ፈልግ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከ51 አመት በፊት ማዕረገ ክህነት ሲቀበሉ የሚያሳይ ምስል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከ51 አመት በፊት ማዕረገ ክህነት ሲቀበሉ የሚያሳይ ምስል። 

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ማዕረገ ክህነት የተቀበሉበትን 51ኛ አመት አከበሩ።

እ.ኤ.አ. በታህሳስ 13/1969 ዓ.ም ማዕረገ ክህነት የተቀበሉ እና አሁን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የሆኑት ሰው በቅዱስ ማቴዎስ አመታዊ በዓል ላይ እ.ኤ.አ በመስከረም 21/953 ነበር ለምስጢረ ክህነት የነበራቸው ጥሪ የተሰማቸው።

የእዚህ ዘገባ አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ከዛሬ ሃምሳ አንድ ዓመት በፊት እ.ኤ.አ. ታህሳስ 13/1969 ዓ.ም እና ሠላሳ ሦስተኛውን የልደት በዓል ከማክበራቸው ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ ጆርጅ ማሪዮ በርጎግልዮ ማዕረ ክህነት ተቀበሉ። ማዕረ ክህነት ከመቀበላቸው ከአሥራ አንድ ዓመት በፊት እ.ኤ.አ. በመጋቢት 11/1958 ዓ.ም የኢየሱሳዊያን ማሕበር ተመክሮ ቤት መግባታቸው የሚታወስ ሲሆን አስፈላጊውን ምዕራፍ ካጠናቀቁ በኋላ የመጨረሻ መሃላ በየካቲት22/1973 አድርገው የኢየሱሳዊያን ማሕበር ቋሚ አባል ሆነዋል።

ይህንን ዝግጅት ከእዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ!

አሁን የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የሆኑት ፍራንቸስኮስ ለክህነት ሕይወት ያላቸውን ጥሪ የተቀበሉት እና ይህ መንፈሳዊ ጥሪ የተሰማቸው እ.ኤ.አ. በመስከረም 21/1953 ዓ.ም በቅዱስ ማቴዎስ አመታዊ በዓል ላይ ሲሆን በዚያን ቀን በወቅቱ የ17 ዓመቱ ወጣት ልጅ የነበሩት ጆርጅ በርጎግልዮ በአርጄንቲና በቦነስ አይረስ በተለምዶ እርሳቸው ሲያዘወትሩት በነበረው ደብር አጠገብ በማለፍ ላይ በነበሩበት ወቅት ምስጢረ ንስሃ በመግባት ኃጢአታቸውን መናዘዝ እንዳለባቸው የሚገልጽ ስሜት ተሰማቸው። ወደ ቤተክርስቲያን በገቡበት ወቅት እርሳቸው በወቅቱ የማያውቁት አንድ ካህን ጋር ተገናኙ፣ እናም በወቅቱ ያደረጉት ያ ኑዛዜ ሕይወታቸውን ለውጦታል።

በኋላ ላይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ስለሁኔታው ሲገልጹ “ለእኔ ይህ ድንገተኛ ገጠመኝ ነበር” ብለዋል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ እ.ኤ.አ. ግንቦት 18/2013 ዓ.ም በጴንጤቆስጤ በዓል ዋዜማ ላይ ባደረጉት ንግግር ስለሁኔታው ሲገልጹ ከረጅም ጊዜ በፊት ወደ እዚያ ቤተክርስቲያን በመሄድ ጉብኝት ማደረጋቸውን የገለጹ ሲሆን “አንድ ሰው እየጠበቀኝ ነበረ አገኘሁትም። ነገር ግን ማን እንደ ሆነ አላውቅም ፣ አላስታውስም ፣ ያ የማላውቀው ልዩ ካህን እዚያ ለምን እንደነበረ አላውቅም፣ ወይም ለምን የመናዘዝ ፍላጎት እንደተሰማኝ አላውቅም ፣ እውነታው ግን አንድ ሰው እየጠበቀኝ ነበር። ለተወሰነ ጊዜ ይጠብቀኝ ነበር። ኑዛዜ ካደረኩኝ በኋላ የሆነ ነገር እንደተለወጠ ተሰማኝ። እኔ ተመሳሳይ ሰው አልነበርኩም። እንደ ድምፅ ወይም እንደ ጥሪ የሆነ ነገር ሰምቻለሁ። ቄስ መሆን እንዳለብኝ እርግጠኛ ነበርኩ” በማለት መናገራቸው ይታወሳል።

ጆርጅ በርጎግልዮ በሕይወታቸው ውስጥ የእግዚአብሔርን ፍቅር መገኘታቸውን ተመለከቱ፣ ልባቸው እንደተነካ እና የሎዮላውን የቅዱስ ኢግናሺዬስ ምሳሌ ተከትለው ርህራሄ በሚመስል መልኩ ወደ ሃይማኖታዊ ሕይወት የጠራቸው የእግዚአብሔር ምህረት መፍሰሱ ተሰማቸው። የሊቀ ጳጳሱን ምርጫ ያነሳሳው ይህ የሕይወታቸው ክፍል ነበር ፣ በኋላም የእርሳቸው የርዕሰ ሊቃነ ጵጵስና ዘመን መሪ ቃል በላቲን ቋንቋ “Miserando atque eligendo” በአማርኛ "ራራለት እና መረጠው” የሚለውን መሪ ቃል ለመምረጥ ያነሳሳቸው የቅዱስ ማቴዎስን ጥሪ በሚገልጸው የቅዱስ ወንጌል ክፍል ላይ አስተያየት ሲሰጡ በላቲን ቋንቋ “Vidit ergo lesus publicanum et quia miserando atque eligendo vidit, ait illi sequere” (ኢየሱስ ቀረጥ ሰብሳቢውን አይቶ በምህረት ዐይን ተመለከተውና መረጠው) እርሱን ተከተለኝ አለው ከሚለው የቅዱስ ወንጌል ቃላት ጋር የራሳቸውን ጥሪ አዛምደዋል።

ካህናት በሊቀ ጳጳሱ ልብ ውስጥ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በንግግራቸው እና በስብከታቸው ውስጥ ሳይቀር ብዙውን ጊዜ ስለካህናት መናገራቸው ይታወሳል። በተለይ ዘንድሮ የወቅቱን ወረርሽኝ እና ድንገተኛ በሆነ መልኩ በጤና ላይ ባስከተለው አደጋ ለተፈተኑ እና ለተሞከሩ ታማኝነትን ላሳዩ ቁርጠኛ የሆኑ ካህነትን በመጥቀስ ደጋግመው በማንሳት አመስግኗቸዋል።

በእዚህ በያዝነው አመት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ለመከላከል ይችላ ዘንድ በተጣለው እገዳ ምክንያት አንዳንድ የቤተክርስቲያኗ በዓላት መስዋዕተ ቅዳሴ ዘንድሮ ሲተላለፉ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በሮም ከተማ ለሚገኙ ካህናት መልእክት አስተላልፈው ነበር። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በመልእክታቸው “የሕዝቡን ሥቃይ በገዛ እጃቸው ለሚነኩት” የእግዚአብሔር ሰዎች ለሆኑ ካህናት ሞቅ ያለ ሰላምታ ካቀረቡላቸው በኋላ በእዚህ በኮሮና ቫይረስ መክንያት ለተጎዱ ሰዎች ካህናቱ የሚያደርጉትን ከፍተኛ ድጋፍ አድንቀው ከእነርስ ጋር በመንፈስ እንደ ሚሆኑ እና በጉዞዋቸው አብሮዋቸው እንደ ሚሆኑ ማረጋግጣቸው ይታወሳል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በወቅቱ ባስተላለፉት መልእክት እንደ ካህናት ማህበረሰብ “እኛ ለእነዚህ ሁኔታዎች እንግዳ አይደለንም ነበር ፤ በመስኮት ላይ ቁመን ጉዳዩን በትዝብት ብቻ ቁመው አልተመለከቱም። አውሎ ነፋሱን በፍጹም ሳይፈሩ ማህበረሰቡን፣ ለመከታተል እና አብሮ ለመሄድ የሚያስችሉ መንገዶችን አግኝተዋል። ተኩላ ሲመጣ ባዩ ጊዜ አልሸሹም፣ መንጋውንም ጥለው አልሄዱም” በማለት መናገራቸው ይታወሳል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ  ካህናትን ጠቢባን ፣ አርቆ አሳቢ እና ቁርጠኛ እንዲሆኑ አሳስበዋል። ወደ ፊትም በመመልከት  ለካህናቱ “የማዳመጥ ችሎታ እንዲያዳብሩ እና በተስፋ የተሞሉ፣ ረጋ ያሉ ግን ጠንካራ የሆኑ፣ ጠንቃቃ ፣ በጽናት የቆሙ እና ፍርሃት የለሽ” እንዲሆኑ በመልእክታቸው ማሳሰባቸው ይታወሳል። በወቅቱ ያስተላለፉትን መልእክት ሲያጠናቅቁ “ካህናት የካህናት ማሕበር አባላት እንደ መሆናችን መጠን ለወደፊቱ ሃላፊነት መውሰድ እና እንደ ወንድም ማቀድ የእኛ ድርሻ ነው” ማለታቸው ይታወሳል።

የካህናት ሐዋርያዊ መንፈስ

ከጣሊያናዊቷ የሎምባዲያ ክልል ለተውጣጡ ሐኪሞች፣ ነርሶች እና የጤና ባለሙያዎች በቫቲካን ባደረጉት ንግግር ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ  ሲናገሩ በሽተኞች የእምነት ጉዞዎቻቸውን እንዲቀጥሉ እና ህመም ሲገጥማቸው ብቻቸውን እንዳይቆዩ እና እንዲረዱ ማደረግ አስፈላጊ መሆኑን ሲናገሩ ይህንን ለማደረግ ደግሞ “ሐዋርያዊ የሆነ ቅንዓት እና በፈጠራ ችሎታ የታገዘ እንክብካቤ” ያለምንም ፍርሃት ማድረግ እንደ ሚጠበቅባቸው ማሳሰባቸው ይታወሳል።

“የብዙ ካህናት ሐዋርያዊ መንፈስ አደናቃለሁ፣ ብዙ ሰዎችን በስልክ አነጋግረዋል፣ ወይም ቤቶችን እያንኳኩ ሰዎችን ጠይቀዋል፣ ‘ምንም ያስፈልጎታል? ወደ ገበያ ማዕከል መሄድ ከፈለጉ ልረዳዎ ዝግጁ ነኝ’” “በማለት በእዚህ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት እንክብካቤ ሲሰጡ ስለነበሩ ካህናት ተናግረዋል። "በየዕለቱ በማካፈል ከህዝባቸው ጎን የቆሙት እነዚህ ካህናት የእግዚአብሔር ማጽናኛ መገኘት ምልክቶች ነበሩ” በማለት አክለው ገልጸዋል። አክለውም “በጣም የሚያሳዝነው በጣም ጥቂቶቹ ሞተዋል ፣ ሐኪሞች እና የህክምና ባለሙያዎችም እንዲሁ” እንዲሁም ታመው የነበሩ ብዙ ካህናትን አስታወሳለሁ፣ ነገር ግን “እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ”  ከዚያ በኋላ ተፈወሰዋል። እናም “ለህዝቡ ብርታት እና ፍቅር ማረጋገጫ ያቀረቡትን” ቀሳውስት ሁሉ አመስግናለሁ ማለታቸው ይታወሳል።

13 December 2020, 12:15