ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፥ “የእያንዳንዱ ምዕመን ጸሎት በእግዚአብሔር ዘንድ ተሰሚነት አለው”

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ጥቅምት 4/2013 ዓ. ም. ሳምንታዊውን የረቡዕ ዕለት የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምሮአቸውን አቅርበዋል። በቫቲካን ውስጥ በሚገኘው በቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ የመስብሰቢያ አዳራሽ ለተሰበሰቡት ምዕመናን ያቀረቡት አስተምህሮ ስለ ጸሎት በሚያስተምረው በመዝሙረ ዳዊት መጽሐፍ ላይ መሠረት ያደረገ እንደነበር ለመገንዘብ ተችሏል። ቅዱስነታቸው በዛሬ አስተምህሮአቸው እንደገለጹት፣ በጸሎት ወደ እግዚአብሔር ስንቀርብ እንደማንነታችን መሆነ እንዳለብን ገልጸው፣ በችግርም ሆነ በማንኛውም ሕይወት ውስጥ ሆነው ጸሎታቸውን የሚያቀርቡትን እግዚአብሔር ሳይተዋቸው የሚያደምጣቸው መሆኑን አስረድተዋል።

የቫቲካን ዜና፤

ባለፈው ሳምንት ስለ ጸሎት የጀመሩትን የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸውን በመቀጠል፣ በብሉይ ኪዳን መጽሐፍት ውስጥ የሚገኘው የመዝሙረ ዳዊት መጽሐፍ በርካታ ጸሎቶች የሚገኙበት እና እንዴትም መጸለይ እንዳለብን የሚያስተምር መሆኑንም አስረድተዋል።

“በመዝሙረ ዳዊት መጽሐፍ ውስጥ ሁሉንም የሰው ልጅ ስሜቶች እናገኛለን፤ ደስታን፣ ሐዘንን፣ ጥርጣሬን፣ ተስፋን እና በሕይወታችን ውስጥ ሊያጋጥሙን የሚችሉትን ሁሉ እናገኛለን። ትምህርተ ክርስቶስ እንደሚያረጋግጥልን በመዝሙረ ዳዊት መጽሐፍ ውስጥ የተገለጹት መዝሙሮች፣ ሁሉም ሰው በማንኛውም ቦታ እና ጊዜ ላይ ሆኖ ማቅረብ የሚችለውን የጸሎት ዓይነቶችን የያዘነው”።

በጸሎት ውስጥ እያንዳንዱ ስሜታችን ቦታ አለው፤

በመዝሙረ ዳዊት መጽሐፍ ውስጥ ስሜታችንን የምንገልጽበት፣ ውዳሴን እና ምስጋናን የምናቀርብበት፣ በደስታ እና በመከራ ጊዜ ሆነን ልመናችንን ወደ እግዚአብሔርን የምናቀርብበትን ቃል እናገኛለን። በዚህ መጽሐፍ ውስጥ እውነተኛ የሕይወት ልምድ ያላቸውን ሰዎች ብቻ እናገኛቸዋለን።

"ጸሎታችንን ወደ እግዚአብሔር ማቅረብ ስንፈልግ እንደ ማንነታችን መቅረብ አለብን። በሚገባ ለመጸለይ ከፈለግን ጸሎታችን የምንገኝበትን ሁኔታ የሚገልጽ መሆን ይኖርበታል። በጸሎት ወደ እግዚአብሔር ስንቀርብ፣ እኛ ራሳችን ብቻ የምናውቃቸውን ውስጣዊ ችግሮቻችንን ሆነ መልካም ነገሮቻችንን ይዘን መቅረብ ያስፈልጋል"።          

መከራዬ እስከ መቼ ይሆን?

በጸሎት በኩል ከምናቀርባቸው በርካታ ጥያቄዎች መካከል አንዱ፥ “ጌታ ሆይ! ይህን መከራ እስከ መቼ ልታገሰው”? በማለት ስንት ጊዜ ጸልየናል? ያሉት ቅዱስነታቸው፣

"የእያንዳንዱ ምዕመን ጸሎት በእግዚአብሔር ዘንድ ትርጉም አለው ብለው፣ በጸሎት ወደ እግዚአብሔር ዘንድ ስንቀርብ፣ እግዚአብሔር በቸርነት ዓይኖቹ ስለሚመለከተን እና ስለሚሰማን ወደ እርሱ እንሄዳለን ብለዋል። ወደ እግዚአብሔር ዘንድ እንድንቀርብ በውስጣችን ያለው መንፈስ ቅዱስ ስለሚገፋፋን ነው፤ የእግዚአብሔር ውድ ልጆች በመሆናችን እና እግዚአብሔርም ይህን ስለሚመለከት ወደ እርሱ በጸሎት እንቀርባለን"።

ምዕመናን የእግዚአብሔርን እገዛ ለመለመን፣ በሕይወት የሚያጋጥማቸውን ችግሮች በሙሉ፣ የጥላቻን፣ የጦርነትን፣ የስቃይን፣ እምነት የማጣትን እና የሞት ታሪክን እና የተለያዩ ገጠመኞቻቸውን ይዘው ይቀርባሉ። መዝሙረ ዳዊትን የሚደግም ሰው፣ የማይጠቅሙ እና የሚጎዱ ነገሮችን በመዘርዘር፣ እግዚአብሔርም በምሕረት ዓይኖቹ ተመልክቶት ከክፉ ነገሮች እንዲያድነው በማለት ይጸልያል። ጸሎት የእግዚአብሔር የማዳን ኃይል የሚጀምርበት ደረጃ መሆኑን የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የሰዎችን ስቃይ ምንነት ሲያስረዱ፥

"እግዚአብሔር እንደሚያግዘው የሚያምን ወይም የማያምን ሰው ቢሆን፣ በመዝሙሩ አማካይነት ስቃዩ ከእግዚአብሔር ጋር ግንኙነትን እንዲፈጥር ያደርገዋል። እርዳታ የሚጠይቅ ዋይታ ተደማጭነትን ያገኛል እንጂ እንዲሁ አይቀርም። ስቃዮቻችንም ቢሆኑ የተፈጥሮ ሕግን ተከትለው የሚያጋጥሙን ሳይሆን እንባችንን በማፍሰስ ዕርዳታን የምንጠይቅባቸው ናቸው"።

እግዚአብሔር በስማችን ያውቀናል፤

በእግዚአብሔር ዘንድ እያንዳንዳችን እውቅና አለን ያሉት ቅዱስነታቸው፣ እግዚአብሔር በቁጥር ብቻ ሳይሆን፣ ከልባችን መሻት ጋር እግዚአብሔር በስማችን ያውቀናል በማለት አስረድተዋል። እግዚአብሔር ወደ ራሱ ሊቀበለን በሩን ሁል ጊዜ ክፍት አድርጎ እንደሚጥብቀን እና በእርሱ ዘንድ ድነት እንዳለ እናውቃለን ያሉት ቅዱስነታቸው፣ ጸሎቱን ወደ እግዚአብሔር የሚያቀርብ ሰው በፍጹም እንደማያፍር፣ ከእግዚአብሔር ጋር ከሆኑ ማንኛውንም ዓይነት ችግር ማሸነፍ እንደሚቻል አስረድተዋል።

"ከሁሉ የሚያሳዝነው፣ ያለ ረዳት በችግር ውስጥ ወድቆ መገኘት ነው። ጸሎት ከዚህ ዓይነት ሕይወት ይሰውረናል። የእግዚአብሔር ዕቅድ ምን እንደሆነ ስለማገነዘብ ይህም ሊያጋጥመን ይችላል። ጸሎታችን በከንቱ ወድቀው የሚቀሩ አይደሉም። ርህራሄውን ለእያንዳንዳችን ወደሚገልጽ አባታችን ዘንድ ይደርሳሉና። ኢየሱስም በመከራችን ጊዜ ያዝናል፣ ያለቅሳል"።          

ከእግዚአብሔ ጋር ያለንን ግንኙነት ማሳደግ አስፈላጊ መሆኑን ያስረዱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በእግዚአብሔር ዕርዳታ በመታመን ከመከራ እና ስቃይ መውጣት የሚቻል መሆኑን ገልጸው፣ ዘወትር ሊረዳን ከእኛ ጋር ወዳለው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጸሎታችንን ሳናቋርጥ ማቅረብ እንዳለብን አሳስበውናል።               

14 October 2020, 14:39