ፈልግ

በኮቪድ-19 ወቅት ዕርዳታን ለማግኘት ተሰልፈው የሚጠባበቁ ሰዎች፤ በኮቪድ-19 ወቅት ዕርዳታን ለማግኘት ተሰልፈው የሚጠባበቁ ሰዎች፤ 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ ኮቪድ-19 ያስከተለው ቀውስ በመካከላችን መረዳዳትን የሚያሳደግ መሆን አለበት አሉ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከላቲን አሜሪካ አገሮች ለተወጣጡትና፣ ሴሚናሩን በበይነ መረብ በኩል በመካፈል ላይ ለሚገኙት ተሳታፊዎች የቪዲዮ መልዕክት ማስተላለፋቸው ታውቋል። “ቤተክርስቲያን፣ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ እና የኮቪድ 19 ወረርሽኝ የሚገኝበት ደረጃ” በሚል ርዕስ ውይይት በማድረግ ላይ ለሚገኙት አባላት በላኩት መልዕክታቸው፣ ኮቪድ-19 ያስከተለው ቀውስ በመካከላችን መረዳዳትን የሚያሳድግ መሆን እንዳለበት፣ ይህ ካልሆነ ግን በሕዝቦች መካከል መለያየትን የሚያስከትል መሆኑን አስረድተዋል። የአንድ እግዚአብሔር ልጆች እና ወንድማማቾች መሆናችንን በማስተዋል፣ በተለይም በድህነት ምክንያት በብዙዎች ላይ የደረሰውን የኮቪድ-19 ቀውስ ሃላፊነት በተሞላበት መንገድ፣ በግልጽነት እና በታማኝነት መመከት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የሰውን ልጅ ስቃይ በተለይም የድሃው ማኅበረሰብ በበሽታው ተጠቂነትን አጉልቶ የሚያሳይ፣ በሌላ ወገን አንዱ ለሌላው እንዲጨነቅ፣ በተለይም በፖለቲካው ዓለም በተሰማሩት መካከል ግንኙነት እንዲፈጠር መንገድ ያመቻቸ መሆኑን ለሴሚናሩ ተካፋዮች በላኩት መልዕክት ቅዱስነታቸው አስረድተዋል። የሴሚናሩ ዋና ዓላማ ባሁኑ ጊዜ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ያስከተለውን ቀውስ ትኩረት ሰጥቶ መመልከት፣ ያስከታላቸውን ጥፋቶች ተመልክቶ አስፈላጊውን እርምጃ እና ወረርሽኙን ለመከላከል ጥረት በማድረግ ላይ የሚገኙ የላቲን አሜሪካ አህጉር ተወላጆች የአህጉሪቱን ውበት እና ተስፋ የሚያሳድጉ መሆን አለባቸው በማለት ቅዱስነታቸው በመልዕክታቸው አሳስበዋል።

የወረርሽኙ ተጠቂነት ጉልህ ምልክቶች፤

በድህነት ሕይወት ውስጥ የሚገኙትን፣ ከማኅበረሰቡ የተገለሉትን እና ከማኅበራዊ ሕይወት ርቀው የሚገኙትን ሰዎች ያስታወሱት ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ ወረርሽኙ ባስከተለው ስቃይ ክፉኛ መጎዳታቸውን በግልጽ የሚያሳዩ ድሆች፣ ሁሉንም የላቲን አሜሪካ ሕዝቦች በችግር ውስጥ እንዲገቡ ያደረገው ኢ-ፍትሃዊ የሆነ የኤኮኖሚ ክፍፍል መሆኑን አስረድተዋል። በኑሮ አለመመጣጠንን ወደ ጎን በመተው፣ ልዩነቶችንም በማስወገድ፣ ኮቪድ-19ን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ፍሬያማ ለማድረግ ማኅበራዊ ርቀቶችን ማክበር፣ ንጽሕናን መጠበቅ እና አስተማማኝ የሥራ ዕድሎችን ማመቻቸት ሕይወትን ለማትረፍ የሚያግዝ መሆኑን ቅዱስነታቸው አስረድተው፣ በላቲን አሜሪካ ውስጥ በሰደድ እሳት ቃጠሎ በወደመው በአማዞን በረሃማው ግዛት ውስጥ የሚገኙ የፓንታናል ነዋሪዎችን አስታውሰዋል።

የአንድ ቤተሰብ አባል ነን፤

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ያስከተለውን ኢኮኖሚያዊ ተፅእኖዎችን ያስታወሱት ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ በግልም ሆነ በጋራ የሚጠበቅብንን ተግባር ለማከናወን፣ ተልዕኮዋችንንም በሃላፊነት፣ በግልጽነት እና በታማኝነት ለመወጣት ተጠርተናል ብለዋል። ምክንያቱንም ሲገልጹ፣ በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ ለሁሉም የሚበቃ እና የሚተርፍ የዕለት እንጀራ አለ ብለው፣ ስለዚህም ማኅበራዊ ድርጅቶች ያላቸውን ሃብት ለግል ብቻ ሳያውሉ በሰዎች መካከል ልዩነትን ሳያንጸባርቁ ከሌሎች ጋር መካፈል እና ለሌሎች በማዳረስ እንዳለባቸው አደራ ብለዋል። ቸርነት በተግባር መገለጽ ያለበት ሌላም ማኅበራዊ ችግሮች መኖራቸውን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ መጠለያ አልባነት፣ የእርሻ መሬት እጦት እና ሥራ አጥነት መሆናቸውን ገልጸዋል።

አንድነትን እና ማኅበራዊ ጥቅምን ማሳደግ፤

የላቲን አሜሪካ ሕዝብን ያጋጠመው ማኅበራዊ ችግር ሕዝቡ በአዲስ መንፈስ እንዲነሳሳ ምክንያት ሆኗል ያሉት ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ ይህ ሕዝብ ችግሮች ቢበዙበትም ተስፋውን ማጣት የለበትም ብለዋል። ቅዱስነታቸው በተጨማሪም ማኅበራዊ ጥቅምን በማሳደግ በአንድነት የሚደረግ ጉዞ የፍቅር እና የመቀራረብ መልካም መገላጫዎች ናቸው ብለዋል። የወንድማማችነት ጥሪም ወደ መተሳሰብ የሚመራ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ጎዞ መሆኑን አስረድተው፣ ፖለቲካም ማኅበራዊ ጥቅም በተግባር የሚታይበት ልዩ ጥሪ መሆኑን አስረድተዋል።

የኮቪድ-19ን ጥቃት እንደ ሽፋን መጠቀም አያስፈልግም፤

በኮቪ-19 ወረርሽኝ ዙሪያ የሚካሄደው የፖለቲካ እንቅስቃሴ በጣም ጠንካራ መሆኑን የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ሕዝባችንን ለደረሰው ችግር መፍትሄዎችን ለማግኘት በሚደረጉት ጥረቶች መካከል የሚታዩትን ልዩነቶች በአግባቡ መመልከት እና መምራት ያስፈልጋል ብለዋል። ከሁላችን በተለይም የመሪነት ቦታ የተሰጠን በሙሉ መማር ያለብን ስነ-ጥበብ ቢኖር ጠቃሚ የሆኑ ግንኙነቶችን ማሳደግ እንጂ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ያስከተላቸውን ቀውሶች ለፖለቲካ ፍጆታ መጠቀም አያስፈልግም ብለዋል።

በድሆች ላይ ጉዳትን አስከትሏል፤

በላቲን አሜሪካ ሕዝቦች መካከል ሌላውን የማንቋሸሽ ዝንባሌ መኖሩን የገለጹት ቅዱስነታቸው፣ በላቲን አሜሪካ ውስጥ በድሃው ማኅበረሰብ መካከል ያለውን ችግር ለመቅረፍ የሚያስችሉ አመቺ መንገዶችን ማግኘት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። በተለይም ከሕዝቡ መካከል ተገልለው የሚኖሩ ድሃ ሕዝቦች፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ባደረሰው ጥቃት ከፍተኛውን መስዋዕትነት እየከፈሉ መሆኑን ገልጸዋል። በዚህ አስጨናቂ ጊዜ ውስጥ የፖለቲካ ሃላፊነት የተሰጣቸው በሙሉ አደራን ተቀብለው የጋራ ጥቅምን ለማስከበር የሚጥሩ እንጂ የጋራ ጥቅምን ለግል ጥቅም የሚያውሉ መሆን የለባቸውም ብለው፣ አለበለዚያ ለሙስና መስፋፋት መንገድን ይከፍታል ብለዋል። በቤተክርስቲያን ውስጥም ስብከተ ወንጌል እንዳይስፋፋ የሚያደርጉ እንቅፋቶች መኖራቸውንም ተናግረዋል።

አዲስ ሕይወት መኖር ያስፈልጋል፤

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው መጨረሻ እንዳስገነዘቡት፣ በችግር ውስጥ ለሚገኙት እርዳታን ለማቅረብ ከሚያስችሉ መንገዶች ዋናው የመልካም ሳምራዊን ምሳሌ መከተል ነው ብለዋል። በፍቅር እና በአንድነት ላይ የተመሠረተ መልካም ተግባር ማከናወን የሚቻለው አዲስ ሕይወት መኖር ሲቻል ነው ካሉ በኋላ፣ አንድነት ከልዩነት እንደሚበልጥ አስረድተው፣ የአንድ እግዚአብሔር ልጆች እና ወንድማማቾች እንድንሆን የጓዳሉፔዋ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትርዳን በማለት፣ ሴሚናሩን ለሚከታተሉ የላቲን አሜሪካ አገሮች ተወካዮች መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።              

20 November 2020, 08:47