ፈልግ

ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን በሕዳር 24/2013 ዓ.ም በአለም አቀፍ ደረጃ ታስቦ በዋለበት ወቅት ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን በሕዳር 24/2013 ዓ.ም በአለም አቀፍ ደረጃ ታስቦ በዋለበት ወቅት 

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ የአካል ጉዳተኞችን ክብር ማስጠበቅ ይገባል አሉ!

ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን በሕዳር 24/2013 ዓ.ም በአለም አቀፍ ደረጃ ታስቦ መዋሉ ይታወቃል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ይህንን ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን አስመልክተው ባስተላለፉት መልእክት የአካል ጉዳተኞችን ለመንከባከብ ይችላ ዘንድ አካታችን እና ንቁ ተሳትፎ ማደረግ አስፈላጊ መሆኑን አጉልተው ገልጸዋል።በጣም ተጋላጭ የሆኑትን ሰዎች ክብር የሚጎዳውን የማባከን ባህል ቅዱስነታቸው በመልእክታቸው አውግዘዋል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

በሕዳር 24/2013 ዓ.ም የተከበረው የዚህ ዓመት ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን መሪ ሃሳብ “አካል ጉዳተኞችን የሚያካትት፣ ተደራሽ እና ዘላቂ የሆነ ከድህረ- ኮቪድ 19 በኋላ በተሻለ ሁኔታ የወደፊቱን መልሶ መገንባት” የሚል መሪ ቃል መሆኑም ይታወቃል።

ይህንን ዝግጅት ከእዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ይህንን መሪ ቃል በአእምሮአቸው በመያዝ በዓሉን አስመልክተው ባስተላለፉት መልእክት ይህ የዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን “በወረርሽኙ ምክንያት በተፈጠረው ቀውስ በተለይም ደግሞ በዚህ ቀውስ የተነሳ ከፍተኛ ችግር ውስጥ ለወደቁት የአካል ጉዳተኞች” ያላቸውን ቅርበት ለመግለጽ እድል እንደሰጣቸው ተናግረዋል።

“ሁላችንም በአንድ ጀልባ ውስጥ ሁነን እኛን ሊያስፈራራን በሚችል በማዕበል የታወከ ባህር ላይ ነን። ሆኖም በዚህ ተመሳሳይ ጀልባ ውስጥ፣ አንዳንዶቻችን የበለጠ እየታገልን ነው ፤ ከእነዚህ መካከል ከባድ የአካል ጉዳተኞች ይገኙበታል” ብለዋል።

የማባከን ባህል

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በዚህ ዓመት ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች መሪ ቃል ላይ በማተኮር “በተሻለ ሁኔታ የወደፊቱን መልሶ መገንባት” የሚለው የዘንድሮ የአለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች መሪ ቃል አገላለጽ በጣም አስገራሚ ሆኖ እንዳገኙት በመልእክታቸው ገልጸዋል።

በቅዱስ ወንጌል ውስጥ የተጠቀሱስትን በአለት ወይም በአሸዋ ላይ የተገነቡ ቤቶችን ምሳሌ እንዳስብ እንዳደረጋቸው በመግለጽ በመቀጠል በእዚህ ምሳሌ መሠረት በማድረግ አንዳንድ ሐሳቦችን ለማካፈል አጋጣሚውን ተጠቅሟል።

በመልእክታቸውም “በቅዱስ ወንጌል ውስጥ ቤቱን በጠንካራ መሰረት በድንጋይ ላይ የገነባውን እና እንዲሁም ቤቱን በአሸዋ ላይ የገነባውን ሰው ምሳሌ በመጠቀም በዘመናችን እየተስፋፋ ስለመጣው የማባከን ባሕል ተናግረዋል። ይህ ባሕል  “በተለይ ተጋላጭ የሆኑትን የሕብረተሰብ ክፍሎች ከእነዚህም መካከል አካል ጉዳተኞች በከፍተኛ ሁኔታ የሚጎዳ ባሕል ነው” በማለት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ አክለው ገልጸዋል።

ባለፉት ሃምሳ ዓመታት በሲቪል እና በቤተ ክህነት ደረጃ “የአካል እና የስነልቦና ውስንነት ያጋጠማቸው” የሕብረተሰብ ክፍሎች እንዲካተቱ ያደረጉ አስፈላጊ እርምጃዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል። በባህላዊው ደረጃ ግን “አሁንም ቢሆን የዚህ አዝማሚያ በተለይም ደግሞ አካል ጉዳተኞችን በተመለከተ አንዳንድ አንቅፋቶች እንደሚታዩ” ቅዱስነታቸው አክለው ገልጸዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በመልእክታቸው አክለው እንደገለጹት አሁንም ቢሆን በእኛ ዘመን የአካል ጉዳተኞችን በተመለከተ የተዛባ አስተሳሰብ አለ በማለት የተናገሩ ሲሆን አካል ጉዳተኞችን በተመለከተ የቸልተኝነት መንፈስ አለ፣ የሚጠቅሙንን ሰዎች ብቻ ለራሳችን ጥቅም በማዋል፣ እውነታውን ችላ በማለት የገለልተኝነት እና የጥቅም ስሜት በሚፈጥር አስተሳሰብ ምክንያትም የአካል ጉዳተኞችን እናገላቸዋለን፣ ይህ ተገቢ አይደለም ብለዋል።

በዚህም የተነሳ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት እንደገለጹት “የእያንዳንዱን ሰው ክብር ያለማቋረጥ የሚያረጋግጥ እና በተለይም በሁሉም ዕድሜ እና ማህበራዊ ሁኔታ ውስጥ ያሉ የአካል ጉዳተኞችን እና ሴቶችን ለመከላከል የሚሰራውን የሕይወት ባህል ማራመድ አስፈላጊ ነው” ብለዋል።

ማካተት

ወቅታዊውን የጤና ሁኔታ በመጥቀስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ እንደ ገለጹት አሁን ያለው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ “በዘመናችን የተስፋፉውን ልዩነቶችን ይበልጥ ጎልቶ አሳይቷል” በተለይም ተጋላጭ የሆኑትን ሰዎች ብለዋል። በዚህ ምክንያት “ቤታችን የሚገነባበት የመጀመሪያ‘ ዐለት ማካተት መሆን አለበት ’” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አክለው አንደ ገለጹት “በህይወት ጎዳና ላይ ብዙውን ጊዜ የቆሰሉ ሰዎችን እናገኛለን፣ እነዚህም የአካል ጉዳተኞችን እና ልዩ ፍላጎቶችን ሊያካትቱ ይችላሉ፣ እኛ ደጉ ሳምራዊ ወይም ግድየለሽ የሆኑ ተመልካቾች መሆን አለመሆናችንን በእየቀኑ አይቶ መወሰን ይኖርብናል” ብለዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ መልእክታቸውን ሲቀጥሉ “ማካተት” የሲቪል እና የቤተ-ክህነት ተቋማት መርሃ ግብሮችን እና ተነሳሽነቶችን የሚገነቡበት “ዐለት” መሆን አለበት ፣ “በተለይም በከባድ ችግር ውስጥ ያሉ ሰዎች ሳይቀሩ ማንም ሰው ወደ ኋላ እንዳይቀር ለማድረግ ጠንክረን መስራት ይኖርብናል ብለዋል።

ንቁ ተሳትፎ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ህብረተሰቡን “በተሻለ ሁኔታ እንዲገነባ” ለማገዝ “ተጋላጭ የሆኑ ሰዎችን  ማካተት ንቁ ተሳትፎአቸውን ለማሳደግ ጥረት ማድረግም አስፈላጊ እንደ ሆነ” ገልጸዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ “ከምንም በፊት ፣ እንደሌሎች የቤተክርስቲያኗ አባላት ሁሉ የአካል ጉዳተኞች ቅዱስ ቁርባንን የመቀበል መብታቸውን አጥብቄ አረጋግጣለሁ” ብለዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አካል ጉዳተኞች የሐዋርያዊ አገልግሎት ውስጥ ንቁ ተሳትፎ እንዲኖራቸው አንደ ሚፈልጉ የገለጹ ሲሆን የአካል ጉዳተኞች የሐዋርያዊ አገልግሎት ተጠቃሚዎች ብቻ ሳይሆኑ በተቻላቸው አቅም የበኩላቸውን አስተዋጾ እዲያበረክቱ ልንፈቅድላቸው እና ሁኔታዎችን ልናመቻችላቸው ይገባል ብለዋል።  “እኛን የሚያሳስበን እነሱን መንከባከብ ብቻ ሳይሆን በሲቪል እና በቤተ-ክህነት ማህበረሰብ ውስጥ‘ ንቁ ተሳትፎአቸውን ማረጋገጥም” ጭምር ነው ብለዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ አክለውም “የአካል ጉዳተኞች በትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ላይ የሚያደርጉት ተሳትፎ የመላው ምዕመናንን ሕይወት በእጅጉ ያበለጽጋል” ካሉ በኋላ የአካል ጉዳተኞች በቤተክርስቲያን ውስጥ እና በሲቪል ተቋማት ውስጥ ሳይቀር እንደየአቅማቸው የሚሳተፉበትን ሁኔታዎች ማመቻቸት ይገባል ካሉ በኋላ መልእክታቸውን አጠናቀዋል።

03 December 2020, 13:43