ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ የካቶሊክ የእርዳታ ሰጪ ድርጅቶች የሶሪያ እና የኢርቅ ሕዝቦችን እንዲረዱ አሳሰቡ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመካከለኛው ምስራቅ አከባቢ የሚገኙ የካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናት በሶሪያ እና በኢራቅ እየተከሰተ ባለው የሰብዓዊ ቀውስ የተነሳ ለሚሰቃዩት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ፍላጎት ለማስተባበር እና ምላሽ ለመስጠት የሚያደርጉትን ጥረት ያበረታቱ ሲሆን የካቶሊክ የእርዳታ ሰጪ ድርጅቶች በመከራ ላይ ያሉ የሶሪያ እና የኢራቅ ሕዝቦችን እንዲረዱ አሳስበዋል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዩርጊስ ቫቲካን

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመካከለኛው ምስራቅ የሚገኙ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን መሪዎች በታሕሳስ 01/2013 ዓ.ም በቪድዮ የሚያደርጉትን ኮንፈረንስ እርሳቸው ባስጀመሩበት ወቅት ባስተላለፉት መልእክት በስቃይ እና በመከራ ውስጥ የሚገኙ ሕዝቦችን በሙሉ በተቻለ አቅም መርዳት እና መልሶ ማቋቋም ይገባል ብለዋል።

ይህንን ዝግጅት ከእዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ!

ስብሰባው በሶሪያ እና በኢራቅ እንዲሁም በአጎራባች ሊባኖስ ፣ በቱርክ እና በዮርዳኖስ ባሉ ወቅታዊ የሰብአዊ ቀውሶች ላይ ያተኮረ ሲሆን ስብሰባው ሐሙስ ታሕሳስ 01/2013 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ ዙም በመባል በሚታወቀው በቪዲዮ ቴክኖሎጂ አማካይነት የተከናወነ ሲሆን ስብሰባው የተዘጋጀው ደግሞ በቫቲካን የተቀናጀ የሰው ልጅ ልማት እንዲስፋፋ በሚሰራው ጳጳሳዊ ምክር ቤት እንደ ሆነም ተገልጿል።

በእዚህ በቪዲዮ በተካሄደው ስብሰባ ላይ በመካከለኛው ምስራቅ የሚንቀሳቀሱ የእርዳታ ሰጪ ድርጅቶች ፣ የሀገረ ስብከት ተወካዮች እና የተለያዩ መንፈሳዊ ማሕበራት ተወካዮች ጨምሮ በርካታ የካቶሊክ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ተወካዮች ተሳትፈዋል።

የቫቲካን የዜና ምንጭ ይህንን ስብሰባ በተመለከተ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ መሠረት ስብሰባው በቀጠናው ውስጥ የሚሠቃዩ ሰዎችን ሕይወት ለማሻሻል እንዲቻል በተለያዩ የቤተክርስቲያን ተቋማት መካከል ያለውን ቅንጅት ለማሻሻል ያቀደ ስብሰባ እንደ ሆነ ተገልጿል።

ፍትሃዊ የሆነ ማህበረሰብ መገንባት

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በቪዲዮ መልዕክታቸው ፍትሃዊ የሆነ ማህበረሰብ ለመገንባት የታቀደው እቅድ ግቡን እንዲመታ ያላቸውን ድጋፍ ገልጸዋል። “ይብዛም ይነስም የሰላም ጎዳና እንዲስፋፋ እየተደረገ የሚገኘውን ጥረት ለመደገፍ በፍትሃዊ ማህበረሰብ መዋቅር ላይ አንድ እርምጃ ወደ ፊት እንደ መጓዝ ይቆጠራል፣ ይህም እያንዳንዱ ሰው የራሱ የሆነ ቦታ እንዲያገኝ ያስችለዋል፣ ሁሉም ሰው በሰላም እንዲኖር ሁኔታዎችን ያመቻቻል” ብለዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ አክለው እንደ ገለጹት ብዙውን ጊዜ በጦርነት አስፈሪነት እና ሰቆቃ ምክንያት ቤታቸውን ለቀው ለመሰደድ የተገደዱ ከመካከለኛው ምስራቅ የመጡትን ስደተኞች እንደ ሚያስቧቸው በመልእክታቸው የገለጹ ሲሆን በተለይም እምነታቸው መጀመሪያ የበቀለበትን ከተወለዱበት ቦታ የሸሹትን በርካታ ክርስቲያኖችን ችግር በምሬት ገለፀዋል።

“በእነዚህ ሀገሮች ውስጥ የሚኖሩ ክርስቲያኖች ሁሌም እንደነበረው በገዛ አገራቸው መኖር እንዲቀጥሉ ለማድረግ መጣር አለብን ፤ የሰላም ፣ የእድገት ፣ የልማት እና በህዝቦች መካከል የእርቅ ምልክት” በመፍጠር ሰዎች ልዩነታቸውን በጠበቀ መልኩ አንድነት ፈጥረው በሰላም እንዲኖሩ የበኩላችንን ማደረግ ይጠበቅብናል ብለዋል።

ወደ ቤት የመመለስ ህልም

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወደ አገራቸው መመለስ የሚፈልጉ ስደተኞችን በማስታወስ ዓለምአቀፉ ማህበረሰብም ደህንነታቸውን እና ወደ ገዛ አገራቸው የመመለስ ሕልማቸውን እውን ለማድረግ አስፈላጊ የሆኑትን ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች እንዲያረጋግጡ ያሳሰቡ ሲሆን “በዚህ ረገድ የሚደረገው ጥረት ሁሉ ከፍተኛ ዋጋ የሚሰጠው ነው” ብለዋል።

ስደተኞችን መንከባከብ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ መልእክታቸውን ሲቀጥሉ ሐባቸውን በቀጠናው የሰብዓዊ ዕርዳታ በማደረግ ላይ ወደ ሚገኙ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የእርዳታ ሰጪ ተቋማት ተወካዮች በማዞር “የደጉ ሳምራዊውን አርዓያ በመከተል፣ የእነዚህን አገራት ስደተኞች እና የተፈናቀሉ ሰዎችን የተለያየ ሐያማኖት ያላቸውን ሰዎች በሙሉ ያልምንም ልዩነት ለመቀበል ፣ ለመንከባከብና አብሮ ለመጓዝ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ በመሥራት ላይ የሚገኙትን ድርጅቶች” ማመስገናቸው ተገልጿል።

በቅዱስ ወንጌል የተደገፈ ቸርነት

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከእዚህ ቀደም በተደጋጋሚ እንደ ሚናገሩት “የካቶሊክ ቤተክርስቲያን መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት አይደለችም (NGO)” በማለት በአጽኖት የገለጹ ሲሆን “የበጎ አድራጎት ስራችን በቅዱስ ወንጌል አነሳሽነት የታጀበ መሆን አለበት” ብለዋል። የእኛ እርዳታ በካቶሊካዊ የሰብአዊ እና የልማት ዕርዳታ አስደናቂ መንገዶች አማካኝነት እየተሰቃዩ ለሚገኙ ሰዎች እና የአከባቢውን አብያተ ክርስቲያናት የሚያግዝ ተጨባጭ ምልክት መሆን አለበት። ይህም ማለት በቀላሉ “አንድ ቤተክርስቲያን ሌላ ቤተክርስቲያን ትረዳለች” ማለት ነው ብለዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በመካከለኛው ምስራቅ ላሉት የቤተክርስቲያን መሪዎች በቪዲዮ ባስተላለፉት መልእክት በቋሚነት በጸሎታቸው እና በቡራኬያቸው ከእነርሱ ጋር እንደ ሚሆኑ በማረጋገጥ አጠናቀዋል። ይህ ስብሰባ ለአገሮቻችሁ የተትረፈረፈ የብልጽግና ፣ የልማት እና የሰላም ፍሬ እንዲያፈራ በማደረግ አዲስ ህይወት ያመጣላቸው ዘንድ” ቅዱስነታቸው ከተመኙ በኋላ መልእክታቸውን አጠናቀዋል።

የቤተክርስቲያን ሥራ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን መርዳት ነው

የስብሰባው አዘጋጆች በመግለጫቸው እንዳመለከቱት የቤተክርስቲያኗ ሰፋፊ የእርዳታ ድርጅቶች እ.አ.አ ከ 2014 ዓ.ም ጀምሮ ከሶርያ እና ከኢራቅ ለተፈናቀሉ ሰዎች ከ 1 ቢሊዮን ዶላር በላይ መመደባቸው የተገለጸ ሲሆን ይህ ድጋፍ በየአመቱ ከ 4 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ሰዎች አስቸኳይ ዕርዳታ ለማቅረብ እንዳስቻለም ተይዞ ተገልጿል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንደሚገምተው 11 ሚሊዮን ሶርያዊያን ሰብአዊ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሲሆን 4 ሚሊዮን የሚሆኑ ኢራቃውያን በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ።

10 December 2020, 14:01