ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ “ከማኅበራዊ እና ኤኮኖሚያዊ ውድቀት ለመነሳት ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል”

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ማክሰኞ መስከረም 20/2013 ዓ. ም. ባቀረቡት ሳምንታዊ የረቡዕ ዕለት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ፣ እንደ ኮሮና ቫይረስ የዓለም ሕዝብን እየጎዳ ለሚገኝ ማኅበራዊ እና ኤኮኖሚያዊ ቀውስ መፍትሄ ማግኘት፣ ሁሉን አቀፍ ዘላቂ ማኅብረሰብን መፍጠር እና እርስ በእርስ በመተሳሰብ ወደ ፊት መጓዝ ያስፈልጋል ብለዋል። ዛሬ ዕለቱ፣ የቤተክርስቲያን ሊቅ የሆነው፣ የቅዱስ ጀሮም መታሰቢያ ዕለት መሆኑንም ቅዱስነታቸው አስታውሰዋል።

የቫቲካን ዜና፤

በቫቲካን ውስጥ በሚገኘው በቅዱስ ዳማሶ ቅጥር ግቢ ውስጥ ያቀረቡት ሳምንታዊ አስተምህሮ፣ ባሁኑ ጊዜ ዓለማችንን እጅግ እያስጨነቀ በሚገኝ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ፣ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸውን ሕዝቦች ለማጽናናት በማሰብ “ዓለምን መፈወስ” በሚል ዐብይ አርዕስት የጀመሩት አስተምህሮ የመጨረሻ ክፍል መሆኑ ታውቋል። ዛሬ ባቀረቡት ዘጠነኛ የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ፣ እየተስፋፋ ካለው ማኅበራዊ እና ኤኮኖሚያዊ ውድቀት ለመነሳት ጥረት ሊደረግ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

ዓለማችን ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ አስቀድሞ ጉዳት የደረሰበት መሆኑን የገለጹት ቅዱስነታቸው፣ ወደዚያ ዘመን መመለስ የለብንም ብለው ቫይረሱ ዓለማችን የሚገኝበትን ክፉ ጊዜን በግልጽ እንድንመለከት አድርጎናል ብለዋል። በዓይን የማይታይ ረቂቅ ቫይረስ ወረርሽኝ በመካከላችን በመግባት ጥልቅ ቁስልን በመፍጠር አካላዊ፣ ማኅበራዊ እና መንፈሳዊ ተጋላጭነታችንን ሰውሮብናል ብለዋል። በዓለማችን የተዛመተው ኮሮና ቫይረስ ለረጅም ዘመናት ስር ሰድዶ የቆየው የኤኮኖሚ እድገት፣ የጤና፣ የትምህርት ዕድሎችን እና የቴክኖሎጂ እድገት አለመመጣጠን ጎልቶ እንዲታይ ማድረጉን አስረድተዋል። ባሁኑ ጊዜ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሕጻናት ትምህርት ቤት የመሄድ ዕድል የሌላቸው መሆኑን ገልጸዋል። ሌሎች በርካታ ኢፍትሃዊ ተግባራት ከሰው ልጅ ልብ ውስጥ የመነጩ ናቸው ብለው ይህም የብዙዎችን ተስፋ በማጨለም፣ በስጋት እና በስቃይ ውስጥ እንዲኖሩ አድርጓቸዋል ብለዋል።                  

ኮሮና ቫይረስን ብቻ መዋጋት የለብንም፤

ምንም እንኳን አስፈላጊ ቢሆንም ጥረታችን ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ለመውጣት ብቻ ሳይሆን ከበርካታ ማኅበራዊ እና ኤኮኖሚያዊ ችግሮች ለመውጣት መሆን አለበት ብለዋል። ማኅበራዊ ችግሮቻችንን መደበቅ የለብንም ያሉት ቅዱስነታቸው፣ አሁን የምንጠቀምባቸው የኤኮኖሚ እድገት ሞዴሎች በማሻሻል ችግሮቻችንን ለማስወገድ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

ማኅበረሰባችን አብሮነትን ያማከለ እና አሳታፊ ይሁን፤

ማኅበራዊ እና ኤኮኖሚያዊ ችግሮችን መቋቋም አለብን በምንልበት ጊዜ በሰዎች መካከል ላለው ልዩነት በማክበር እና እውቅናን በመስጠት፣ እያንዳንዱ የማኅበረሰብ አባል ወደ ጎን ሳይባል፣ በተለይ ከአቅመ ደካሞች ጋር ያለውን አድነት ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ቅዱስነታቸው አሳስበዋል። መልካም የፖለቲካ ስርዓትን ለማዋቀር ትጋት እና ቁርጠኝነት ያስፈልጋል ብለው፣ ልዩነትን፣ ብዝበዛን እና የግል ጥቅም ከመፈለግ ይልቅ ለማኅበራዊ ጥቅም የቆሙ ሕዝባዊ ድርጅቶችን ለማዋቀር የሚያግዙ ስርዓቶችን መዘርጋት ያስፈልጋል ብለዋል። አብሮ የመኖር ጥቅምን የተረዳ ማኅበረሰብ ጤናማ ማኅበረሰብ እንደሆነ የገለጹት ቅዱስነታቸው በተለይ አቅመ ደካሞችን በሚያሳትፍ ማኅበረሰብ መካከል ያለው አንድነት እጅግ ጠንካራ ነው ብለዋል።

ኢየሱስን መከተል፤

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ባለፉት ሳምንታት ባቀረቡት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸው ስለ ሰብዓዊ ክብር፣ ስለ አንድነት እና እና ስለ መተጋገዝ ሰፊ ትምህርት ካስተላለፉ በኋላ በዛሬው የመጨረሻ ክፍል አስተምህሮአቸው፣ ሰብዓዊ ክብርን ለማሳደግ የጋራ ጥቅምን ማሳደግ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። እንደ ደቀ መዛሙርት የኢየሱስን ፈለግ ለመከተል ተጠርተናል ያሉት ቅዱስነታቸው፣ ለድሆች በመጨነቅ፣ የጋራ ጥቅምን ለማሳደግ እና የጋራ መኖሪያ ምድራችንን ከውድመት ለመጠበቅ፣ የቤተክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምሮን በመከተል በእምነት፣ በተስፋ እና በቸርነት ለመኖር ተጠርተናል ብለዋል። ይህም ምኞትን እውን ለማድረግ እንደሚጥሩ ጠንካራ ሰራተኞች እንድንሆን፣ ከሚለያዩን እና ከሚያቆስሉን ተግባራት ይልቅ በጋራ ለመኖር ምቹ የሆነች አዲስ ዓለምን ለመገንባት ያግዘናል ብለዋል።

30 September 2020, 20:51