ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ ዓለም አቀፍ የትምህርት ስምምነት የተስፋ ፍሬ ያለበት መሆኑን አስታወቁ።

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ጥቅምት 5/2013 ዓ. ም. ባደረጉት የቪዲዮ ኮንፈረንስ፣ ዓለም አቀፍ የትምህርት ስምምነትን በማስመልከት በሮም የላቴራን ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲ ለተካሄደው የውይይት መድረክ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የቫቲካን ዜና፤

ቅዱስነታቸው በመልዕክታቸው እንዳስተወቁት፣ በዓለም ዙሪያ የሚገኙት ማኅበራዊ ተቋማት በዓለም አቀፍ የትምህርት ስምምነት ውስጥ አባል በመሆን ለፍሬያማነቱ ድጋፋቸውን እንዲያደርጉ አሳስበዋል። ዓለም አቀፉ የትምህርት ስምምነቱ በሁሉም የዓለማችን ክፍሎች ተስፋን፣ ሕብረትን እና በሰላም አብሮ የመኖር ባሕሎችን የሚያሳድጉ የቸርነት፣ የሰላም፣ የፍትህ፣ የደግነት፣ የትዕግስት እና የወንድማማችነት እሴቶችን ለማሳደግ ጥረት በማድረግ ላይ መሆኑ ታውቋል።

ትምህርት፣ የተስፋ ፍሬ ነው፤

በቫቲካን የካቶሊክ ትምህርት ስርጭት አስተባባሪ ጽ/ቤት ድጋፍ የተዘጋጀው ዓለም አቀፍ የትምህርት ስምምነት መድረክ፣ ትምህርት በመላው ዓለማችን ወንድማማችነትን፣ ሰላምን እና ፍትህን ለመፍጠር የሚረዱ ድጋፎችን የሚያቀርብ መድረክ መሆኑ ታውቋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ እንዳስታወቁት፣ ዓለም አቀፉ የትምህርት ስምምነት፣ እያንዳንዱ ሰው ሰብዓዊ ክብሩ ተጠብቆለት፣ ጥራት ያለውን ትምህርት በመቅሰም፣ ወንድማማችነትን ለማሳደግ በጋራ መጠራቱን የሚያረጋግጥበት ነው ብለዋል።

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው፣ ዓለም አቀፍ የትምህርት ስምምነት የተስፋ ፍሬ የሆኑትን የሰላም እና የፍትህ፣ የደግነት እና አብሮ በሰላም የመኖር ተስፋን በዘላቂነት የሚያስገኝ መሆኑን አስረድተዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም በሰላም አብሮ የመኖር ባሕልን በማሳደግ፣ ልዩነትን ለሚያስከትሉ ነገሮች ቦታን ሳይሰጡ በአንድነት ወደ ፊት መጓዝ እንደሚያፈልግ አሳስበዋል።

በቪዲዮ ኮንፈረንስ በኩል ከር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ጋር በመገናኘት፣ በዓለም አቀፍ የትምህርት ስምምነት ላይ በተካሄደው ውይይት ላይ መልዕክታቸውን ያካፈሉት፣ በፓሪስ ከተማ የሚገኝ የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባሕል ድርጅት “UNESCO”፣ ኦድሪ አዙሌይ ድርጅት፣ በቫቲካን የካቶሊክ ትምህርት ስርጭት አስተባባሪ ጽ/ቤት እና ጥቂት የሚባሉ የጣሊያን ዩኒቨርሲቲዎች መሆናቸው ታውቋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በዓለም አቀፍ የትምህርት ስርዓት ላይ ያስከተለው ቀውስ መኖሩን ሲያስረዱ፥ በትምህርት አሰጣጥ እና በቴክኖሎጂ አለመመጣጠን ምክንያት አሥር ሚሊዮን የሚሆኑ ሕጻናት ትምህርታቸውን እንዲያቋርጡ መገደዳቸውን ገልጸው፣ አስቀድሞም ቢሆን ለትምህርት የደረሱ፣ ከሁለት መቶ ሃምሳ ሚሊዮን የሚበልጥ ሕጻናት ከትምህርት ገበታቸው ተወግደው መቆየታቸውን ገልጸዋል።

በአንድት ላይ የተመሰረተ ተስፋ፤

በዓለማችን ውስጥ እርስ በእርስ መረዳዳትን፣ ለጋራ መኖሪያ ቤታችን እና ለሰላም የሚጨነቁ ሕዝቦችን እና ማኅበረሰቦችን ለመገንባት ከሁሉ አስቀድሞ ለሰብዓዊ ክብር ቅድሚያን የሚሰጥ አዲስ ባሕል እና አዲስ የዕድገት ሞዴል መዘርጋት እንደሚያስፈልግ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አሳስበዋል። "ትምህርት የሰውን ልጅ የሚለውጥ መሆን አለበት" ያሉት ቅዱስነታቸው፣ ትምህርት የኃያላንን ራስ ወዳድነት ማስቀረት የሚቻልበትን ተስፋ የሚሰጥ መሆን አለበት ብለዋል። ትምህርት አቅመ ደካማነትን እና በምኞት ብቻ መኖርን የሚያስቀር መሆን አለበት ብለውል። “ማስተማር፣ ተስፋን የሚሰጥ ተግባር ነው” ያሉት ቅዱስነታቸው፣ ተስፋ፣ እርስ በእርስ መስተናገድን፣ ከትውልድ እስከ ትውልድ የሚቆይ አንድነትን ለማምጣት እና ለአዲስ ባሕል ፈር ቀዳጅ መሆን ይኖርበታል ብለዋል። ተስፋ በአንድት ላይ የተመሰረተ መሆን እንዳለበት ያስረዱት ቅዱስነታቸው፣ የትምህርት ሂደትም በዘመናችን ላጋጠሙን ተግዳሮቶች በሙሉ መፍትሄን የሚሰጥ፣ የትውልድን ጥያቄ የሚመልስ መሆን አለበት ብለዋል። ይህም የዛሬን እና የመጭውን ትውልድ በማሳደግ ከፍተኛ እገዛን ሊያደርግ ይችላል ብለዋል።

ትምህርት፣ ፀረ-ስግብግብነት እና የማግለል ባሕልን ለማስቀረት፤   

ትምህርት የግለኝነትን ባሕል ለማስቀረት የሚያግዝ ተፈጥሮአዊ መድኃኒት ነው ያሉት ቅዱስነታቸው፣ አንዳንድ ጊዜም ራስን ወደማምለክ እና ወደ ግድየለሽነት ስሜት ይለወጣል ብለዋል። በመሆኑም ከፍተኛ ኢ-ፍትሃዊነት እና የመብት ጥሰት እንዳይፈጸም፣ አሰቃቂ ድህነት እና የሰው ሕይወት በከንቱ የሚጠፋበት ሁኔታ እንዳይከሰት ለማድረግ፣ እያንዳንዱ የማኅበረሰብ ክፍል፣ በሁሉም ደረጃ የበኩሉን ጥረት ማድረግ እንደሚያስፈልግ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አሳስበዋል።

ዓለም አቀፍ የትምህርት ስምምነት፣ የወጣቶችን የብቸኝነት፣ የተስፋ መቁረጥ፣ የሱሰኝነት፣ የቁጡነት፣ የጥላቻ ቃላትን የመናገር እና የወንጀለኝነት ስሜቶችን ለማስወገድ የሚረዱ ዘዴዎችን የሚያሳይ መንገድ ነው። የትምህርት ስምምነቱ በተጨማሪም የተለያዩ አመጾችን፣ በሕጻናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን፣ ያለ ዕድሜ ጋብቻን፣ ሕጻናትን ለውትድርና አገልግሎት መመልመልን እና ለባርነት ሕይወት መዳረግን፣ ጭቆናን እና ወደ ከባድ የአካባቢ እና የአየር ንብረት ቀውስ የሚያደርሱ ብዝበዛዎችን በግልጽ ለማየት ይረዳል።

ለወደፊት ስኬት አብሮ መሥራት፤

አሁን ካጋጠመን የጤና ቀውስ እና ከአደጋው ለመውጣት በጋራ መሥራት እና እያንዳንዱ ማኅበረሰብም በዓለም አቀፍ የትምህርት ስምምነት ውስጥ አባል በመሆን፣ የዛሬውን እና የወደ ፊቱን ትውልድ ለማገዝ ድጋፋቸውን እንዲያደርጉ በማለት ቅዱስነታቸው አሳስበዋል። ይህም የእያንዳንዱን ቤተሰብ፣ ማኅበረሰብ፣ ትምህርት ቤቶች እና ዩኒቨርሲቲዎች፣ ተቋማት እና ሐይማኖታዊ ድርጅቶች፣ የመንግሥታት፣ በእድሜ የደረሱ ወንዶች እና ሴቶች ስልጠናን እና ዝግጁነት ይጠይቃል ብለዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም፣ በመላው ዓለም የሚገኙ የባሕል፣ የሳይንስ፣ የስፖርት፣ የስነ-ጥበብ እና የሚዲያ ጠበብት በጋራ ሆነው፣ የቸርነት፣ የሰላም፣ የፍትህ፣ የደግነት፣ የትዕግስት እና የወንድማማችነት እሴቶችን በማሳደግ፣ ዓለም አቀፉን የትምህርት ስምምነት በመደገፍ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል። ቅዱስነታቸው የቪዲዮ መልዕክታቸውን ሲያጠቃልሉ፥ ስምንት ነጥቦችን በማስታወስ፣ ዓለም አቀፍ የትምህርት ስምምነት፣ እያንዳንዱ ሰው ሰብዓዊ ክብሩ ተጠብቆለት፣ ጥራት ያለውን ትምህርት በመቅሰም፣ ወንድማማችነትን ለማሳደግ በጋራ መጠራቱን የሚያረጋግጥበት መንገድ መሆኑ አስታውቀዋል።

16 October 2020, 18:48