ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ “የክርስቲያን ተልዕኮ ወንጌልን መመስከርና የዜግነት ግዴታን መወጣት ነው"

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ጥቅምት 8/2013 ዓ.ም ፣ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ፣ ዘወትር እሁድ በእለቱ ቅዱስ ወንጌል ላይ ተንተርሰው የሚያደርጉትን የቅዱስ ወንጌልን አስተንትኖ አቅርበዋል። ቅዱስነታቸው በስፍራው ለተገኙ ምዕመናን፥ በወቅቱ ያደርጉት አስተንትኖ በማቴ. 22፥15-21 ላይ በተጠቀሰው፣ “ስለዚህም ፈሪሳውያን ሄዱና እንዴት አድርገው በነገር እንዲያጠምዱት ተማሩ። ጥያቄም አቀረቡለት፤ እንግዲህ ምን ይመስልሃል? ንገረን ለቄሣር ግብር መክፈል ተፈቅዷልን ወይስ አልተፈቀደም? አሉት። ኢየሱስም ክፋታቸውን አውቆ፦ እናንተ ግብዞች፣ ስለምን ትፈትኑኛላችሁ? የግብሩን ብር አሳዩኝ አለ። እነርሱም ዲናር አመጡለት። እርሱም፦ ይህች መልክ ጽሕፈቲቱስ የማን ናት? አላቸው። የቄሣር ነው አሉት። በዚያ ጊዜ፦ እንኪያስ የቄሣርን ለቄሣር የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር አስረክቡ አላቸው።” በሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ መሠረት ያደረገ አስተንትኖ እንደ ነበረ የተገለጸ ሲሆን፥ የቅዱሳን የሕይወት ምስክርነት የሚያስተምረንም እምነትነን በሙላት እንድንኖር ነው። እንዲሁም  በትሕትናና በልበ ሙሉነት በመሠጠትም፥ ፍትሕ የሰፈነበት የወንድማማች ፍቅር በማሕበረሰባችን የበለጠ እንዲኖር የበኩላችንን አስተዋጽዎ ማድረግ ይጠበቅብናል ማለታቸው ተገልጿል።

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዕለቱ ያደረጉትን አስተንትኖ ትርጉም ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል፥

የቫቲካን ዜና፤

          "የተወደዳችሁ ወንድቼ እና እህቶቼ! እንደምን አረፈዳችሁ!

የዛሬው እሑድ ምንባብ በማቴ. 22፥15-21 ላይ ያለው የሚሳየን፥ ጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዘመኑ ከነበሩ ተቃዋሚዎቹ ጋር የነበረውን ትግል ነው። በመሆኑም ፈሪሳውያኖቹ እንዴት አድርገው በነገር እንዲያጠምዱት በመማከርም በማሕበረሰቡ እንዲዋረድ ለማድረግ ጥያቄ ያቀርቡለት ነበር። እንዲህም ብለው ጠየቁት፦ እንግዲህ ምን ይመስልሃል? ንገረን ለቄሣር ግብር መሥጠት ተፈቅዷልን ወይስ አልተፈቀደም? አሉት። ፈሪሳውያኖቹም ለጥየቄያቸው የጠበቁት መልስም አዎ ወይም አይደለም ነበር። ነገር ግን ጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ክፋታቸውን አውቆ ስለነበር፣ እናንተ ግብዞች፥ስለ ምን ትፈትኑኛላችሁ? አላቸው። እንዲሁም የግብሩን ብር አሳዩኝ አለ። እነርሱም ዲናር አመጡለት። እርሱም፦ ይህች መልክ ጽሕፈቲቱስ የማን ናት? አላቸው። የቄሣር ነው አሉት። በዚያን ጊዜ፦ እንኪያስ የቄሣርን ለቄሣር የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር አስረክቡ አላቸው።

ጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመለሰው መልስም ብዙ ክርክሮች ተነሱበት። በአንድ በኩል የቄሣርን ለቄሣር መከፈል አለበት አለ፤ ምክንያቱም በገንዘቡ ላይ የሚታየው ምስል የቄሣር ነበርና። በሌላ በኩል ደግሞ ከምንም በላይ እያንዳንዱ ሰው በውስጡ ሌላ መልክ አለ፤ እርሱም የእግዚአብሔር መልክ ነው፤ ስለሆነም እያንዳንዱ ሰውም ለእግዚአብሔር ብቻ ነው ሕልውናውን መሥጠት ያለበት አላቸው።በዚህ የጌታችን እና የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አስተምህሮ ላይ የምናገኘው፥ ፖለቲካ እና ሐይማኖት ያላቸውን የልዩነታቸው መመሪያ ብቻ ሳይሆን፣ ዛሬም ቢሆን ክርስቶስን የሚከተል አማኝ ሁሉ ሊከተለው ስለሚገባ መርህም ነው የሚያሳየን። ግብርን መክፈል የዜጎች ግዴታ ነው፤ ምክንያቱም ሕግን ማክበር አለባቸውና። በተመሳሳይም ደግም በሰዎች ሕይወትም እንዲሁም በታሪክም የእግዚአብሔርን የበላይነት መታወጅ ይኖርበታል፤ ስለሆነም የሚገባውን ክብርም መሥጠት ያስፈልጋል።

በመሆኑም የክርስቲያኖች እና የቤተክርስቲያን ተልዕኮ፣ ለትውልድ ሁሉ ስለ እግዚአብሔር ማስተማር እና የወንጌል መስካሪዎችም መሆን ነው። ሁሉም ሰው በጥምቀት አማካይነት በማሕበረሰባችን ውስጥ በመንፈስ ቅዱስ ተመርተን ወንጌልን እንድንሰብክ ተጠርተናል። በመሆኑም በትሕትናና በልበ ሙሉነት በመሠጠት፣ ፍትሕ የሰፈነበት የወንድማማች ፍቅር በማሕበረሰባችን የበለጠ እንዲኖር የበኩላችንን አስተዋጽዎ ማድረግ ይጠበቅብናል።

ይህ የክርስቶስ ሐዋርያ የመሆን ተልዕኮም በተለይ ለምዕመኑ፣ ከቤተክርስቲያን አባቶች እና አስተማሪዎች ጋር በሚኖር እውነተኛ ታማኝነት ነው ግቡን የሚመታው። የክርስቶስ መሆን እና በእርሱም መኖር ዓለም ውስጥ ከመኖር የሚያግደን ወይም የሚያስቀረን አይደለም። ስለሆነም በአገልግሎታችን ለሌሎችም በፍቅር መኖር ምክንያት እንድንሆን የሚያደርገን ነው። የቅዱሳን የሕይወት ምስክርነትም የሚያስተምረን፥ እምነትን በሙላት ለመኖር እራስን በመስጠት የእግዚአብሔር መልክ ያለበት የሰውን ልጅ ክብር መጠበቅ ነው።

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ ከግብዝነት ተላቀን ታማኝ፣ ብቁ እና አጋዥ ዜጎች እንድንሆን ትርዳን። እንዲሁም እግዚአብሔር የሕይወታችን ማዕከል እንደሆነም የምንመሠክርበት፣ የክርስቶስ ሐዋርያ የምንሆንበት ተልዕኳችንም እንድበረታ ትርዳን"።

19 October 2020, 15:49