ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንቸስኮስ፥ "ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በመስከረም 3/2013 ዓ. ም. በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ፣ ዘወትር እሁድ በእለቱ ቅዱስ ወንጌል ላይ ተንተርሰው የሚያደርጉትን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ በስፍራው ለተገኙ ምዕመናን አቅርበዋል። የቅዱስነታቸው አስተንትኖ በማቴ. 18፡21-35 ላይ በተጠቀሰው “ጴጥሮስም፦ ጌታ ሆይ! ወንድሜ ቢበድለኝ ስንት ጊዜ ይቅር ልበለው? እስከ ሰባት ጊዜ ነውን? አለው (ቁ. 21)፤ ኢየሱስም፦ እስከ ሰባ ጊዜ ሰባት እንጂ እስከ ሰባት ጊዜ ብቻ አልልህም” (ቁ. 22) በሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ መሠረት ያደረገ ሲሆን “ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች፥ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በእለቱ ያደረጉትን አስተንትኖ ትርጉም ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተለው አሰናድተነዋል፥

የቫቲካን ዜና፤

የተወደዳችሁ ወንድቼ እና እህቶቼ! እንደምን አረፈዳችሁ!

የዛሬው የወንጌል አስተምህሮ በማቴ. 18፤21-35 ላይ ያጠነጠነ ይሆናል። በዚህ በዛሬው ወንጌል ስለ ምህረት አድራጊው ንጉሥ የወንጌል ምሳሌ ሁለት ጊዜ የሚከተለውን ተማጽኖ እናያለን። ይኸውም በቁ. 26 እና 29 ላይ "በዚህ ጊዜ አገልጋዩ እግሩ ላይ ወድቆ፣ ታገሰኝ ያለብኝን ዕዳ ሁሉ እከፍልሃለሁ ሲል ለመነው" የሚለው ነው። ይህ ተማጥኖ ለመጀመሪያ ጊዜ አሥር ሺህ መክሊት ወይም ብዙ ገንዘብ ለጌታው መስጠት ከነበረበት አገልጋይ በግልጽ የቀረበ ሲሆን ለሁለተኛ ጊዜ ደግሞ በቁ. 29 ላይ፣ በሌላኛው አገልጋይ የቀረበ ነው። ይህ ሁለተኛው አገልጋይ ዕዳው እንዲተውለት ተማጥኖ የጠየቀው ደግሞ ባለዕዳ ለነበረው እና ነገር ግን እዳው ለተተወለት አገልጋይ ነው፤ ሁለቱም የአንድ ጌታ አገልጋዮችም የሆኑ ናቸው። ይሁን እንጂ ሁለተኛው አገልጋይ ከመጀመሪያው ጋር ሲነጻጸር እዳው በጣም ያነሰ ነበር።

የዚህ ምሳሌ ዋናው መልዕክት፥ ጌታው ብዙ እዳ ለነበረበት አገልጋይ ያሳየው ርህራሄ እና አዘኔታ ነው።ወንጌላዊውም በቁ. 27 "ጌታውም አዘነለት እና ማረው፤ ዕዳውንም ትቶለት አሰናበተው" የሚለው ላይ ትኩረት አድርጓል። ብዙ እዳ የነበረበት፥ ነገር ግን የተሰረየለት አገልጋይ፥ ወዳጁ ለሆነው ለሌላኛው አገልጋይ ግን ምህረትን ማሳየት ተሳነው፤ ትንሹ እዳውንም ሊተውለት አልቻለም። ይህም በቁ.28. ላይ "ያ አገልጋይ ከጌታው ፊት እንደወጣ አንድ መቶ ዲናር የእርሱ እዳ ያለበትን አገልጋይ ባልንጀራውን አግኝቶ እንቅ አድርጎ በመያዝ፥ ያለብህን እዳ ክፈለኝ! አለው"። ስለሆነም በቁ. 30 ላይ "ነገር ግን ሊታገሰው ፈቃደኛ ስላልነበረ፣ ያለበትን እዳ አስኪከፍለው ድረስ ወህኒ ቤት አስገባው።" ጌታውም ይህንን በሰማ ጊዜ ጨካኙን አገልጋይ አስጠርቶ አወገዘው። (ቁ. 32-34)

በዚህ የወንጌል ክፍል በተጠቀሰው ምሳሌ፥ ሁለት አመለካከቶችን እናያለን፤ ይኸውም በንጉሡ ወይም በጌታው የተመሰለው እግዚአብሔር እና የሰው ልጅን ነው። በመጀመሪያው በመለኮታዊው አመለካከት ምህረት በመደረጉ ፍትህ ወርዷል ወይም ፍትህ ሰፍኗል፤ በሰዎች በኩል ደግሞ ፍትህ የተገደበ ስለመሆኑ ያሳያል። ጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በመጀገን ለይቅርታ ልባችንን እንድንከፍት ይገፋፋናል፤ ምክንያቱም በሕይወት ሁሉም ነገር በፍትህ ሊፈታ አይችልምና። በመሆኑም ምህረት አድራጊ ፍቅር ያስፈልጋል። ይህም ጌታ ክርስቶስ ለጴጥሮስ ለሰጠው መልስ መሠረት ነው። ጴጥሮስም፦ጌታ ሆይ! ወንድሜ ቢበድለኝ ስንት ጊዜ ይቅር ልበለው? አስከ ሰባት ጊዜ ነውን? አለው (ቁ. 21)፤ ኢየሱስም፦እስከ ሰባ ጊዜ ሰባት እንጂ እስከ ሰባት ጊዜ ብቻ አልልህም አለው (ቁ. 22)። በመጽሐፍ ቅዱስ ስዕላዊ አገላለጽም፥ ሁላችንንም ይቅር እንድንል የተጠራን መሆኑን ያሳያል፡፡

ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም፦ በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል፤ እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው፡፡

የዛሬው የወንጌል ምሳሌ በማቴ. 6፤12 እኛም ደግሞ የበደሉንን ይቅር እንደምንል፣ “በደላችንን ይቅር በለን” የሚለውን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተማረንን ጸሎት በሙላት እንድንረዳ የሚረዳን ነው። እነዚህ ቃላቶች ቁልፍ የሆነ እውነትን የያዙ ናቸው። ወንድሞቻችን እና እህቶቻችንን ይቅር የማንል ከሆነ፥እኛም ምህረትን ከእግዚአብሔር እንደማናገኝ የሚያስረዳ እውነት አለው። ሌሎች ወንድሞቻችን እና እህቶቻችንን ይቅር የማንል እና የማናፈቅር ከሆነም፥ እኛም ፍቅርን እና ምህረትን ማግኘት አንችልም።

የአምላክ እናት ድንግል ማርያም፣ በእናታዊ አማላጅነትዋ፣ እግዚአብሔር የምህረት አምላክ እንደሆነ በሚገባ እንድናውቅ እና እንዲሁም ልባችንን ለይቅርታ እና ለመልካምነት እንድንከፍት ትርዳን!

14 September 2020, 10:41