ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፥ “እግዚአብሔር የማያቋርጥ ጥሪውን ለእያንዳንዳችን ያቀርብልናል”

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዘወትር እሁድ በዕለቱ ቅዱስ ወንጌል ላይ ተንተርሰው የሚያደርጉትን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ በመስከረም 10/2013 ዓ. ም፣ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተገኙት ምዕመናን አቅርበዋል። የቅዱስነታቸው አስተንትኖ በማቴ. 20፡1-16 ላይ በተጠቀሰው፣ “መንግሥተ ሰማያት ለወይኑ አትክልት ሠራተኞችን ሊቀጥር ማልዶ የወጣ ባለቤት ሰውን ትመስላለችና” በሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ መሠረት ያደረገ እንደ ነበረ የተገለጸ ሲሆን፥ እግዚአብሔር በራሱ ዓለም ብቻ ታጥሮ የሚኖር ሳይሆን፥ ባለማቋረጥ በመውጣት ሰዎችን ለመንግሥቱ ሥራ የሚፈልግ ነው፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር ሁሉንም አካታች በሆነው ፍቅሩ፥ ማንም እንዲጎድልበት አይፈልግም። እንዲሁም "እግዚአብሔር በሥራው ከፍትሃዊነት ባሻገር ነው፤ ምክንያቱም በጸጋው የሚደግፍ አምላከ ነውና" በማለት ገልጸዋል።

ክቡራት እና ክቡራን፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በእለቱ ያደረጉትን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ትርጉም ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተለው አቅርበነዋል፥

የቫቲካን ዜና፤

የተወደዳችሁ ወንድቼ እና እህቶቼ! እንደምን አረፈዳችሁ!

የዛሬው የወንጌል አስተንትኖ፥ በማቴ. 20፤ 1-16 ላይ ያተኮረ ይሆናል። የዛሬው የወንጌል አስተምህሮ፥ሠራተኞችን ሊቀጥር ማልዶ ስለወጣ የወይን አትክልት ስፍራ ባለቤት ምሳሌ ይናገራል። በዚህም ምሳሌ፥ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ እግዚአብሔር የሚሠራባቸውን አስደናቂ መንገዶችን ያሳያል። በሁለቱ የአትክልቱ ባለቤት አመለካከቶችም ይመሰላል፤ ይኸውም፦ መጥራትን እና ክፍያን ወይም ደመወዝን ስለ መስጠት ያጠነጠነ ነው።

ከሁለቱ የወይን አትክልት ቦታው ባለቤት ባህሪያት፥ የመጀመሪያው ወጥቶ ሠራተኞችን ስለ መጥራቱ  ነው።ይህም ባለቤት፥ አምስት ጊዜ ሰዎች ሥራ ይሠሩ ዘንድ በ12፥3፣6፣9 እና 11 ሰዓት ወጥቶ ጠርቷል፤ ይሠሩለት ዘንድም በተደጋጋሚ የቀን ሠራተኞችን ፍለጋ መውጣቱ ልብን ይነካል። በዚህ ምሳሌ የወይን አትክልት ሥፍራ ባለቤት፥ በእግዚአብሔር ይመሰላል፤ እርሱም ሁሉንም፥ ሁል ጊዜ የሚጠራ መሆኑን ያሳያል። ዛሬም እግዚአብሔር በዚሁ መንገድ ነው የሚሠራው፤ ማለትም ማንኛውንም ሰው፥ በፈለገው ጊዜ በመጥራት ለመንግሥቱ ሥራ ይጋብዛል። ይህ የእግዚአብሔር አሠራር ነው፤ እኛም ይህንን ተቀብለን ለምኖር እንድንተጋ ተጠርተናል። እግዚአብሔር በራሱ ዓለም ብቻ ታጥሮ የሚኖር ሳይሆን፥ ባለማቋረጥ በመውጣት ሰዎችን ለመንግሥቱ ሥራ የሚፈልግ ነው፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር ሁሉንም አካታች በሆነው ፍቅሩ፥ ማንም እንዲጎድልበት አይፈልግምና፡፡

ሕብረታችንም ለዚሁ ዓላማ የተጠራ ነው፤ ያለ ምንም ገደብ በመውጣት፥ ክርስቶስ ያመጣውን የመዳን ወንጌል ማሰራጨት እና እስከ ዓለም ዳርቻ ማድረስ ይጠበቅብናል። ይህም ማለት የሕይወታችንን አድማስ በማስፋት ክርስቶስን ወዳጅ በማድረግ የሚገኘውን ብርሃን እና ብርታት ላላገኙት በመድረስ፥ ተስፋ እና አጋዥ መሆን ይኖርብናል፡፡

ሁለተኛው በእግዚአብሔር የተመሰለው የወይን አትክልት ስፍራ ባለቤት አመለካከት፥ የቀን ሠራተኞቹን ደሞዝ ስለመክፈል ነው የሚያወሳው። እርሱም በጠዋቱ ለቀጠራቸው ሠራተኞቹ፥ በወንጌሉ እንደተጠቀሰው “ሠራተኞቹንም በቀን አንድ ዲናር ተስማምቶ ወደ ወይኑ አትክልት ወሰዳቸው" (ቁ. 2). በሌላ በኩል ደግሞ፥ረፋዱ ላይ ለቀጠራቸው፦ “እናንተ ደግሞ ወደ ወይኔ አትክልት ሂዱ፤ የሚገባውንም እሰጣችኋለሁ አላቸው፤እነርሱም ሄዱ” (ቁ. 4)። በስተ መጨረሻም የወይኑ አትክልት ባለቤት ሁሉም ተመሳሳይ ወይም እኩል ደመዎዝ፥ አንድ ዲናር እንዲከፈላቸው አዘዘ። ከጠዋት ጀምረው የሠሩት ግን ቀጣሪያቸው በሆነው በአትክልቱ ስፍራ በባለቤት ላይ አጉረመረሙ። በወንጌሉ እንደተጠቀሰውም "በመሸም ጊዜ የወይኑ አትክልት ጌታ አዛዡን፦ ሠራተኞቹን ጥራና ከኋለኞች ጀምረህ እስከ ፊተኞች ድረስ ደመወዝ ስጣቸው አለው። በአስራ አንደኛው ሰዓትም የገቡ መጥተው እያንዳንዳቸው አንድ ዲናር ተቀበሉ። ፊተኞችም በመጡ ጊዜ አብዝተው የሚቀበሉ መስሏቸው ነበር፤ እነርሱም ደግሞ እያንዳንዳቸው አንድ ዲናር ተቀበሉ። ተቀብለውም፦ “እነዚህ ኋለኞች አንድ ሰዓት ሠሩ፥ የቀኑንም ድካምና ትኩሳት ከተሸከምን ከእኛ ጋር አስተካከልሃቸው” ብለው በባለቤቱ ላይ አጉረመረሙ። እርሱ ግን መልሶ ከእነርሱ ለአንዱ እንዲህ አለው፦ “ወዳጄ ሆይ፥አልበደልሁህም፤ በአንድ ዲናር አልተስማማኸኝምን? ድርሻህን ውሰድና ሂድ፤ እኔ ለዚህ ለኋለኛው እንደ አንተ ልሰጠው እወዳለሁ፤ በገንዘቤ የወደድሁትን አደርግ ዘንድ መብት የለኝምን? ወይስ እኔ መልካም ስለ ሆንሁ ዓይንህ ምቀኛ ናትን? (ከቁ. 8-15)" በማለት መለሰለት። ይህም ማለት በዋናነት ልንረዳው የሚያስፈልገው፥ ጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ሥራ እና ስለ ደመወዝ አይደለም የሚናገረው፤ ነገር ግን ስለ እግዚአብሔር መንግሥት እና ስለ ሰማዩ አባታችን መልካምነት ነው።

በመሠረቱ እግዚአብሔር በዚህ መልኩ ነው የሚሠራው፤ ውጤቱን እና ጊዜውን አይደለም የሚመለከተው፤እርሱን ለማገልገል በመገኘት መሰጠታችንን ነው የሚያየው። እግዚአብሔር በሥራው ከፍትሃዊነት ባሻገር ነው፤ ምክንያቱም በጸጋው የሚደግፍ አምላከ ነውና፤ ጸጋውን ሲሰጠንም ከሚገባን በላይ አድርጎ ነው የሚለግሰን። ይሁን እንጂ በሰዋዊ አስተሳሰባቸው እና በእውቀታው መጠን፥ ታላቅነታቸውን መዝነው በመመካት፥ ከፊት ለመቅደም የሚሻሙት ከኋላ ይቀራሉ። ነገር ግን በትሕትና በእግዚአብሔር ምህረት በመመካት እና እርሱን በመደገፋቸው ከፊት ቀድመው ይገኛሉ። ስለሆነም "ኋለኞች ፊተኞች፥ ፊተኞችም ኋለኞች ይሆናሉ፤ የተጠሩ ብዙዎች፥ የተመረጡ ግን ጥቂቶች ናቸውና” (ቁ. 16)።

ቅድስት የሆነችው እናታችን ድንግል ማርያም፥ በእግዚአብሔር ተጠርተን ለመንግሥቱ ሥራ ተግተን በመሥራት የሚገኘው ደስታ እዲሰማን እና በፍቅሩ እንድንጠበቅ ትርዳን።

21 September 2020, 11:05