ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ የምዕመናንን ባሕል የተላበሱ የአምልኮ ስነ-ስርዓቶች ሊኖሩ ይገባል አሉ።

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ ኅዳር 22/2013 ዓ. ም. ባስተላለፉት የቪዲዮ መልዕክት፣ የኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፓብሊክ ካቶሊካዊ ሀገረ ስብከቶች የሚከተሉትን የመስዋዕተ ቅዳሴ ስነ-ስርዓት የሚያብራራ መጽሐፍ፣ “ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እና ሮማዊት ቤተክርስቲያን የመስዋዕተ ቅዳሴ ስነ-ስርዓት በዛየር ለሚገኙ ካቶሊካዊ ሀገረ ስብከቶች” በሚል ርዕስ የተጻፈው መጽሐፍ በመታተሙ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ከኅዳር 20/2013 ዓ. ም. ጀምሮ በአገልግሎት ላይ የሚውል፣ የሮማዊት ቤተክርስቲያን አዲስ የመስዋዕተ ቅዳሴ ስነ-ስርዓት ማስተዋወቃቸው ይታወሳል። “በዚህ ታሪካዊ ወቅት በአፍሪካ አህጉር ከምትገኝ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ጋር ለመገናኘት በመብቃቴ ደስታ ይሰማኛል” በማለት ደስታቸውን ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ለሌሎች ባህሎችም ተስፋ ሰጭ የጸሎት ሥነ-ስርዓት ነው

በመጽሐፉ ውስጥ የተገለጹ ሃሳቦችን በመቀበል ሌሎች ባህሎችም በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ወቅት መገልገል እንዲችሉ ተስፋ የሚሰጥ ሥነ-ስርዓት ነው ብለው፣ ቅዱስነታቸው፣ የመጽሐፉ ቀዳሚ ዓላማ የመስዋዕተ ቅዳሴው ጸሎት ስነ-ስርዓት በእምነት እና በደስታ የሚከናወን መሆኑን የሚመሰክር እንደሆነም አስረድተዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አክለውም የመጽሐፉ ዋና ዓላማ የዛየር (ኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፓብሊክ) የመስዋዕተ ቅዳሴ ስነ-ስርዓት፣ መንፈሳዊነትን፣ ቤተክርስቲያናዊነትን እና  ሐዋርያዊነትን ለመግለጽ መሆኑን አስረድተዋል። የመጽሐፉ ደራሲ በጥናት ላይ የተመሠረቱ የጸሎት ስነ-ስርዓት መርሆዎችን በመከተል እና በሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ሰነድ ውስጥ በተቀመጡት ጥብቅ ሃሳቦች የተመራ መሆኑን ገልጸዋል። የምዕመናንን ባሕል መሠረት ያደረገ እና በሁለተኛው ቫቲካን ጉባኤ ሰነድ የጸደቀው የዛየር (ኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፓብሊክ) የመስዋዕተ ቅዳሴ ስነ-ስርዓት፣ የላቲን የአምልኮ ስርዓትን ከሚከተሉት ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን መካከል ብቸኛው ሲሆን፣ ሌሎች ባህሎችም ምሳሌነቱን በመከተል፣ የራሳቸውን የጸሎት ሥነ-ስርዓት መዘርጋት እንዲችሉ መንገድ የሚከፍት መሆኑን ቅዱስነታቸው አስታውቀዋል።

የሁለተኛው ቫቲካን ጉባኤ ተነሳሽነት ነው

ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ካበረከታቸው አስተዋፅዖች መካከል አንዱ፣ የተለያዩ ሕዝቦች የአምልኮ ስርዓታቸውን ከባሕላቸው ጋር ማዛመድ የሚችሉበትን ደንብ እና መንገድ ማመቻቸት መሆኑን ቅዱስነታቸው ገልጸዋል። እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ፣ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን በቫቲካን ያደረጉትን የኮንጎን ዴሞክራሲያዊ ሪፓብሊክ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳትን በተቀበሏቸው ጊዜ፣ ከባሕላቸው ጋር የሚስማማ የመስዋዕተ ቅዳሴን ስነ-ስርዓት ለማዘጋጀት በሚነሱበት ጊዜ፣ ምስጢራትን እና ምስጢራቱ የሚገለጹበትን ስርዓት በሚገባ ለማዘጃጀት ጥረት እንዲያደርጉ ማሳሰባቸውን፣ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ አስታውሰዋል። በቅርቡ በተካሄደው የአማዞን አካባቢ አገሮች ብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ሰነድ ላይ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ ስርዓተ አምልኮን በተመለከት የተነሱት በርካታ ሃሳቦች፣ የአካባቢውን ሕዝቦች ባሕል፣ ወግ፣ የሕይወት ልምድ እና ከተፈጠሮ ጋር ያላቸውን ትስስር ያገናዘቡ እንዲሆን አሳስበዋል። ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ከተካሄደ ሃምሳ አመታት የተቆጠሩ ቢሆንም፣ ስርዓተ አምልኮን አስመልክቶ ከተቀመጡ ደንቦች መካከል ጥቂቶቹ ብቻ ተግባራዊ መሆናቸውን ቅዱስነታቸው አስታውሰዋል።

የባህል እና የእሴቶች ተነሳሽነት

የዛየር የመስዋዕተ ቅዳሴ ስነ-ስርዓት ጉልህ ካደረጋቸው ውጤቶች መካከል አንዳንዶቹን መጥቀስ ቢያስፈልግ፣ ለተለያዩ ቋንቋዎች፣ የአምልኮ አልባሳት እና ቀለም እንዲሁም የሰውነት እንቅስቃሴዎች ትኩረትን በመስጠት፣ ሁሉንም የምዕመናን አኗኗር ተመልክቶ ለእያንዳንዱ እሴት ዋጋን መስጠቱ ነው ብለዋል። የኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፓብሊክ ካቶሊካዊ ሀገረ ስብከቶች የሚከተሉት የመስዋዕተ ቅዳሴ ስነ-ስርዓት ማብራሪያ መጽሐፍ መታተሙ፣ በአገሩ ማኅበረሰብ መካከል የሚከናወን የመስዋዕተ ቅዳሴ ስነ-ስርዓት፣ የእግዚአብሔር ሕዝብ ምስጋናውን ለመድኃኒታቸን ኢየሱስ ክርስቶስ በደስታ እና በዜማ ማቅረብን የሚያስታውሰን መሆኑን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቪዲዮ መልዕክታቸው አረጋግጠዋል።           

   

01 December 2020, 20:01