ፈልግ

LIBYA-SECURITY/SIRTE LIBYA-SECURITY/SIRTE 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ በሊቢያ ሰላም እንዲወርድ ጸሎት አቅርበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እሁድ ጥቅምት 8/2013 ዓ. ም. ያቀረቡትን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ከፈጸሙ በኋላ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተገኙት ምዕመናን ጋር የብስራተ ገብርኤል ጸሎት አድርሰዋል። ከጸሎቱ ሥነ -ሥርዓት በኋላ ባሰሙት ንግግር፣ በሊቢያ ውስጥ የሚካሄደውን ደም መፋሰስ ለማስቆም፣ በመንግሥታት መካከል እየተደረገ ያለው ዓለም አቀፍ ውይይት ውጤታማ እና የሰላም በር የሚከፍት መሆን አለበት ብለዋል።

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ በሊቢያ ውስጥ ለዓመታት የዘለቀው እና ለብዙዎች ሕይወት መጥፋት ምክንያት የሆነው ጦርነት እንዲያበቃ በማለት ጸሎታቸውን አቅርበዋል። ቅዱስነታቸው ቀጥለውም በሜዲቴራኒያን ባሕር ዓሣ ሲያጠምዱ በሊቢያ ጠረፍ ጠባቂዎች ተይዘው በቤንጋዚ የሚገኙትን የጣሊያን እና የቱኒሲያ ዓሣ አጥማጆችን አስታውሰዋል። ከብስራተ ገብርኤል ጸሎት በኋላ ባሰሙት ንግግር፣ በሊቢያ ውስጥ ሰላምን እና እርቅን ለማውረድ፣ ከረጅም ጊዜ አንስቶ በተለያዩ ጊዜያት ሲደርጉ የቆዩት የእርቅ እና የሰላም ውይይቶች መልካም ውጤትን እንዲያስገኙ፣ ማንኛውንም ዓይነት አመጽ ማስወገድ እንዲቻል በተቃራኒ ቡድኖች መካከል የሚደረግ ውይይት ተጠናክሮ እንዲቀጥል አደራ ብለዋል።    

የወንጌል ተልዕኮ ቀን

ዕለቱ ዓለም አቀፍ የወንጌል ተልዕኮ ቀን የሚታወስበት መሆኑን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ የወንጌል ተልዕኮ በምዕመና እና ሕይወታቸውን በሙሉ ለዚህ አገልግሎት በሰጡት ሰዎች የሚፈጸም ክቡር አገልግሎት መሆኑን አስረድተዋል። እያንዳንዱ ክርስቲያን ወዳጅነትን እና ወንድማማችነትን ለማሳደግ የተጠራ መሆኑን የገለጹት ቅዱስነታቸው፣ በተለይም ባሁኑ ጊዜ በወንጌል ተልዕኮ ላይ ተሰማርተው የሚገኙትን፣ ካህናትን እና ምዕመናንን በጸሎት በማገዝ፣ ተጨባጭ እርዳታን ማድረግ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

19 October 2020, 16:06