ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ “ሁላችንም ወንድማማቾች ነን” በሚል ርዕስ አዲስ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ይፋ አደረጉ።

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ቅዳሜ መስከረም 23/2013 ዓ. ም ከሰዓት በኋላ በጣሊያን ውስጥ አሲዚ ወደተባለች አነስተኛ ከተማ በመጓዝ የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ማድረሳቸው ታውቋል። የቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ ጉዞ ዓላማ በመስከረም 24 ቀን ለሚከበረው የቅዱስ ፍራንችስኮስ ዓመታዊ ክብረ በዓል በተዘጋጀው የዋዜማ ዕለት ጸሎት ለማቅረብ ሲሆን በዚሁ ዕለትም “ሁላችንም ወንድማማቾች ነን” የተሰኘውን አዲስ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸውን በፊርማቸው በማጽደቅ ይፋ ማድረጋቸው ታውቋል። ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸውን በተለያዩ ቋንቋዎች በመተርጎም የተባበሩትን የቅድስት መንበር ጽ/ቤት ሠራተኞችን አመግነዋል። ወደ አሲዚ በተጓዙበት ወቅት ወደ ቅድስት ኪያራ ማኅበር ገዳም በመሄድ በዛው የሚገኙ መነኩሳትንም ጎብኝተዋል።

የቫቲካን ዜና፤

ቅዱስነታቸው የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ያቀረቡበት የመላዕክት ንግሥት ቅድስት ማርያም ባዚሊካ የቅዱስ ፍራንችስኮስ መካነ መቃብር የሚገኝበት እና በየዓመቱ ከአራቱ ማዕዘናት በብዙ ሺህዎች የሚቆጠሩ ምዕመናን ለጸሎት የሚመጡበት ቅዱስ ሥፍራ መሆኑ ታውቋል። “ሁላችንም ወንድማማቾች ነን” የተሰኘውን የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ አዲስ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን በሕዝቦች መካከል ወንድማማችነትን እና ማኅበራዊ ወዳጅነትን በማሳደግ፣ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እጅግ ለተጎዳው የዓለማችን ሕዝብ በሙሉ ተስፋን የሚሰጥ መሆኑ ሲነገር፣ ቃለ ምዕዳኑ “ሁላችንም ወንድማማቾች ነን” የሚለውን ርዕስ ያገኘው ከቅዱስ ፍራንችስኮስ ንግግሮች መሆኑ ታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወደ አሲዚ ያደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ጥቂት ምዕመናን የተሳተፉበት፣ በጥልቅ ጸሎት እና አስተንትኖ የተካሄደ መሆኑ ታውቋል። ቅዱስነታቸው በዕለቱ ያቀረቡት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሥነ-ሥርዓት በመስከረም 20 ቀን የሚከበረውን የቅዱስ ፍራንችስኮስ ክብረ በዓል የሚያስታውስ ነው ተብሏል። ቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸውን በፊርማ በማጽደቅ ይፋ ከማድረጋቸው በፊት በትርጉም ሥራ የተባበሩት የቅድስት መንበር ጽ/ቤት ሠራተኞችን አመግነዋል። ፊርማቸውን በማኖር አዲሱን ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸውን ይፋ ያደረጉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ የሐርያዊ ቃለ ምዕዳን የትርጉም ሥራን በበላይነት የመሩትን ብጹዕ አቡነ ፓውሎ ብራይዳን፣ በትርጉም ሥራ፣ ከስፓኒሽ ቋንቋ ወደ ፖርቹጊስ ቋንቋ የተረጎሙትን ክቡር አባ አንቶኒዮስን እና ወደ ሌሎች ቋንቋዎች የተደረጉ ትርጉሞችን የተከታተሉትን ክቡር አባ ክሩዝን እና የቅድስት መንበር ጽ/ቤትን አመስግነዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወደ አሲዚ ከመድረሳቸው በፊት የቅድስት ኪያራ ማኅበር ገዳምን ጎብኝተው በገዳሙ ውስጥ ከሚኖሩ መነኩሳት ጋር ሰላምታ ተለዋውጠዋል። ቅዱስነታቸው በአሲዚ ከተማ ወደሚገኝ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የመላዕክት ንግሥት ባዚሊካ ሲደርሱ በገዳሙ አለቃ በሆኑት በክቡር አባ ማውሮ ጋምቤቲ የክብር አቀባበል የተደረገላቸው ሲሆን የገዳሙ ወንድሞችም ከቅዱስነታቸው ጋር በመስዋዕተ ቅዳሴው ጸሎት ሥነ-ሥርዓት ላይ መካፈላቸው ታውቋል። በመስዋዕተ ቅዳሴው ሥነ-ሥርዓት ላይ አንዳንድ ገዳማዊያን እና ገዳማዊያት እንዲሁም የሀገረ ስብከቱ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ዶሜኒኮ ሶሬንቲኖ፣ እና በአሲዚ ከተማ የሚገኝ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የመላዕክት ንግሥት ጳጳሳዊ ባዚሊካ ተጠሪ ብጹዕ ካርዲናል አጎስቲኖ ቫሊኒ ተግኝተዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወደ አሲዚ ከተማ ያደረጉት ይህ ሐዋርያዊ ጉብኝት አራተኛው መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።  

04 October 2020, 14:36