ፈልግ

እ.አ.አ በጥር 21/2020 ዓ.ም ለክርስቲያኖች ሕብረት ጸሎት በተደረገበት ወቅት እ.አ.አ በጥር 21/2020 ዓ.ም ለክርስቲያኖች ሕብረት ጸሎት በተደረገበት ወቅት  

ስለ ክርስቲያኖች አንድነት የሚደረግ ውይይት

ለክርስቲያኖች አንድነት ዝግጁ መሆን ‹‹ሁሉም አንድ ይሆኑ ዘንድ›› (ዮሐ.17፡21) ለሚለው ለጌታ ኢየሱስ ጸሎት ምላሽ መስጠት ነው፡፡ ክርስቲያኖች መከፋፈላቸውን ቢያስወግዱና ‹‹በጥምቀት አንድ ቢሆኑ እንኳ ቤተክርስቲያን ከእርስዋ ሙሉ ኅብረት በተለዩ ልጆችዋ ውስጥ የሚገባትን የሁሉን አቀፍነት ሙላት›› (ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ፣ ኡኒታቲስ ሬድእንቴግራስዩ (እንደገና አንድ መሆን) የተሰኘ የክርስቲያኖች አንድነት ድንጋጌ ፣4) ልታገኝ ብትችል የክርስትና መልእክት ተአማኒነት እጅግ የበለጠ ይሆናል፡፡ በመንፈሳዊ ጉዞ ላይ አብረን የምንጓዝ መሆናችንን ከቶ መርሳት የለብንም፡፡ ይህም ማለት አብረውን በሚጓዙ መንፈሳዊ ተጓዦች ላይ ጽኑ እምነት ሊኖረን ይገባል፤ ጥርጣሬን ወይም አለመተማመንን ወደ ጎን ትተን ሁላችንም ወደምንሻው ነገር፣ ማለትም በሰላም ወደሚያበራ የእግዚአብሔር ፊት ዐይናችንን ማዞር አለብን፡፡ ሌሎችን ማመን ጥበብ ነው፣ ሰላም ጥበብ ነው፡፡ ኢየሱስ እንደሚነግረን፣ ‹‹ሰላምን የሚያውዱ ብፁዓን ናቸው›› (ማቴ.5፡9)፡፡ እኛም በመካከላችን ይህን ሥራ ተቀብለን ‹‹ሰይፋቸውን ቀጥቅጠው ማረሻ ያደርጉታል›› (ኢሳ.2፡4) የሚለውን የጥንቱን ትንቢት እንፈጽማለን፡፡

ከዚህ አንጻር፣ የክርስቲያኖች አንድነት ለሰው ልጅ አንድነት አስተዋጽኦ ያደርጋል ማለት ይቻላል፡፡ የቁስጥንጥንያ ፓትሪያርክ ብፁዕ በርቶሎሜዎስ ቀዳማዊና የካንተርበሪው ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ሮዋን ዊሊያምስ በሲኖዶሱ ላይ መገኘታቸው ከእግዚአብሔር የተሰጠ እውነተኛ ስጦታና ታላቅ የክርስትና ምስክርነት ነበር፡፡

በክርስቲያኖች መካከል በተለይ በእስያና በአፍሪካ ያለው የወንጌል ምሥክርነት የማይሰጥ መከፋፈል ከባድ በመሆኑ ወደ አንድነት የሚመሩ መንገዶችን የመፈለጉ ጉዳይ ከመቼውም ጊዜ በላይ አስቸኳይ ሆኗል፡፡ በእነዚያ አህጉራት የሚገኙ የወንጌል ልዑካን ብዙውን ጊዜ የክርስቲያኖችን የመከፋፈል ነቀፋ የሚያስከትላቸውን ትችቶች፣ ቅሬታዎችና ሽሙጦች ይጠቅሳሉ፡፡ በምንጋራቸው እምነቶች ላይ ብናተኩርና የእውነቶችን የደረጃ መርሆ ብናስተውል ስብከትን፣ አገልግሎትንና ምስክርነትን በጋራ ለመግለጽ ወደሚያስችል ደረጃ በቁርጠኝነት መጓዝ እንችላለን፡፡ የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል ያልተቀበሉ አያሌ ሕዝቦች ቸልተኞች እንድንሆን አይፈቅዱልንም፡፡ ስለዚህ፣ ኢየሱስ ክርስቶስን እንዲቀበሉ ለሚረዳቸው አንድነት ዝግጁ መሆን የተራ ዲፕሎማሲ ወይም የግዴታ ታዛዥነት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፣ ወደ ስብከተ ወንጌል የሚመራ ወሳኝ መንገድ ነው፡፡ ሁከት በሰፈነባቸው አገሮች በሚኖሩ ክርስቲያኖች መካከል ያሉ የመከፋፈል ምልክቶች የሰላም እርሾ መሆን በሚገባቸው በኩል ለተጨማሪ የግጭት ምክንያቶች ይሆናሉ፡፡ አንድ የሚያደርጉን በርካታ ጠቃሚ ነገሮች አሉ! በሙሉ ነጻነት በሚሠራው በመንፈስ ቅዱስ ሥራ በእውነት ካመንን እርስ በርሳችን ብዙ እንማራለን! ቁም ነገሩ ስለ ሌሎች የተሻለ መረጃ ማግኘት ሳይሆን፣ መንፈስ ቅዱስ በእነርሱ ውስጥ የዘራውንና ለእኛም ስጦታ የሆነውን ፍሬ ሀሳብ መሰብሰብ ነው፡፡ አንድ ምሳሌ ለመጥቀስ ያህል፣ እኛ ካቶሊካውያን ከኦርቶዶክስ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጋር በምናደርገው ውይይት ስለ ኤጲስ ቆጶሳዊ ግንኙነትና ስለ ሲኖዶስ ምንነት በይበልጥ የመማር ዕድል አለን፡፡ በምናደርገው የስጦታ ልውውጥ አማካይነት መንፈስ ቅዱስ ወደ ሙሉ እውነትና ርኅራኄ ይመራናል፡፡

ምንጭ፡ የወንጌል ደስታ የተሰኘ የቅዱስ አባታችን ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በዛሬው ዓለም ወንጌልን ስለ መስበክ ለጳጳሳት፣ ለካህናት፣ ለደናግልና ለምእመናን ያስተላለፉት ሐዋርያዊ  ምክር። ከአንቀጽ 244-246

20 November 2020, 11:32