ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ የሚጸልይ አንድ ክርስቲያን ምንም ነገር አይፈራም ማለታቸው ተገለጸ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዘውትር ረቡዕ እለት በቫቲካን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እንደ ሚያደርጉ የሚታወቅ ሲሆን በዚህ መሰረት ቅዱስነታቸው በዛሬው እለት ማለትም በህዳር 02/2013 ዓ.ም ያደረጉት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ከዚህ ቀደም በጸሎት ዙሪያ ላይ ጀምረውት ከነበረው አስተምህሮ ቀጣይ ክፍል እንደ ነበረ የተገለጸ ሲሆን የሚጸልይ አንድ ክርስቲያን ምንም ነገር አይፈራም ማለታቸው ተገልጿል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በወቅቱ ያደረጉትን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተለው አሰናድተነዋል፣ ተከታተሉን።

በእለቱ የተነበው የቅዱስ ወንጌል ቃል

“ስለዚህ እላችኋለሁ፤ ለምኑ ይሰጣችኋል፤ ፈልጉ ታገኛላችሁ፤ በር አንኳኩ ይከፈትላችኋል፤ ምክንያቱም የሚለምን ሁሉ ይቀበላል፤ የሚፈልግም ያገኛል፤ በር ለሚያንኳኳም ይከፈትለታል። “ከእናንተ መካከል አባት ሆኖ ሳለ ልጁ  ዓሣ ቢለምነው እባብ የሚሰጠው ይኖራልን? ወይስ ዕንቊላል ቢለምነው ጊንጥ ይሰጠዋልን? እናንተ ክፉዎች ሆናችሁ ሳላችሁ፣ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታን መስጠት ካወቃችሁበት፣ የሰማዩ አባታችሁ ታዲያ ለሚለምኑት መንፈስ ቅዱስን እንዴት አብልጦ አይሰጥ!” (ሉቃስ 11፡9-13)

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

በጸሎት ዙሪያ ላይ ስናደርገው የነበረውን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ዛሬም እንቀጥላለን። አንድ ሰው ወደ እኔ ቀርቦ “አንተ ስለ ጸሎት በጣም ትናገራለህ። ይህ አስፈላጊ አይደለም” አለኝ። እኔም አዎን አስፈላጊ ነው አልኩት። ምክንያቱም ካልፀለይን በህይወት ወደ ፊት ለመራመድ የሚያስችል ጥንካሬ አይኖረንም ብዬ መለስኩለት። ጸሎት ለሕይወት አስትንፋስ ኦክስጅን ነው። ጸሎት ሁል ጊዜ ወደ ፊት እንድንጓዝ የሚያደረገንን የመንፈስ ቅዱስን ኃይል በእኛ ላይ እንዲሆን የማድረግ ብቃት አለው። ለዚህም ነው እኔ ስለ ጸሎት ብዙ የምናገረው።

ኢየሱስ በጽናት እና የማያቋርጥ ቀጣይነት ባለው መልኩ ሊደረግ ስለሚገባ ጸሎት ምሳሌ ስጥቶናል። ከአብ ጋር የማያቋርጥ ውይይት ፣ በዝምታ እና በማሰላሰል ያድርገው የነበረው ግንኙኘት የሁሉም የእርሱ ተልእኮው ምሰሶ ነበር። ቅዱሳን ወንጌላዊያን ለደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ ጸሎትን በተመለከተ የሰጠውን ማሳሰቢያ በገለጹበት ወቅት እነርሱ ማለትም ደቀመዛሙርቱ ስይታክቱ በፅናት እንዲፀልዩ ኢየሱስ አሳስቦዋቸው እንደ ነበረ ይገልጹልናል። ይህንን በተመለከተ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ (ቁ. 2613) ሲናገር በሉቃስ ወንጌል ውስጥ የተካተቱትን ሦስት ምሳሌዎች ያስታውሰናል፣ ይህም የኢየሱስን የጸሎት ባህሪ የሚያጎላ ነው።

በመጀመሪያ ደረጃ ጸሎት በጽናት መደረግ የሚገባው ሲሆን ለምሳሌም በቅዱስ ወንጌል ውስጥ እንደ ተጠቀሰው ድንገት የመጣውን እንግዳ ለመቀበል፣ እኩለ ሌሊት ላይ የጓደኛውን ቤት በማንኳኳት ዳቦ እንደለመነው ሰው መሆን ማለት ነው። እኩለ ሌሊት ስለሆነና ጓደኛው ተኝቶ ስለነበረ በቤቱ ውስጥ ተኝቶ የነበረው ጓደኛው “አይሆንም!” ተኝቻለሁኝ ሲል ይመልስለታል፣ እሱ ግን ተነስቶ ዳቦ እንዲሰጠው እስከሚያስገድደው ድረስ አጥብቆ ይጠይቃል (ሉቃ. 11፡5-8) በጽናት የተደርገ ጥያቄ ነበር። ነገር ግን እግዚአብሔር ከእኛ የበለጠ ታጋሽ በመሆኑ የተነሳ በእርሱ በልቡ በር ላይ በእምነት እና በጽናት መንፈስ ሆነው የሚያንኳኩ ሰዎች አያፍሩም። እግዚአብሔር ሁል ጊዜ ይመልሳል ፡፡ ሁል ጊዜም። አባታችን የምንፈልገውን ነገር ገና ሳንጠይቀው በፊት በደንብ ጠንቅቆ ይውቃል። አጥብቆ በጽናት እርሱን መለመናችን እርሱን ምን እንደ ሚያስፈልገን ለማሳወቅ ወይም ለማሳመን አይጠቅመንም፣ ነገር ግን በውስጣችን ፍላጎትን እና ተስፋን ለመመገብ ይጠቅማል።

ሁለተኛው ምሳሌ ደግሞ ‘ከባላጋራዬ ጋር ስላለብኝ ጒዳይ ፍረድልኝ’ እያለች ፍትህ ፈልጋ ወደ አንድ ዳኛ ትመላለስ የነበረች ሴት ታሪክ እናያለን።  ይህ ዳኛ ሙሰኛ ነው ፣ እሱ ሥነ ምግባር የጎደለው ሰው ነበር፣ ነገር ግን በመጨረሻ ይህች መበለት ስለ ምትጨቀጭቀኝ እፈርድላታለሁ፤ አለበለዚያ ዘወትር እየተመላለሰች ታሰለቸኛለች (ሉቃ 18፡1-8) በማለት ይፈርድላታል። እናም እንዲህ ያስብ ነበር “ነገር ግን እኔ ችግሯን ፈትቼ ብገላገል ይሻላል ምክንያቱም ያለማቋረጥ እየመጣች ትጨቀጭቀኛለች፣ ታማርራለች” በማለት ይፈርድላታል። ይህ ምሳሌ እምነት ለክፉ ነገሮች እና ፍትህ መጓደልን ለመቅረፍ አንድ አፍታ በችኮላ አድርገነው የምንተወው ነገር ሳይሆን ይልቁኑ እግዚአብሔርን ለመጠየቅ ድፍረት የተሞላበት ዝንባሌ መሆኑን እንድንገነዘብ ያደርገናል።

ሦስተኛው ምሳሌ ለመጸለይ ወደ ቤተ መቅደስ የሄዱ አንድ ፈሪሳዊ እና አንድ ቀራጭ የነበረ ሰው ታሪክ ያቀርባል። የመጀመሪያው በብቃቱ በመኩራራት ልቡን ነፍቶ ወደ እግዚአብሔር ይቀርባል፤ ሌላው ወደ መቅደሱ ለመግባት እንኳን ብቁ እንዳልሆነ ይሰማዋል። ሆኖም  እግዚአብሔር የመጀመሪያውን ማለትም የትዕቢተኞችን ጸሎት አልሰማም፣ እሱ ማለትም እግዚአብሔር ደግሞ ለትሑታን መልስ ይሰጣል (ሉቃ. 18: 9-14)። የትህትና መንፈስ ከሌለ እውነተኛ ፀሎት የለም። በጸሎት እንድንጠይቅ የሚያደርገን የትህትና መንፈስ ነው።

የቅዱስ ወንጌል አስተምህሮ ግልፅ ነው-ሁሉም ነገር ከንቱ ቢመስልም እንኳን እግዚአብሔር መስማት የተሳነው እና ዲዳ ሆኖ ሲታይ እና ጊዜ የምናባክን በሚመስለን ጊዜም ቢሆን ሁል ጊዜ መጸለይ አለብን። ሰማዩ የጨለመ ቢመስለውም እንኳ ክርስቲያን ጸሎቱን አያቆምም። ጸሎቱ ከእምነት ጋር አብሮ ይሄዳል። እናም እምነት በሕይወታችን ውስጥ ባሉት ብዙ ቀናት ውስጥ ሀሳባዊ እና የማይረባ ጥረት ሊመስል ይችላል። በሕይወታችን ውስጥ ጨለማ ጊዜያት አሉ እናም በእነዚያ ጊዜያት እምነት እንዲያው ቅዤት ሊመስል ይችላል። ነገር ግን ጸሎትን መለማመድ ማለት እንዲሁ ይህንን ጥረት መቀበል ማለት ነው። "አባቴ ሆይ እኔ ለመጸለይ እሄዳለሁ ነገር ግን ምንም ስሜት አይሰማኝም ... በደረቅ ልብ የማደርገው ጸሎት መስሎ ይሰማኛል” ልንል እንችል ይሆናል። ነገር ግን እኛ ምንም ይሁን ምን መጥፎ ስሜት በሚሰማን ጊዜያት በነዚህ መጥፎ ጊዜያት ወደ ፊት መጓዝ ይኖርብናል። ብዙ ቅዱሳን እምነታቸው የጨለመባቸው ጊዜያት ነበሩ፣ እግዚአብሔር ዝም ያለ የመሰላቸው ጊዜያት ነበሩ፣ እነዚህን ነገሮች በሕይወታቸው ተመልክተው አልፈዋል፣ ስናንኳኳ እና እግዚአብሔር መልስ ባይሰጠን እንኳን እነዚያ ቅዱሳን እንዳደረጉት በጽናት ጸሎታችንን መቀጠል ይኖርብናል።

በእነዚህ እመነታችን ጨለማ ውስጥ የገባ በሚመስለን ወቅቶች ውስጥ የሚጸልዩ ሰዎች በጭራሽ ብቻቸውን አይደሉም። በእውነቱ ኢየሱስ የጸሎት ምስክር እና አስተማሪ ብቻ አይደለም፣ እርሱ ከእዚያ የበለጠ ነው። ከእርሱ እና በእርሱ በኩል እንድንጸልይ ይጋብዘናል። ይህ ደግሞ የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ነው። በኢየሱስ ስም ወደ አብ እንድንጸልይ ቅዱስ ወንጌል የሚጋብዘን በዚህ ምክንያት ነው። ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ እነዚህን የጌታን ቃላት “አብ በወልድ ይከብር ዘንድ በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ አደርጋለሁ” (ዮሐንስ 14፡13) በማለት ገልጾታል። የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ ይህንን በተመለከተ ሲናገር “የምናቀርበው ልመና የመሰማት እርግጠኛነት በኢየሱስ ጸሎት ላይ የተመሠረተ ነው” (ቁ. 2614) በማለት ያስረዳናል። የሰው ልጅ ጸሎት ሁል ጊዜ ክንፍ እንዲኖረው የሚያደርገው እርሱ ክርስቶስ ብቻ ነው።

ከእግዚአብሄር የሚሆነውን ሁሉ ከሚጠብቅ ልብ የመነጨ በመተማመን የተሞሉትን “በላባዎቹ ይጋርድሃል፤ በክንፎቹ ሥር መሸሸጊያ ታገኛለህ፤ ታማኝነቱ ጋሻና መከታ ይሆንሃል። የሌሊትን አስደንጋጭነት፣በቀን የሚወረወረውንም ፍላጻ አትፈራም፤ በጨለማ የሚያደባ ቸነፈር፣ በቀትር ረፍራፊውም አያሠጋህም” የሚሉትን የመዝሙር ”(91፡ 4-6) ቃላትን እዚህ ለማስታወስ እንዴት አቃተን? ይህ አስደናቂ ጸሎት የተፈጸመው በክርስቶስ ውስጥ ነው ፣ ሙሉ እውነቱን የሚያገኘው በእርሱ ውስጥ ነው። ያለ ኢየሱስ ጸሎታችን ወደ ሰው ጥረት የመቀነስ አደጋ ይገጥመዋል፣ ብዙውን ጊዜ ለውድቀት ይዳርገናል። እርሱ ግን እያንዳንዱን ጩኸት ፣ መቃተት፣ ደስታን ሁሉ ፣ እያንዳንዱን ልመና ... ወዘተ የሰውን ልጅ ጸሎት ሁሉ በራሱ ላይ ተሸከመ። ደግሞም በውስጣችን የሚጸልየውን መንፈስ ቅዱስ አንርሳ፤ እርሱ እንድንጸልይ የሚያደርገን እና ወደ ኢየሱስ የሚወስደን እርሱ ነው፣ እርሱ ወደ አብ እንድንሄድ አብ እና ወልድ የሰጡን ስጦታ ነው። ስንጸልይ በልባችን የሚጸልየው መንፈስ ቅዱስ ነው።

በጸሎት ሕይወታችንም ቢሆን ክርስቶስ ለእኛ ሁሉ ነገር ነው ፡፡ ቅዱስ አውግስጢኖስ ይህንን በተመለከተ ሲገልጽ በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ ውስጥ እናገኘዋለን-ኢየሱስ “እንደ ካህናችን ሁኖ ይጸልይልናል፤ እንደ መሪያችን ሆኖ በእኛ ውስጥ ይጸልያል፣ እርሱ እንደ አምላካችን ሆኖ ለእኛ ይጸልይልናል። ስለዚህ በእርሱ ውስጥ ድምፃችን እንዲሁም በውስጣችን ያለውን የእርሱን ድምፁን እንወቅ ”(ቁ. 2616) ይለናል። እናም በዚህ ምክንያት ነው ክርስቲያን የሆነ ሰው ሳይፈራ የሚጸልየው፣ እርሱ ለእኛ ስጦታ ሆኖ ለተሰጠን እና በውስጣችን ለሚጸልይ መንፈስ ቅዱስን በአደራ የሰጠው። የጸሎትን መንገድ የሚያስተምረን የፀሎት መምህር ራሱ መንፈስ ቅዱስ ይሁን።

11 November 2020, 12:06