ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንቸስኮስ፥ “ወንጌል የሚሰበከው ለሁሉ ሰው እንጂ ለተወሰኑት ብቻ አይደለም”

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በጥቅምት 1/2013 ዓ. ም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ፣ ዘወትር እሁድ በእለቱ ቅዱስ ወንጌል ላይ ተንተርሰው የሚያደርጉትን የቅዱስ ወንጌልን አስተንትኖ ለመከታተል በስፍራው ለተገኙ ምዕመናን፥ በወቅቱ ያደርጉት አስተንትኖ (በማቴ. 22፥1-14) ላይ በተጠቀሰው “መንግሥተ ሰማያት ለልጁ ሠርግ ያደረገ ንጉሥን ትመስላለች። የታደሙትንም ወደ ሠርጉ ይጠሩ ዘንድ አገልጋዮቹን ላከ ሊመጡም አልወደዱም። ደግሞም ሌሎቹን አገልጋዮቹን ልኮ፦ የታደሙትን፦ እነሆ ድግሴን አዘጋጀሁ፥ኮርማዎቼና የሰቡት ከብቶቼ ታርደዋል፤ ሁሉም ተዘጋጅቷል፤ ወደ ሠርጉ ኑ በሏቸው አለ።” በሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ መሠረት ያደረገ አስተንትኖ እንደ ነበረ የተገለጸ ሲሆን፥ ለልጁ ሠርግም ግብዣ ያዘጋጀው ንጉሥ ምሳሌነቱ የሚያመለክተው፥ እግዚአብሔር ለሰው ሁሉ ያዘገጀው፥ በልጁ ፊት በፍቅር እና በአንድነት ሊኖረን ስለሚገባ ደስታ ነው የሚያወሳው። እንዲሁም ቤተክርስቲያንም ወደ ጎዳናው በመውጣት፥ በችግር እና በተስፋ መቁረጥ እንዲሁም በተለያየ የሕይወት ውጣ ውረድ ውስጥ ላሉት ትደርስ ዘንድ ተጠርታለች ማለታቸውን ተገልጿል።

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዕለቱ ያደረጉትን አስተንትኖ ትርጉም ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል።

የቫቲካን ዜና፤

"የተወደዳችሁ ወንድቼ እና እህቶቼ! እንደምን አረፈዳችሁ!

በዛሬው የወንጌል ንባብ በማቴ. 22፥1-14 ባለው በሠርጉ ግብዣ ላይ የተጠሩ ሰዎች ምሳሌ፥ ጌታችን እና ማድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ያየውን ዓላማ በሚገባ ያሳየበት ነው። ለልጁ ሰርግም ግብዣ ያሰናዳው ንጉስ ምሳሌነቱ የሚያመለክተው፥ እግዚአብሔር ለሰው ሁሉ ያዘገጀው፥ በልጁ ፊት በፍቅር እና በአንድነት ሊኖረን ስለሚገባ ደስታ ነው የሚያወሳው። ንጉሡ የተጋበዙትን ሰዎች እንዲጠሩ ሁለት ጊዜ አገልጋዮቹን ላከ፤ ነገር ግን ታዳሚዎቹ ሊመጡ አልወደዱም፤ አንዱ ወደ እርሻው፥ ሌላው ወደ ንግዱ ሄደ። ይህም የሚመለክተው ብዙ ጊዜ እኛም የእግዚአብሔርን ጥሪ ትተን የራሳችንን ፍላጎት ማሟላት ላይ እንዘምታለን፤ በቁስ ነገሮችም ለመከበብ ጥረት እናደርጋለን። ይሁን እንጂ በምሳሌው ላይ ያለው ንጉሥ፥ አዳራሹ ባዶ እንዲሆንበት አይፈልግም፤ ምክንያቱም ከመንግሥቱ የሚገኘውን ሐብት መስጠት ይፈልጋልና። ስለዚህም ለአገልጋዮቹ እንዲህ አላቸው፦ ወደ መንገድ መተላለፊያ ወጥታችሁ ያገኛችሁትን ሁሉ ወደ ሠርጉ ግብዣ ጥሩልኝ አላቸው። ይህ እግዚአብሔር የሚጽናናበት መንገድ ነው፤ ጠርቶን ስንቀርበትም እርሱ ተስፋ አይቆርጥም፤ በመሆኑም ማንም ሳይቀር፥ በመንገድ መተላለፊያ ያሉትንም ሁሉ በድጋሚ በመጠየቅ ይጠራል።

በዚህ የወንጌል ክፍል ሰባኪው ቅዱስ ማቴዎስ የተጠቀመው የመጀመሪያው ስያሜ ወይም አገላለጽ፥ አንዳንድ መንገዶች የተገደቡ ስለመሆናቸው እና እርግጠኛ የማይኮንባቸው የሕይወት አቅጣጫዎች እንዳሉ ያሳየበት ነው። በምሳሌውም ላይ የተጠቀሰው ንጉሥም በእርግጠኝነት በግብዣው ማዕድ ላይ ለመቀመጥ ፈቃደኛ ይሆናሉ ብሎ በማመን፥ ያገኙትን ሁሉ እንዲጠሩ አገልጋዮቹን ወደ ጎዳናው ላካቸው። በመሆኑም የግብዛው አዳራሽም በሰው ተሞላ፤ እነዚህም በማኅበረሰቡ የተጠሉ እንዲሁም በእንደዚህ አይነት የሰርግ ግብዣ ላይ ይገባቸዋል ተብለው የማይታሰቡ እና የማይካተቱ ናቸው። ቤተክርስቲያንም ወደ ጎዳናው በመውጣት በችግር እና በተስፋ መቁረጥ እንዲሁም በተለያየ የሕይወት ውጣ ውረድ ውስጥ ላሉት ትደርስ ዘንድ ተጠርታለች። በመሆኑም ወንጌልን ለተወሰኑ እና ለተመረጡ ሰዎች ብቻ የሚሰበክ ሳይሆን ልባችንን በመክፈት ለሁሉም ማድረስ ያለብን ሥራችን ነው። ምክንየቱም እነዚያ በማህበረሰቡ የተገለሉ እና የተጠሉትም በእግዚአብሔር የተወደዱ እና ፍቅሩ የተገባቸው ናቸውና። ግብዣው ለሁሉም ነው፤ ለጻድቃኑም እንዲሁም ለኃጢአተኛውም፥ ለመልካሙም ደግሞም መልካም ላልሆነውም፥ እንዲሁም ለዓዋቂውም ደግሞም ላላዋቂውም የተዘጋጀ ነው። አገልጋዮቹም ወደ መንገድ ወጥተው ያገኙትን መልካሙንም ክፉውንም ሁሉ ሰብሰስበው የሰርጉን አዳራሽ በእንግዶች ሞሉት። ይሁን እንጂ ንጉሡ አንድ ቅድመ ሁኔታ ነበረው፥ እርሱም ከበር ላይ ይሰጥ የነበረው የመግቢያ ስጦታ ነው።ንጉሡም የተጋበዙትን እንግዶች ለማየት ሲገባ፥ አንድ የሰርግ ልብስ ያለበሰ ሰው አየ፤ እንዲህም አለው፤ የሰርግ ልብስህ ሳትለብስ እንዴት እዚህ ልትገባ ቻልህ? በማለት ጠየቀው፤ ሰውየው ግን የሚመልሰው ቃል አልነበረውም። ንጉሡም አገልጋዮቹን እጅ እና እግሩን አስራችሁ በውጭ ወዳለው ጨለማ አውጥታችሁ ጣሉት፤በዚያ ለቅሶ እና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል አላቸው። ይህ ሰው የመግቢያውን ቅድመ ሁኔታ አላሟላም፤ እራሱን በእራሱ ግብዣው ላይ እንዳይታደም አደረገ፤ የመግቢያ ስጦታውንም ናቀ፤በራሱ የበቃ መሰለው፤ ንጉሡም ምንም ሊያደርግለት አልቻለም፤ በመሆኑም አውጥቶ መጣል ነበረበት። ይህ የመግቢያውን ሥጦታ እና የግብዣውን ልብስ ችላ ያለው ሰው፥ ግብዣውን ተቀብሏል፤ ነገር ግን ከምንም አልቆጠረውም፤ ለመለወጥም ፍላጎት የታየበት አልነበረም። የሰርግ ልብሱ የሚያመለክተው፥ እግዚአብሔር በነጻ ስለሚሰጠን ምሕረት እና ይቅርታ ነው። እግዚአብሔርን ለመከተል፥ግበዣውን ብቻ መቀበል በቂ አይደለም፤ነገር ግን ለለውጥ ጉዞ ዝግጁ መሆን ያስፈልጋል፥እሱም ከልብ የሆነ መለወጥ ነው። የምሕረት ልብሱም እግዚአብሔር ያለማቋረጥ በነፃ የሚሰጠን የፍቅር ሥጦታ ነው፤ ይህም ፀጋው ነው።

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም ካለንበት የጠበበ አመለካከት ወጥተን፥እግዚአብሔር በፀጋው እንድንድን ወደ ግብዣው ማዕድ እንደሚጠራን ለሁሉም በመስበክ፥ በወንጌሉ ምሳሌ የተጠቀሱትን አገልጋዮችን እንድንመስል ትርዳን”።

12 October 2020, 12:19