ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ “ስልጣን ሌሎችን ለማገልገል እንጂ ለመጨቆን የተሰጠ አይደለም"

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እሁድ መስከረም 24/2013 ዓ. ም፣ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተገኙት ምዕመናን፣ በዕለቱ በተነበበውን የቅዱስ ወንጌል ክፍል ላይ በማስተንተን ስብከታቸውን አሰምተዋል። በዕለቱ ያቀረቡት አስተንትኖ ከማቴ. 21፡33-43 ላይ የተወሰደ ሲሆን ይህም፥ “የወይን እርሻው ባለቤት በእርሻው ዙሪያ አጥር አጥሮ፣ ለወይኑ መጭመቂያ ጉድጓድ ቆፍሮ፣ ለጥበቃ የሚሆን ማማ ሠርቶ፣ ከዚያም ዕርሻውን ለገበሬዎች አከራይቶ ወደ ሌላ አገር ሄደ” በሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ መሠረት ያደረገ አስተንትኖ እንደ ነበር ተገልጿል። በዚህም ምሳሌ የወይን እርሻው፥ እግዚአብሔር ስለመረጣቸው ሰዎች ነው የሚያመለክተው። በወይን እርሻው ባለቤት የተላኩት አገልጋዮች ደግሞ በእግዚአብሔር ስለ ተላኩት ነቢያት ነው የሚናገረው፤ የባለቤቱ ልጅ ደግሞ የሚያመለክተው ክርስቶስን ነው። እንዲሁም ሥልጣን አገልግሎት ነው፤ ለሁሉም መልካምን በማድረግ የሚተገበር እና ወንጌልን ከቀደመው በተሻለ ሁኔታ ለማሰራጨት የተሰጠም ነው ማለታቸውን ተገልጿል።

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዕለቱ ያደረጉትን አስተንትኖ ትርጉም ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል።

የቫቲካን ዜና፤

"የተወደዳችሁ ወንድቼ እና እህቶቼ! እንደምን አረፈዳችሁ!

በዛሬው የወንጌል ክፍል (በማቴ. 21፡33-43) ጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ሞቱ እና ስቃዩ አስቀድሞ ያሳወቀበት ነው። ከመግደል የማይመለሱ የወይን እርሻ ገበሬዎች ምሳሌ በመናገር፥አቅጣጫቸውን ስለ ሳቱት ጻፍቶች እና ሽማግሌዎች የተናገረበት ቦታ ነው። በእርግጥም ስለ እርሱ መጥፎ አስተሳሰብ ነበራቸውና ሊያጠፉትም ይፈልጉ ነበር።

በዚህ የወንጌል ክፍል የተነገረው የወይን እርሻ ገበሬዎች ምሳሌ፥ በእርሻው ዙሪያ አጥር አጥሮ፤ ለወይኑ መጭመቂያ ጉድጓድ ቆፍሮ፤ ለጥበቃ የሚሆን ማማ ሠርቶ፣ ከዚያም ዕርሻውን ለገበሬዎች አከራይቶ ወደ ሌላ አገር ስለ ሄደ የወይን እርሻ ባለቤት ነው የሚያወሳው። (ማቴ. 21፥33) በመቀጠልም የመከር ወራት ሲደርስ፣ ፍሬውን ለመቀበል አገልጋዮቹን ወደ ገበሬዎቹ ላካቸው። ገበሬዎቹም አገልጋዮቹን ይዘው አንዱን ደበደቡት፤ ሌላውን ገደሉት፤ ሌላውን ደግሞ በድንጋይ ወገሩት። እርሱም ከፊተኞቹ የሚበልጡ ሌሎች አገልጋዮቹን ላከ፤ ገበሬዎቹም ተመሳሳይ ድርጊት ፈጸሙባቸው። በመጨረሻም ልጄን ያከብሩታል በማለት ልጁን ላከ። ነገር ግን ገበሬዎቹ ልጁን ባዩት ጊዜ፣ ይህማ ወራሹ ነው፤ ኑ እንግደለውና ርስቱን እንውረስ ተባባሉ። ይዘውም ከወይኑ እርሻ ውጭ አውጥተው ገደሉት (ማቴ. 21፡37-39)።

በዚህም ምሳሌ የወይን እርሻው፥ እግዚአብሔር ስለመረጣቸው እና በእንክብካቤ ስለ ሠራቸው ሰዎችን ያመለክታል። በወይን እርሻው ባለቤት የተላኩት አገልጋዮች ደግሞ በእግዚአብሔር ስለ ተላኩት ነቢያት ነው የሚናገረው፤ የባለቤቱ ልጅ ደግሞ የሚያመለክተው ክርስቶስን ነው። ነብያትም ተቀባይነት እንዳላገኙት ሁሉ ክርስቶስ ደግሞ ተቀባይነትን ካለማግኘትም ባሻገር ተገደለ።

በዚህ ምሳሌ መጨረሻ አካባቢም፥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሕዝቡን ለሚመሩት ጥያቄ አቀረበላቸው።ይኸውም “ታድያ የወይኑ እርሻ ባለቤት ሲመጣ እነዚያን ገበሬዎች ምን የሚያደርጋቸው ይመስላችኋል?” አላቸው (ማቴ. 21፥40)። እነርሱም እንዲህ በማለት መለሱለት፤ “እነዚያን ክፉዎች በአሰቃቂ ሁኔታ ገድሎ ከወይኑ እርሻ ተገቢውን ፍሬ በወቅቱ ለሚያስረክቡት ለሌሎች ገበሬዎች ያከራያል” አሉት (ማቴ. 21፥41)።

በዚህ ከባድ ምሳሌ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በውይይቱ ለነበሩ ሰዎች ሃላፊነትን በአግባቡ መወጣት ይችሉ ዘንድ ትምህርትን እንዲያገኙ ነበር ፊት ለፊት የገጠማቸው። ነገር ግን የዚህ ምሳሌ አስተምህሮ በዘመኑ የነበሩ ክርስቶስን ያልተቀበሉት ሰዎችን ብቻ አይደለም የሚመለከተው። ይሁን እንጂ በዘመናችንም እኛንም የሚመለከት መሆኑን መዘንጋት የለብንም። በመሆኑም ዛሬም እግዚአብሔር በወይኑ እርሻ እንዲሠሩ ከተላኩት መልካም ፍሬን ይጠብቃል።

በየትኛውም ዘመን እግዚአብሔር ሕዝቡን እንዲመሩ ሥልጣን የሰጣቸው ሰዎች የእግዚአብሔርን እቅድ ትተው የራሳቸውን ፍላጎት ሊፈጽሙ ይችላሉ። ነገር ግን የወይን አትክልት እርሻው የእግዚአብሔር እንጂ የእኛ አይደለም። ሥልጣን አገልግሎት ነው፤ ለሁሉም መልካምን በማድረግ የሚተገበር እና ወንጌልን ከቀደመው በተሻለ ሁኔታ ለማሰራጨት የሚጠቅም ነው።

በዛሬው ሥርዓተ ሉጥርጊያ ሁለተኛው ንባብ መሠረት ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በእግዚአብሔር የወይን አትክልት እርሻም መልካም ሠራተኞች መሆን እንዳለብን ያስተምራል። በመሆኑም በፊሊጵስዮስ መልዕክቱ ምዕራፍ 4፥8 ላይ እንዲህ ይላል፤ “በቀረውስ ወንድሞች ሆይ፥ እውነተኛ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ጭምትነት ያለበትን ነገር ሁሉ፥ ጽንቅ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ንጹሕ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ፍቅር ያለበትን ነገር ሁሉ፥ መልካም ወሬ ያለበትን ነገር ሁሉ፥ በጎነት ቢሆን ምስጋናም ቢሆን፥ እነዚህን አስቡ” በማለት ይመክራል።በዚህም መሠረት ቤተክርስቲያንም በቅድስና የበለጸገች ትሆናለች። በፍጹም ፍቅሩ ለሚደግፈን እግዚአብሔር አብ፣ በመስቀሉ ላዳነን እግዚአብሔር ወልድ እንዲሁም መልካምነትን በሙላት እንድንኖር ልባችንን ለሚከፍትልን መንፈስ ቅዱስ ክብር እና ምስጋና ይሁን።

ወደ እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተመልሰን በፖምፔ ምልጃን ከሚያቀርቡት አማኞችጋር አንድ ላይ በመሆን እንጸልይ። በዚህ ወርም በመታደስ የመቁጠሪያ ጸሎት እናድርግ።”

05 October 2020, 11:44