ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ለቤተክርስቲያን አገልጋይ አባቶች የካርዲናልነት ማዕረግ ሲሰጡ                ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ለቤተክርስቲያን አገልጋይ አባቶች የካርዲናልነት ማዕረግ ሲሰጡ  

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ የመስቀል መንገድ እና የዓለም መንገድ የተለያዩ መሆናቸውን ገለጹ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ቅዳሜ ኅዳር 19/2013 ዓ. ም. በሮም፣ ቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ በተካሄደው ስነ-ስርዓት ላይ ከስምንት አገራት ለተመረጡት አሥራ ሦስት የቤተክርስቲያን አገላጋዮች የካርዲናልነት ማዕረግ ሰጥተዋል። ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያንን በበላይነት ለመምራት ሐዋርያዊ ስልጣን ከተቀበሉበት ጊዜ ወዲህ ለሰባተኛ ጊዜ በሰጡት የካርዲናልነት ማዕረግ ስነ-ስርዓት ላይ ባሰሙት መልዕክት የመስቀል መንገድ እና ዓለማዊ መንገድ ሁለት የተለያዩ መንገዶች መሆናቸውን ገልጸው፣ ቀይ ቀለም ያለው የካርዲናልነት ማዕረግ አልባስ የደም ምልክት ሲሆን ይህም በሕይወት መካከል ሊያጋጥም የሚችለውን ስቃይ እና ሞት በደስታ ለመቀበል ዝግጁ መሆንን የሚያመለክት መሆኑን አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በስነ-ስርዓቱ መጀመሪያ ላይ፣ የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብጹዕ አቡነ ማርዮ ግሬክ፣ ተሿሚ የቤተክርስቲያን አገልጋይ አባቶችን በመወከል ለቅዱስነታቸው ሰላምታ አቅርበውላቸዋል። ቀጥሎም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በማር. 10: 35-45 ላይ የተጻፈውን በማስታወስ፣ በዚህ የወንጌል ክፍል ላይ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ኢየሩሳሌም በተቃረበ ጊዜ ለአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት፣ እርሱን ስለሚደርስበት መከራ፣ ሞት እና ትንሳኤ የተናገረውን አስታውሰዋል። በዚህ የወንጌል ክፍል ላይ ኢየሱስ ንግግሩን ካጠቃለለ በኋላ ሁለቱ ሐዋርያት፣ ያዕቆብ እና ዮሐንስ ወደ ኢየሱስ ቀርበው፣ በመንግሥቱ ክብር በግራው እና በቀኙ እንዲያስቀምጣቸው በጠየቁት ጊዜ ኢየሱስም “የምትለምኑትን አታውቁም፤ እኔ የምጠጣውን የመከራ ጽዋ መጠጣት ትችላላችሁ? እኔስ የምጠመቀውን ጥምቀት ትጠመቃላችሁ”? ካላቸው በኋላ “ነገር ግን በቀኜ እና በግራዬ መቀመጥን የምፈቅደው እኔ አይደለሁም፤ ይህ የሚሰጠው ለተዘጋጀላቸው ብቻ ነው።” ማለቱን አስታውሰዋል።

ቤተክርስቲያን የምትጓዝበት መንገድ

ርዕሠ ሊቃነ ፍራንችስኮስ ስብከታቸውን በመቀጠል፣ መንገዳችን ሁል ጊዜ ቤተክርስቲያን የምትጓዝበት መንገድ መሆኑን አስረድተው፣ ኢየሱስ ክርስቶስ የተጓዘበት የኢየሩሳሌም መንገድ ዘወትር ከፊታችን ይገኛል ብለው፣ የኢየሱስ ክርስቶስ የመስቀል ላይ ስቃይ እና መከራ እንዲሁም ትንሳኤው ከክርስትና ታሪካችን መካከል አንዱ መሆኑን ገልጸዋል። በማርቆስ ወንጌል ላይ የተጠቀሰው ቃል፣ አዳዲስ ካርዲናሎች በሚሾሙበት ጊዜ ዘወትር የሚታወስ መሆኑን ገልጸው፣ ይህም ጉዞአችንን የሚያመላክት፣ ይህን ጉዞ በኢየሱስ ክርስቶስ መሪነት ከእርሱ ጋር የምንጓዝ መሆናችንን የሚያሳይ፣ ለሕይወታችን እና ለሐዋርያዊ አገልግሎታችን ኃይል የሚሆነን ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን ያረጋግጥልናል ብለዋል።

ኢየሱስ የተከታዮችን ስጋት ስለሚገነዘብ ብቻቸውን አይተዋቸውም

“ኢየሱስን መከተል የሚወድ ይህን የወንጌል ቃል ማስታወስ ይኖርበታል” ያሉት ቅዱስነታቸው፣ ደቀ መዛሙርቱ በኢየሱስ ንግግር የተደናገጡ ቢሆንም በኢየሩሳሌም የሚጠብቃቸው ድንጋጤ ምን ያህል መሆኑን ስለተገነዘበ ብቻቸውን የማይተዋቸው መሆኑን አስረድተዋል። “እርሱን የሚከተሉት ሰዎች ሕይወት ምን እንደሚመስል ኢየሱስ ስለሚያውቅ ጥበቃውን አያጎድልባቸውም፣ መከራንም የተቀበለው እኛን ለማዳን ነው” ካሉ በኋላ ለአስራ ሁለቱ ሐዋርያት የተናገረውም የሚደርስባቸውን መከራ ለመሸከም ዝግጁ እንዲሆኑ ለማድረግ መሆኑንም አስረድተዋል።

የኢየሱስ ክርስቶስ መንገድ አንድ ብቻ ናት

“ኢየሱስ ክርስቶስ እርሱን የሚከተሉት በሙሉ ከእርሱ እንዳይርቁ ይፈልጋል” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ የኢየሱስ ክርስቶስ መንገድ የመከራ፣ የስቃይ እና የሞት መንገድ መሆኑን አስረድተው “ይህም ኢየሱስም የሚታወቅበት ብቸኛው የሕይወት መንገድ ነው” ካሉ በኋላ ሁለቱ ሐዋርያት፣ ያዕቆብ እና ዮሐንስ ለመጓዝ የተመኙት መንገድ ግን ከዚህ የተለየ መሆኑን አስረድተዋል።

ዘወትር ነቅቶ መጠበቅ መልካም ነው

የሁለቱን ሐዋርያት፣ የያዕቆብ እና የዮሐንስ ጥያቄ፣ ምናልባትም የሌሎችን ደቀ መዛሙርት ጥያቄ ኢየሱስ ክርስቶስ ያልተቀበለበት ምክንያት፣ ከተዘጋጀላቸው መንገድ ወጣ ለማለት መፈላጋቸውን ስለተገነዘበ መሆኑን የገለጹት ቅዱስነታቸው፣ ይህ ምኞት በሁላችን ልብ ውስጥ ሊከሰት እንድሚችል አስረድተው፣ ኢየሱስ ክርስቶስን የምንወድ፣ እርሱን መከተል የምንፈልግ ቢሆንም፣ እግራችን እርሱ ባዘጋጀልን መንገድ ቢራመድም፣ በአካልም ከእርሱ ጋር ብንሆን፣ ነገር ግን ልባችን ከእርሱ ሊርቅ ስለሚችል ከእርሱ መንገድ እንዳንወጣ ዘወትር ነቅተን መቆም ያስፈልጋል ብለዋል።

ቤተክርስቲያን ዘወትር ማስታወስ ያለባት አንድ ቃል አለ

ኢየሱስ ባዘጋጀው መንገድ እና ሐዋርያቱ መጓዝ በፈለጉበት መንገድ መካከል ትልቅ ልዩነት መኖሩን ያስረዱት ቅዱስነታቸው፣ ኢየሱስ ክርስቶስ የመከራ እና የስቃይ መንገድ ከተጓዘ በኋላ እንደሞተ እና ከሞትም እንደተነሳ ሁሉ፣ እርሱን ለመከተል የወደዱትን ሁሉ የትንሳኤው ተካፋዮች ይሆኑ ዘንድ ኢየሱስ ወደ ራሱ መንገድ የሚመልሳቸው መሆኑን አስረድተዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው መጨረሻ እንዳስገነዘቡት “እኛ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት እና ካርዲናሎች በዚህ የእውነት ቃል በኩል እራሳችንን መመልከት አለብን” ብለው፣ የሚደርስብን ስቃይ ከፍተኛ ህመምን የሚያስከትል ቢሆንም ከቁስላችን ድነን በነጻነት ወደ አዲስ ሕይወት መግባት እንችላለን ብለዋል። “አዲስ ሕይወት ማግኘት የምንችለው በእግዚአብሔር መንገድ መጓዝ ስንችል ነው” ብለዋል።

ጸሎት ወደ እመቤታችን ቅድስት ማርያም

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ስብከታቸውን ካጠቃለሉ በኋላ ወደ መንበረ ታቦት ፊት ለቀረቡት አዲስ ለተሾሙት ካርዲናሎች የካርዲናልነት ማዕረግ መለያ ምልክት ሰጥተው ጸሎት ካደረሱ በኋላ ቡራኬአቸውን ሰጥተዋቸዋል። በመጨረሻም ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቅዱስ ምስል ፊት ቀርበው ጸሎታቸውን ካቀረቡ በኋላ የስነ-ስርዓቱ ፍጻሜ ሆኗል።        

28 November 2020, 15:00