ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ ኢየሱስ እንደ ሕጻን ልጅ ሆኖ የመጣው እኛን የእግዚአብሔር ልጆች ለማድረግ ነው አሉ!

የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የማሕበረሰብ ክፍሎች ዘንድ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደበት ቀን የሚታሰብበት የገና በዓል ዋዜማ ትላንት ታኅሳስ 15/2013 ዓ.ም  ተከብሮ ማለፉ ይታወሳል። ይህ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ዋዜማ ሐሙስ ማታ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ ተከብሮ ማለፉ የሚታወስ ሲሆን በወቅቱ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ያሳረጉትን መስዋዕተ ቅዳሴ በመላው ዓለም የሚገኙ በሚልዮን የሚቆጠር ምዕመናን በተለያዩ የመገናኛ አውታረ መረቦች አማካይነት መከታተላቸው ተገልጿል፣ በወቅቱ ቅዱስነታቸው ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ባሰሙት ስብከት ኢየሱስ እንደ ሕጻን ልጅ ሆኖ የመጣው እኛን የእግዚአብሔር ልጆች ለማድረግ ነው ማለታቸው ተገልጿል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

በአሁኑ ወቅት በጣሊያን በአዲስ መልክ እያገረሸ በመጣው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ሕዝቡ ከቤት እንዳይወጣ በመደንገጉ የተነሳ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐሙስ አመሻሽ ላይ ባዶ በሆነው የቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ ሌሊት ላይ የገናን በዓል ዋዜማ ማክበራቸው ተገልጿል። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ሥነ ሥርዓቱን በሬዲዮ ፣ በቴሌቪዥንና በተለያዩ የማኅበራዊ መገናኛዎች አማካይነት ለመከታተል ችለዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በወቅቱ ባደረጉት ስብከት “የኢየሱስ መወለድ በየአመቱ እንድንወለድ እና እያንዳንዱን ፈተና ለመጋፈጥ የሚያስችለውን ጥንካሬ በእርሱ እንድናገኝ የሚያስችለን‘ አዲስነት ’ነው” ብለዋል።

ኢየሱስ የተወለደው “ለእኛ” ነው

የኢየሱስ መወለድ አሉ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ስብከታቸውን ሲቀጥሉ “የኢየሱስ የተወለደው ለእኛ ነው፣ በዚህ ቅዱስ ሌሊት ‘ለእኛ’ የሚለው ቃል ምን ያህል ጊዜ እንደ ተደጋገመ ማስተዋል እንችላለን” ያሉ ሲሆን “ነገር ግን እነዚህ ቃላት ‘ለእኛ’ በእውነት ምን ማለት ናቸው?” በማለት ጥያቄ ማንሳታቸው ተገልጿል። በተፈጥሮ ቅዱስ የሆነው የእግዚአብሔር ልጅ እኛ የእግዚአብሔር ልጆች፣ በጸጋ የተሞላን ሊያደርገን መጥተዋል ማለት ነው በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው ይህ “ታላቅ ጸጋ” ነው “ንጹህ ጸጋ” የሆነ ስጦታ ነው ፣ እኛ ማድረግ በምንችለው ነገር ሁሉ ላይ የማይመሠረት ፣ ነገር ግን እርሱ ለእኛ ባለው የእግዚአብሔር ፍቅር ላይ ብቻ የተመካ ነው ብለዋል።

ለእኛ አንድ ልጅ ተሰጠን

በገና በዓል ለእኛ የተሰጠን የእግዚአብሔር ስጦታ እንዲሁ አንድ ቁስ ወይም አንድ ነገር ብቻ አይደለም፣ ይልቁንም  እግዚአብሔር የእርሱ አጠቃላይ ደስታ የሆነውን አንድያ ልጁን ለእኛ ብሎ ሰጠ ያሉት ቅዱስነታቸው እናም አሁንም  “እኛ እግዚአብሄርን ባለማመስገናችን እና በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ላይ በምንፈጽመው ኢ-ፍትሃዊ ተግባር የተነሳ እግዚአብሄር ይህንን አንዲያ ልጁን ስጦታ አድርጎ ለእኛ መስጠቱ ትክክል ነው ወይ ብለን እንድናስብ ያደርገናል ያሉ ሲሆን በእውነቱ የምንሰራው ሁሉም ነገር ለእዚህ ስጦታ ብቁ እንድንሆን አያደርገንም ብሏል። ይልቁንም እግዚአብሔር ለእኛ ያለው “የማይነጥፍ እና የማይለወጠው ፍቅር” እግዚአብሔር ልጁን እንዲሰጠን አድርጎታል በማለት አክለው ገልጸዋል።

ለድህነታችን ተደራሽ የሚሆን ፍቅር

ኢየሱስ በቤተመንግሥት ውስጥ ሳይሆን በከብቶች በረት ውስጥ የተወለደው እግዚአብሔር ለእኛ በማያልቀው ፍቅር ምክንያት ነው በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው ኢየሱስ ወደ አለም የመጣበት መንገድ “እያንዳንዱ ልጅ ወደ ዓለም በሚመጣበት መንገድ ደካማና ለአደጋ የተጋለጠ በመሆን ሲሆን ድክመቶቻችንን በእርጋታ በፍቅር መቀበልን መማር እንድንችል ነው ... እግዚአብሔር በድህነታችን ውስጥ ድንቅ ነገሮችን መሥራት ይወዳል” ብለዋል።

ይህ “በሕይወት ውስጥ እኛን ለመምራት” ምልክት ሆኖ ቀጥሏል ያሉት ቅዱስነታቸው በቤተልሔም ውስጥ “ለመኖር እንደምንበላው እንጀራ እሱን እንደምንፈልግ ለማስታወስ ያህል እግዚአብሔር በግርግም ውስጥ ተኝቷል፣ በእርሱ ነፃ ፣ የማይጠፋ ፣ ተጨባጭ ፍቅር መሞላት ያስፈልገናል” ማለታቸው ተገልጿል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ አክለው እንደ ገለጹት “በሁሉም ነገር ድሃ በሚመስል ነገር ሆኖም በፍቅር የበለፀገ በግርግም ውስጥ እውነተኛ ምግብ የሚመጣው እራሳችንን በአምላክ እንድንወደድ በማድረግ እና ሌሎችንም በመውደድ እንደሆነ ያስተምረናል” ብለዋል።

እንዴት መውደድ እንዳለብን በማስተማር

ማፍቀር እንዴት እንደ ምንችል ያስተምረን ዘንድ እንደ ደካማ እና ለአደጋ ተጋላጭ ልጅ ሆኖ እግዚአብሔር በገና በዓል ወደ እኛ መጣ በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው “እግዚአብሔር ድሆችን በማገልገል ለእርሱ ያለንን ፍቅር ማሳየት እንዳለብን ሊነግረን ፈልጎ በድህነትና በፍላጎት በእኛ መካከል መጣ” ብለዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አዲስ ለተወለደው አዳኙ ኢየሱስ ጸሎት በማደረግ ስብከታቸውን ያጠቃለሉ ሲሆን “ኢየሱስ ሆይ አንተ ልጅ እንድሆን የሚታደርገኝ ልጅ ነህ። የምትወደኝ እኔ ባለኝ ማንነት መሰረት ነው እንጂ እራሴን እንደምገምተው አይደለም። በከብቶች ማደርያ ውስጥ የተወለድክ ሕጻኑ ኢየሱስ ሆይ አንተን በማቀፍ አንድ ጊዜ እንደገና ሕይወቴን አቅፌያለሁ። አንተን የሕይወት እንጀራ ለመቀበል ፣ እኔ ራሴም ሕይወቴን መስጠት እፈልጋለሁ። አንተ አዳኝ የሆንክ አገልጋይ እንድሆን አስተምረኝ። አንተ ብቻዬን ያልተውከኝ ወንድሞቼን እና እህቶቼን እዳጽናና እርዳኝ፣ ከዛሬ ምሽት ጀምሮ ሁሉም ወንድሞቼ እና እህቶቼ ናቸውና ” ካሉ በኋላ ቅዱስነታቸው ለገና እለት ዋዜማ ያዘጋጁትን ስብከት አጠናቀዋል።

25 December 2020, 13:11