ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ 

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ እኛ ሁላችንም ቅዱሳን እንድንሆን ተጠርተናል አሉ!

የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ በጥቅምት 22/2013 ዓ.ም “የሁሉም ቅዱሳን” ዓመታዊ በዓል በታላቅ መንፈሳዊነት ተከብሮ ማለፉ ይታወቃል። ይህ በዓል በቫቲካን በተከበረበት ወቅት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ይህንን “የሁሉም ቅዱስ” በዓል ለማክበር ለተሰበሰቡ ምዕመናን እና የሀገር ጎብኝዎች ቅዱስነታቸው በዕለቱ ከመጽሐፍ ቅዱስ ተወስደው በተነበቡ ምንባባት ላይ ተመስርተው ባሰሙት አስተንትኖ እንደ ገለጹት “እኛ ሁላችንም ቅዱሳን እንድንሆን ተጠርተናል” ማለታቸውን ለመረዳት ተችሉዋል።

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ታዳሚዎች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በጥቅምት 22/2013 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡ ምዕመናን እና የሀገር ጎብኝዎች በእለቱ የተከበረውን “የሁሉም ቅዱሳን” ዓመታዊ ክብረ በዓል አስመልክተው ያሰሙትን አስተንትኖ ሙሉ ይዘት እንደ ሚከተለው ተርጉመነዋል አባራችሁን በመሆን እንድትከታተሉ ከወዲሁ እንጋብዛለን።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

በዚህ በተከበረው የሁሉም ቅዱሳን በዓል ላይ ቤተክርስቲያን በክርስቶስ ትንሳኤ ላይ የተመሠረተውን ታላቅ ተስፋን ፣ በክርስቶስ ከሙታን መነሳት ላይ መሰረቱን ባደረገው ታላቅ ተስፋን እንድናጤን ትጋብዛለች-ክርስቶስ ተነስቷል እኛም ከእርሱ ጋር እንሆናለን ፣ እርሱም ከእኛ ጋር ይሆናል። ቅዱሳን እና ብጹዕን የክርስቲያን ተስፋ ጠንካራ ምስክሮች ናቸው። ምክንያቱም በሕይወታቸው ውስጥ በደስታ እና በመከራ ውስጥ ሆነው ሙሉ በሙሉ ስለኖሩ ፣ ኢየሱስ በተራራ ላይ የሰበከውን ለብጽዕና የሚያበቃውን አስተምህሮ በተግባር ላይ ስላዋሉትም ጭምር ነው (ማቴ 5 1-12 ይመልከቱ)። በእውነቱ በቅዱስ ወንጌል ውስጥ የተጠቀሱት የብጽዕና መገለጫዎች ወደ ቅድስና የሚወስዱ መንገዶች ናቸው። አሁን ደግሞ በሁለተኛው እና ሦስተኛው የብጽዕና መገለጫ ላይ ማተኮር እፈልጋለሁ።

ሁለተኛው የብጽዕና መንገድ “የሚያዝኑ ብፁዓን ናቸው መጽናናትን ያገኛሉና” (ማቴ 5፡ 4) የሚለው ነው። እነዚህ ቃላት የሚቃረኑ ይመስላሉ፣ ምክንያቱም ሀዘን የደስታ እና የሐሴት  ምልክት አይደለም። የልቅሶ ምክንያቶች የሚመጡት ከስቃይና ሞት ፣ ከበሽታ ፣ ከሥነ ምግባራዊ ችግር ፣ ከኃጢአት እና ከስህተቶች ነው-በቀላሉ ከዕለት ተዕለት ኑሮ በመለስተኛነት ፣ በድክመት እና በችግር ውስጥ የሚንጸባረቅ ሲሆን አንዳንድ ጊዜ ምስጋና ከጎደለው ሕይወት እና በአለመግባባት ከቆሰለ እና ከታመመ ሕይወት የሚመነጭ ነው። ኢየሱስ በዚህ እውነታ ላይ የሚያዝኑትን ፣ ምንም እንኳን እነዚህ ሁሉ ችግሮች አብረው የሚኖሩ ቢሆኑም እንኳን በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሁነው በጌታ የሚታመኑ እና ራሳቸውን በእርሱ ጥላ ስር ያደረጉ ሰዎች እንደ ሚባረኩ ያውጃል። እነሱ ግድየለሾች አይደሉም ፣ ወይም ህመም በሚሰማቸው ጊዜ ልባቸውን የሚያደነድኑ ሰዎችም አይደሉም፣ ነገር ግን በትእግስት በእግዚአብሔር መጽናኛ ላይ ተስፋ ያደርጋሉ። እናም በዚህ ህይወት ውስጥ እንኳን ይህንን መጽናናት ይለማመዳሉ።

በሦስተኛው የብጽዕና መንገድ ውስጥ ኢየሱስ “የዋሆች ብፁዓን ናቸው ምድርን ይወርሳሉና” ይላል (ማቴዎስ 5፡5)። ወንድሞች እና እህቶች የዋህነት! የዋህነት ስለራሱ የተናገረው የኢየሱስ ባሕርይ ነው “እኔ የዋህ እና ልበ ትሑት ነኝና ከእኔ ተማሩ” (ማቴ 11 29) በማለት ተናግሮ ነበር። የዋሆች ራሳቸውን እንዴት እንደሚቆጣጠሩ የሚያውቁ ፣ ለሌላው ቦታን የሚሰጡ፣ ሌላውን የሚያዳምጡ ፣ የሌላውን የአኗኗር ዘይቤ ፣ ፍላጎቶቹን እና ጥያቄዎቹን የሚያከብሩ ሰዎች ናቸው። እነሱ ሌላውን ለማጨናነቅ ወይም ለማሳነስ አይፈልጉም ፣ በሁሉም ነገር ላይ ለመሆን ወይም የበላይ ለመሆን አይፈልጉም ፣ ሀሳቦቻቸውን ወይም የራሳቸውን ጥቅም በሌሎች ላይ ለመጫን አያስገድዱም። እነዚህ ሰዎች ለአለም እና አለማዊ ለሆኑ አስተሳሰቦች አድናቆት የሌላቸው ሰዎች ሲሆኑ እንደነዚህ ያሉ ሰዎች ደግሞ በእግዚአብሔር ፊት ውድ ናቸው። እግዚአብሔር ቃል የገባላቸውን ምድር እንደ ርስት ማለትም የዘላለም ሕይወት ይሰጣቸዋል። ይህ የብጽዕና መንገድ ከዚህ የሚጀምር ሲሆን በክርስቶስ ተፈጽሟል። ነገር ግን የዋህነት… በህይወት ውስጥ በዚህ ጊዜ ፣ ​​በዓለም ውስጥም ቢሆን ፣ በጣም የተጋነነ ሁኔታ አለ ፣ በዕለት ተዕለት ሕይወትም እንዲሁ ፣ ከእኛ የሚወጣው የመጀመሪያው ነገር የሚደርስብንን ነገር ለመከላከል ውኔውን እናጣለን፣ በቅድስና ጎዳና ለመራመድ የዋህነት ያስፈልገናል። ማዳመጥ ፣ ማክበር፣ ጥቃት መፈጸም ሳይሆን፣ በትዕግስት መኖር የዋህነት ነው።

ውድ ወንድሞች እና እህቶች ፣ ንፅህናን ፣ የዋህነትን እና ምህረትን መምረጥ; በመንፈስ ድህነት እና በመከራ ውስጥ እራስዎን ለጌታ አደራ ለመስጠት መምረጥ፣ ለፍትህና ለሰላም ራስን መወሰን - ይህ ሁሉ ማለት የዚህን ዓለም አስተሳሰብ ፣ የማግበስበስ ባህልን ፣ ትርጉም የለሽ ደስታን ፣ በአቅመ ደካሞች ላይ በእብሪተኝነት የሚፈጸሙ ተግባራትን በተመለከተ እነዚህን ተግባራት መቃወምን ያመለክታል። ይህ የቅዱስ ወንጌል መንገድ ቅዱሳን እና ብጹዕና የተራመዱበት መንገድ ነው። የሁሉም ቅዱሳን የሚያከብር የዛሬው ክብረ በዓል የግል እና ሁለንተናዊ ጥሪን በቅድስና መንገድ ላይ በመራመድ እንድንኖር ያስታውሰናል ፣ እናም እያንዳንዱ ሰው ልዩ በሆነ ሁኔታ በተጠራበት መንገድ ላይ ይጓዝ ዘንድ ትክክለኛውን መንገድ ያመላክታል። በቅዱሳን መካከል ስላሉ የማይጠፉ ስጦታዎች እና እውነተኛ የሕይወት ታሪኮች ማሰብ በቂ ነው-እነሱ እኩል አይደሉም ፣ እያንዳንዳቸው የራሳቸው ስብዕና ያላቸው እና እንደየራሳቸው ባህሪ የቅድስና ሕይወታቸውን ያዳበሩ ፣ እያንዳንዳችንም ይህንን መንገድ መምረጥ የሚገባን ሲሆን የትህትናን መንገድ በመከተል ወደ ቅድስና ሕይወት መጓዝ እንችላለን።

እነዚህ እጅግ በጣም ብዙ የክርስቶስ ታማኝ ደቀ መዛሙርት ቤተሰብ እናት የሆነች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አለቻቸው። የሁሉም ቅዱሳን ንግሥት በሚል መጠሪያ እርሷን እናከብራታለን። ነገር ግን ከሁሉም በፊት እርሷ ልጆቿን እንዴት መቀበል እና መከተል እንደምንችል የምታስተምር እናት ናት። ወደ ብጽዕና በሚወስደን መንገድ ላይ መጓዝ አንችል ዘንድ እርሷ በአማላጅነቷ ትርዳን።

01 November 2020, 12:50