋ “Lumen fidei” (የእምነት ብርሃን)በሚል አርእስ (እ.አ.አ 2013) ይፋ ካደረጉት ጳጳሳዊ መልእክት በመቀጠል በላቲን ቋንቋ “Laudato si” ወዳሴ ለአንተ ይሁን በሚል አርእስት እ.አ.አ በኝቦት 24/2015 ዓ.ም ያፋ ካደረጉት ጳጳሳዊ መልእክት በመቀጠል በሦስተኛ ደረጃ ይፋ የሆነ ጳጳሳዊ መልእክት ነው።

·        በይፋ ለንባብ የበቃው እ.አ.አ በጥቅምት 03/2020 ዓ.ም አዚዚ በሚባል የጣሊያን ከተማ ውስጥ ነው።

በምን ላይ የተመሠረተ ነው?

·        ወንድማማችነት እና ማህበራዊ ወዳጅነትን በተመለከተ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳትን ያሳሰባቸው ጥያቄዎች የተመለከተ ነው። (አንቀጽ 5)

·        ጳጳሳዊ መልእክቱ እ.ኤ.አ. በየካቲት ወር 2019 ዓ.ም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ከታላቁ ኢማም  አህመድ አል-ታይየብ ጋር በጋራ የተፈራረሙትን “የሰው ልጅ ወንድማማችነት ለዓለም ሰላም እና አብሮ ለመኖር” በሚል ሰነድ ላይ ያጠነጠነ ነው። (አንቀጽ 5)

ምን ዓይነት ሐሳብ ያቀርብልናል?

·        ወንድማማችነት እና ማህበራዊ ወዳጅነት ላይ ትኩረቱን ያደረገ ጳጳሳዊ መልእክት ነው። (አንቀጽ 2፣6)

·        የወንድማማችነት ፍቅር ዓለም አቀፍ ይዘት ያለው መመሪያ እንደ ሆነ ይገልጻል። (አንቀጽ 6)

·        ዓላማው የወንድማማችነት እና ማህበራዊ ወዳጅነት አዲስ ራዕይ ማምጣት ነው። (አንቀጽ 6)

·        እንደ አንድ ሰብዓዊ ቤተሰብ እና አንድ ሥጋ መሆናችንን ተረድተን አብረን የምንጓዝ መንገደኞች እንድንሆን ያበረታታናል። (አንቀጽ 8)

መልእክቱ ማንን ይመለከታል?

·        ይህንን አስተንትኖ ለሚቀበሉ ሰዎች ሁሉ ውይይት ለማደረግ የቀረበ ጥሪ ነው። (አንቀጽ 6)

ርእሱ ከየት ነው የተወሰደው? (አንቀጽ 1)

● ሁላችንም ወንድማማቾች ነን በላቲን ቋንቋ “ፍራቴሊ ቱቲ” የአዚዚው የቅዱስ ፍራንቸስኮስ አገላለጽ (ማሳሰቢያዎች) የተወሰደ ነው።  (አንቀጽ 1፤ 6)

·        ቅዱሱ አገላለፁን የተጠቀመው በወንጌል ጣዕም ምልክት የተደረገበትን የሕይወት መንገድ ለማመልከት ነበር።

·        ቅዱስ ፍራንቸስኮስ ሁሉንም ወንዶችና ሴቶች የመልካምድር አቀማመጥ እና ርቀት ከሚያስከትሉት መሰናክሎች ወደሚሻገር ፍቅር እንድንሄድ ይጋብዙናል።

ጳጳሳዊ መልእክቱ የተዋቀረው እንዴት ነው?

ሁላችንም ወንድማማቾች ነን የተሰኘው ጳጳሳዊ መልእክት አጠቃላይ መግቢያ እና 8 ምዕራፎችን የያዘ ነው።

መግቢያ

ምዕራፍ 1. በተዘጋ ዓለም ላይ ያንዣበበው ጥቁር ጨለማ

ምዕራፍ 2. በመንገድ ላይ ያለ አንድ እንግዳ

ምዕራፍ 3. ለሁሉም ክፍት የሆነ ዓለም ለወደፊቱ እንደ ሚመጣ ማሰብ እና መሳተፍ

ምዕራፍ 4. ለዓለም ሁሉ የተከፈተ ልብ

ምዕራፍ 5. የተሻሉ የፖለቲካ ዓይነቶች

ምዕራፍ 6. ውይይት እና ወዳጅነት በማሕበረሰብ ውስጥ

ምዕራፍ 7. የታደሱ የመገናኛ መንገዶች

ምዕራፍ 8. በአለማችን ውስጥ ወንድማማችነትን በማገልገል ላይ የሚገኙ ሐይማኖቶች።

1.     የምዕራፍ አንድ አጠቃላይ መግለጫ

በተዘጋ ዓለም ላይ ያንዣበበው ጥቁር ጨለማ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በአለማችን ውስጥ ሁለንተናዊ የሆነ የወንድማማችነትን እድገት የሚያደናቅፉ አዝማሚያዎች እንዳሉ ተመልክተዋል።

“ሉላዊ (Globalized) የሆነ ማሕበረሰብ ጎረቤታሞች እንድንሆን አድርጎናል፣ ነገር ግን ወንድማማቾች እና እህተማማቾች እንድንሆን ግን ሁኔታውን አላመቻቸም”። (አንቀጽ 12)

በተዘጋው ዓለም ላይ የተጋረጠውን ጥቁር ጨለማ እንዴት ልብ ማለት ማለት እንችላለን?

1. በኅብረተሰቡ ውስጥ ተስፋፍቶ ያለውን የተስፋ መቁረጥ ስሜት በመመልከት

2. የመወያየት እና አብሮ የመኖር ሁኔታዎችን የሚገቱ ነገሮችን በመመልከት

3. በቀላሉ ተጠቅመን ሲያረጁ የምንጥላቸውን እና የተወገዱ ሰዎችን በመመልከት

4. መብቶች በእኩልነት አለመከበራቸውን እና አዲስ የባርነት ዓይነቶችን በመመልከት

5. የሥነ ምግባር ብልሹነት እና የመንፈሳዊ እሴቶች መዳከም በመመልከት

ዛሬ ብልጣብልጥ በሆነ መልኩ ጫና መፍጠር የሚችሉ የሚከተሉትን ቃላት እየታዘብን እንገኛለን ዲሞክራሲ ---- ነጻነት ---- ፍትህ ---- ሕብረት

እነዚህ ተግዳሮቶች ለመጋፈጥ ፍራቴሊ ቱቲ (ሁላችንም ወንድማማቾች ነን) የተሰኘው ሐዋርያዊ መልእክት አጥብቆ የሚናገረው “መጓዝ ያለብን መንገድ የመቀራረብ መንገድ ነው፣ የመገናኘት ባህል ነው ”(አንቀጽ 30)።

·        እግዚአብሔር የተትረፈረፈ የመልካምነትን ዘር መዝራቱን ቀጥሏል (አንቀጽ 54)።

·        መልካምነት ከፍቅር ፣ ከፍትህ እና አብሮነት ጋር በእያንዳንዱ ሰው እና በየቀኑ መከናወን አለበት (አንቀጽ 11)።

·        ተስፋ አድማሳችንን ከሚገድበው ከማንኛውም የግል ምቾት ባሻገር የሚመለከት ሲሆን ለታላላቅ ሃሳቦች ክፍት እንድንሆን ያደርገናል (አንቀጽ 55)።

2.     የምዕራፍ ሁለት አጠቃላይ መግለጫ

በመንገድ ላይ የሚገኝ አንድ እንግዳ

በደጉ ሳምራዊው ምሳሌ ውስጥ ያሉ የተለያዩ ገጸ-ባህሪያት እነማን ናቸው? ወንበዴ የሆኑ ሰዎች፣ ገለል ብለው ያልፉ ሰዎች እና የቆሰለው እና በሞት አፋፍ ላይ የሚገኘው ሰው። በዚህ ሁኔታ ፊት ለፊት ፍራቴሊ ቱቲ (ሁላችንም ወንድማማቾች ነን) የሚጠይቀን ነገር . . .

Ø ከእነዚህ ሰዎች ውስጥ ለየት አድርገህ የምትመለከተው ሰው የተኛው ነው? (አንቀጽ 64)

Ø ባልንጀራህስ ማነው? (አንቀጽ 80)

“ለእኛ ቅርብ የሆኑ ሰዎች ብቻ ባልጅሮቻችን ናቸው ብለን አንዳንወስድ፣ ይልቁንም እኛ እራሳችን ለሁሉም ሰዎች ባልንጀራ መሆን እንደ ሚገባን ኢየሱስ ያስተምረናል። (አንቀጽ 80)

ዛሬ የደጉ ሳምራዊው ታሪክ ተደግሟል

·        የራሳችንን ግድየለሽነት ለማስረዳት ቁርጠኛ መሆናችንን ወይም ደግሞ ገዳይ መሆናችንን እንድናረጋግጥ የቅረበ ጥሪ ነው። (አንቀጽ 57)

·        ህብረተሰቡ ሌሎችን በተለይም አቅመ ደካሞችን ችላ ወደ ማለት አዘንብሏል። (አንቀጽ 64)

·        ማኅበራዊ መገለልን ዓለም ይፈቅዳል፣ ያበረታታል።

·        ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ግድየለሽነት እየተመለከትን ነው። (አንቀጽ 71)

የቆሰሉ ማህበረሰቦቻችንን መልሰን በማቋቋም ረገድ ንቁ ተሳትፎ አንድናደርግ  ፍራቴሊ ቱቲ (ሁላችንም ወንድማማቾች ነን) ጥሪ ያቀርብልናል። (አንቀጽ 77)

  የተቸገረ ወንድም ወይም እህት ከእኛ አገር ወይም ከሌላ ቦታ ቢመጣ ፍቅር አይገደውም።

ተለያይተን እንድንቀር የሚያደርጉንን ሰንሰለቶች ፍቅር ይሰባብራል፣ በእነሱ ምትክ ድልድዮችን ይገነባል።(አንቀጽ 62)

በመንገድ ዳር ቆስሎ የተኛውን ሰው ስታይ በሌላኛው በኩል አልፈ ትሄዳለህ? ወይስ ቆም ብለህ ልትረዳው ትሞክራለህ?

በብዙ ሥቃይና መከራ ውስጥ የእኛ ብቸኛው ጎዳና ደጉ ሳምራዊው ያደረገውን መኮረጅ ነው። (አንቀጽ 67)

3.     የምዕራፍ ሦስት አጠቃላይ መግለጫ

ለሁሉም ክፍት የሆነ ዓለም ለወደፊቱ እንደ ሚመጣ መመኘት እና እውን እንዲሆን መሳተፍ

ኢየሱስ “ሁላችሁም ወንድማማቾች እና እህተማማቶች ናችሁ” (ማቴ 23 8) ብሎናል። (አንቀጽ 95)

ዓለም አቀፋዊ የወንድማማችነት ጥሪ ግልፅነትን ይጠይቃል (አንቀጽ 87)።

1.     የሰው ልጆች ምልአት የሚያገኙት ከልብ በመነጨ መልኩ ራሳቸውን ለሌሎች ሲያቀርቡ ብቻ ነው (አንቀጽ 87)።

2.     ፍቅር ሌሎችን መቀበል እና ከእኛ ባሻገር ያሉትን ሰዎች ለመድረስ የበለጠ ችሎታን ይሰጠናል። (አንቀጽ 95)

3.     ድንበሮችን ማለፍ የሚችል ፍቅር “በማህበራዊ ወዳጅነት” ላይ የተመሠረተ ነው። (አንቀጽ 99)

መልካም የሆኑ ነገሮችን ማራመድ ማለት የሰውን ልጅ እድገት የሚያፋጥኑ እሴቶችን ማራመድ ማለት ነው።

ይህ እንዴት ሊሳካ ይችላል?

·        ከማህበረሰብ አንፃር በማሰብ እና በመተግበር። (አንቀጽ 116)

·        የድህነትና የኢፍታዊነት መዋቅራዊ መንስኤዎችን በመዋጋት። (አንቀጽ 116)

·        ክልላዊ መንግሥት በቦታው ተገኝቶ ንቁ እንዲሆን በመጠየቅ እና ለአደጋ ተጋላጭ ለሆኑት ሰዎች እገዛ እንዲያደርግ በማድረግ (አንቀጽ 108)።

·        ማንም እንዳይገለል ዋስትና በመስጠት። (አንቀጽ 121)

·        በአለም አቀፍ ደረጃ የአብሮነትና የአገልጋይነት ስነምግባር ላይ የተመሠረተ እውነተኛና ዘላቂ ሰላም በማስፈን። (አንቀጽ 127)

እያንዳንዱ ሰው ዋጋ አለው፣ በክብር የመኖር መብት አለው!

4.     የምዕራፍ አራት አጠቃላይ መግለጫ

ለዓለም ሁሉ የተከፈተ ልብ

ለዓለም አቀፍዊ ወንድማማችነት የሚጠቅሙን እርምጃዎች የተኞቹ ናቸው?

1.     ስደተኞችን እና ተገልለው የሚገኙትን ሁሉ መቀበል ፣ መጠበቅ ፣ ማስተዋወቅ እና ማዋሃድ (አንቀጽ 129)።

2.     በዘመናችን ሁላችንም አንድ ላይ እንድናለን፣ ወይም ማንም አይድንም የሚለውን የበለጠ መገንዘብ።(አንቀጽ 137)

3.     የሁሉንም ህዝቦች ልማት የሚደግፍ ዓለም አቀፍ የሕግ ፣ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ስርዓት መዘርጋት።  (አንቀጽ 138)

በነጻ የተሰጠን ነገር ምንድነው? (አንቀጽ 139)

·        አንዳንድ ነገሮችን ማድረግ መልካም ነው፣ ምክንያቱም ነገሮች በራሳቸው መልካም ናቸውና።

·        ለግል ጥቅም ወይም ወሮታ ባለማሰብ እርምጃ መውሰድ።

·        እንግዶችን መቀበል ምንም እንኳን ወዲያውኑ ተጨባጭ ጥቅም ባያስገኝልንም በእዚህ ተግባር መሳተፍ።

የተለያዩ የዓለማችን ሀገሮች ትክክለኛ እሴታቸው የሚለካው ራሳቸውን የትልቁ የሰባዊ ቤተሰብ አካል አድርጎ በመቁጠር ላይ የተመሰረተ የማሰብ ችሎታቸው ላይ የተመሰረተ ነው። እግዚአብሔር ሁል ጊዜ በነፃ ይሰጣል። (አንቀጽ 140-141)

እያንዳንዱ ጤናማ ባህል በተፈጥሮው ለሁሉም ክፍት እና እንግዳ ተቀባይ ነው (አንቀጽ  146)

·        አእምሯችንን እና ልባችንን መክፈት ከእኛ ልዩ የሆኑ ሰዎችን ለመረዳት ይረዳናል። (አንቀጽ 147)

·        አለም አቀፋዊ በሆነ ህብረት እያንዳንዱ የሰብስዊ ቡድን የራሱ የሆነ ውበት እንዳለው የገነዘባል። (አንቀጽ 149)

·        የሰው ልጆች ውስን የሆኑ ፍጥረታት ቢሆኑም እንኳ ገደብ የለሽ ናቸው። (አንቀጽ 150)

ዓለማቀፋዊ ቤተሰብ መሆናችንን ከተረዳን ለባልንጀሮቻችን ራሳችንን መክፈት አንችላለን። (አንቀጽ 151)

“Laudato Sì” ውዳሴ ለአንተ ይሁን ሳምንት

በእዚህ በተገባደደው በጎርጎሮሳዊያኑ 2020 ዓ.ም ውስጥ “ሁሉም ነገር የተሰላሰለ ነው” በሚል መሪ ቃል “ውዳሴ ለአንተ ይሁን” በላቲን ቋንቋ “Laudato Sì” ሳምንት ከግንቦት 10-16/2012 ዓ.ም ድረስ ተክብሮ ማለፉ የሚታወስ ሲሆን ይህ ሳምንት በቫቲካን ሁለንተናዊ ሰብዓዊ እድገት በበላይነት የሚከታተለው ጳጳሳዊ ምክር ቤት ጋር በመተባበር ለአንድ ሳምንት የተዘጋጀ መታሰቢያ ነው። ዓላማውም ከእዚህ ቀደም የጋራ መኖሪያ ቤታችን የሆነችውን ምድራችን በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት እየደረሰባት ካለው ውድመት ለመከላከል ከእዚህ ቀድም የተጀመሩ በጎ ተግባራት ለማስተዋወቅ የተጀመረ የለውጥ ጉዞ ቀጣይ ክፍል ሲሆን “በጸሎት ፣ በማሰላሰል እና የተሻለ ዓለም ለመፍጠር አብረን በመዘጋጀት በአሁኑ ወቅት በምድራችን ላይ የተቃጣውን አደጋ በጋራ በመዋጋት  የተሻለ የጋራ መኖሪያ መገንባት ይኖርብናል” በሚል ሕሳቤ ለአንድ ሳምንት ተከብሮ ማለፉ ይታወሳል።

“ውዳሴ ለአንተ ይሁን” በላቲን ቋንቋ “Laudato Sì” በሚል አርእስት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ  እ.አ.አ በኝቦት 24/2015 ዓ.ም ይፋ ያደረጉት ጳጳሳዊ መልእክት አምስተኛ አመት ለአንድ ሳምንት ያህል በተለያዩ ምድራችንን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራትን በመፈጸም እንዲከበር ይህ አሁን መላውን ዓለም እያስጨነቀ የሚገኘው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኛ ከመከሰቱ በፊት በቫቲካን ሁለንተናዊ ሰብዓዊ እድገት በበላይነት የሚከታተለው ጳጳሳዊ ምክር ቤት መወሰኑ የሚታወስ ሲሆን ለእዚህ በወቅቱ የተመረጠው መሪ ቃል ደግሞ “ሁሉም ነገር የተሰላሰለ ነው” የሚል እንደ ሆነ መገለጹ ይታወሳል።

“ውዳሴ ለአንተ ይሁን” በላቲን ቋንቋ “Laudato Sì” በሚል አርእስት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ  የዛሬ አምስት አመት ገደማ ይፋ ያደረጉት ጳጳሳዊ መልእክት ስድስት ምዕራፎችን በውስጥ አቅፎ የያዘ ጳጳሳዊ መልእክት ሲሆን የእዚህ ጳጳሳዊ መልእክት መሪ ሐሳብ የመነጨው ደግሞ እ.አ.አ. በ11ኛው ክፍለ ዘመን በኖረው እና ለተፈጥሮ እጅግ ከፍተኛ የሆነ ፍቅር ከነበረው ቅዱስ ፍራንቸስኮስ ዘአዚዚ ጥሎት ካለፈው አሻራ ሲሆን እርሱም ምድራችንን በተመለከተ ሲናገር “የጋራ ቤታችን፣ ሕይወታችንን የምናጋራት እህታችን እና እጆቿን ዘርግታ የምታቅፈን ውድ እናታችን” በማለት የምድራችንን ውበት ይገልጽ የነበረ ሲሆን በተጨማሪም “ጌታዬ ሆይ በምትንከባከበን እና በምታስተዳድረን በቀለማት ባሸበረቁ አበቦች እና ዕጽዋት በተሞላችውና ልዩ ልዩ ፍሬዎችን በምታፈራልን እህታችን እና እናታችን ምድር አማካይነት ተወደስ” በማለት የተፈጥሮን ሥጦታዎችን በመመልከት ብቻ የዚህ ስጦታ ፈጣሪ የሆነውን አምላክን ማወደስ እንደ ሚቻል ይገልጽ ነበር። ምድራችንን መንከባከብ ማለት የአምላክ ስጦታን መንከባከብ ማለት እንደ ሆነ አበክሮ ይግልጽ ነበር።

ቤተሰብን የተመለከቱ አስተምህሮዎች

በእዚህ በተገባደደው በጎርጎሮሳዊያኑ 2020 ዓ.ም ውስጥ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ቤተሰብን በተመለከተ በርካታ አስተምህሮችን መስጠታቸው የሚታወስ ሲሆን ከብዙዎቹ በጥቂቱ የሚከተለውን ብለዋል . . .

“የቅዱስ ቤተሰብን አብነት በመከተል ቤተሰብ ትምህርት ቤት መሆኑን የሚያሳዩ እሴቶችን እንደገና እንድናገኝ ተጠርተናል፤ የተስፋ አድማሶችን በመክፈት ግንኙነቶችን ሁል ጊዜ በሚያድስ ፍቅር መመስረት ያስፈልጋል። ቤተሰብ የጸሎት ቤት በሚሆንበት ጊዜ ፣ ​​ፍቅር ጥልቅ እና ንፁህ በሚሆንበት ጊዜ ፣ ክርክር በይቅርታ ሲያሸንፍ ፣ የዕለት ተዕለት የኑሮ ውድነት በጋራ ርህራሄ እና በእግዚአብሄር ፈቃድ በሰላማዊ መንገድ በመታዘዝ ልባዊ ህብረት ማግኘት ይቻላል። በዚህ መንገድ ቤተሰቡ እግዚአብሔር እንዴት በደስታ መስጠት እንዳለባቸው ለሚያውቁ ሰዎች ሁሉ የሚሰጣቸውን ደስታ ይካፈላሉ። በተመሳሳይ ጊዜም ​​ራሱን ወደ ውጭ በማውጣት ለሌሎች ለወንድሞቹ አገልግሎት ለዘለቄታው አዲስ የሆነና የተሻለ ዓለም ለመገንባት  ለመተባበር ራሱን ለመክፈት መንፈሳዊ ኃይል ያገኛል ፤ ስለሆነም አዎንታዊ ተነሳሽነት መግለጽ የሚችል፣ ስብከተ ወንጌልን በሕይወቱ መስበክ የሚችል ሰው ምሳሌ ይሆናል”።

የዛሬ አምስት አመት ገደማ ይፋ የሆነው እና በመጪው እ.አ.አ መጋቢት 19/2021 ዓ.ም ይፋ የሆነበት 5ኛው ዓመት የሚዘከርለት በላቲን ቋንቋ “Amoris laetitia” (የፍቅር ሐሴት) በሚል አርእስት የተጻፈው ሐዋርያዊ ማሳሰቢያ ላይ እንደተገለጸው የጠበቀና የቤተሰብ ፍቅርን ተስማሚ አድርጎ በማቅረብ ይህንን ገቢራዊ እንድናደርግ ለዚህ አስቸኳይ ጥሪ ያቀርብልናል።

ይህ ልዩ ዓመት በላቲን ቋንቋ “Amoris laetitia” (የፍቅር ሐሴት) በተሰኘው ሐዋርያዊ ማሳሰቢያ ሰነድ ይዘቶች ላይ አስተያየት እና ሐዋርያዊ መሳሪያዎችን ጥልቀት ባለው መልኩ ለመረዳት እድሉን ይሰጠናል። ለቤተክርስቲያኗ ማህበረሰቦች እና ለቤተሰቦቻቸው በጉዞአቸው አብረው እንዲጓዙ ያደረጋል። ከአሁን ጀምሮ ሁሉም ሰዎች የምዕመናንን፣ የቤተሰብን እና የሕይወትን ጉዳይ በበላይነት የሚቆጣጠረው ጳጳሳዊ ምክር ቤት አስተባባሪነት እና ተነሳሽነት በዓመቱ ውስጥ የምንራመድበት ሁኔታ በማመቻቸት በሚካሄደው አመት ውስጥ ተካፋይ ትሆኑ ዘንድ እገብዛለሁ። ይህንን ጉዞ ከመላው ዓለም ከመጡ ቤተሰቦች ጋር ማከናወን አንችል ዘንድ ለናዝሬት ቅዱስ ቤተሰብ በተለይም የማርያም እኞኛ እና አስተዋሽ አባት ለሆነው ለቅዱስ ዮሴፍ በአደራ እንሰጣለን በማለት ቅዱስነታቸው ልዩ የቤተሰብ አመት ማወጃቸው ይታወሳል።

31 December 2020, 13:01