ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ ለወደፊቱ ትውልድ የሚሆን የተሻለ ዓለም በጋራ ለመገንባት እንችላለን አሉ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዘወትር ረቡዕ እለት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እንደ ሚያደርጉ የሚታወቅ ሲሆን በዛሬው እለት ማለትም በሐምሌ 29/2012 ዓ.ም ያደረጉት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ በአሁኑ ወቅት ዓለማችንን እጅግ በጣም እያስጨነቃት በሚገኘው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት እጅግ በጣም ጉዳት የደረሰባቸውን ሕዝቦች ለማጽናናት ይረዳ ዘንድ በማሰብ “ዓለምን መፈወስ” በሚል ዐብይ አርዕስት የቀረበ አስተምህሮ ሲሆን ለወደፊቱ ትውልድ የሚሆን የተሻለ ዓለም በጋራ ለመገንባት እንችላለን ማለታቸው ተግልጿል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በወቅቱ ያደረጉትን የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል ተከታተሉን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

ወረርሽኙ ተጋላጭነታችንን በመጠቀም ጥልቅ የሆኑ ቁስሎችን በእኛ ላይ መፍጠሩን ቀጥሏል። በሁሉም አህጉራት ውስጥ የሚገኙ ሕዝቦች ብዙዎች ሟቾች ፣ በጣም ብዙ በሽተኞች ሁነዋል። ብዙ ሰዎች እና ብዙ ቤተሰቦች በተለይም ድሆች በተከሰተው ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የተነሳ እርግጠኛ ባልሆነ ጊዜ ውስጥ በመኖር ላይ የገኛሉ።

በዚህ ምክንያት ትኩረታችንን በኢየሱስ ላይ ማድረግ አለብን (ዕብ. 12፣2) እናም በዚህ እምነት ኢየሱስ ራሱ ያመጣውን የእግዚአብሔርን መንግሥት ተስፋ እንቀበላለን (ማርቆስ1፡5፣ ማቴዎስ 4፡17፣ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ቁ. 2816)። ይህ የእግዚአብሔር መንግሥት በመካከላችን ያለ የመፈወስ እና የመዳን ኃይል ያለው መንግሥት (ሉቃ 10፡11) ነው። መልካም ተስፋን እና እምነትን የሚያጠናክረው በበጎ አድራጎት ሥራዎች ውስጥ የፍትህ እና የሰላም መንግሥት ነው (1ቆሮ 13፡13)። በክርስትና ባህል ውስጥ እምነት ፣ ፍቅር እና ተስፋ ከስሜቶች ወይም አመለካከቶች በላይ ናቸው። በመንፈስ ቅዱስ ጸጋ (የካቶሊክ ቤተክርስትያን ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ቁ. 1812-1813)  የሚፈውሱና ፈዋሾች የሚያደርጉን ስጦታዎች ፣ በችግሮቻችን እና አስቸጋሪ ጊዜያት ውስጥ ቢሆንም እንኳ ወደ አዲስ አድማስ እንድናመራ መንገዱን የሚከፍቱ ስጦታዎች ናቸው።

ከእምነት ወንጌል፣ ተስፋ እና ፍቅር ጋር በአዲስ መልክ መገናኘት እንችል ዘንድ የፈጠራ እና የታደሰ መንፈስ እንድንወስድ ይጋብዘናል። በዚህ መንገድ አካላዊ ፣ መንፈሳዊና ማህበራዊ ድክመቶቻችንን ከሥር መሰረታቸው መለወጥ እንችላለን። እርስ በእርሳችን የሚለያዩን ፍትህ የጎደላቸው መዋቅሮችን እና የሰውን ልጅ እና ምድራችንን አደጋ ላይ የሚጥሉ መጥፎ ድርጊቶችን በጥልቀት ለመፈወስ እንችላለን።

የኢየሱስ አገልግሎት ብዙ የመፈወስ ምሳሌዎችን ይሰጣል። በበሽታው የተጠቁትን ሰዎች ሲፈውስ (ማርቆስ 1፡29-34) ፣ የሥጋ ደዌ የተያዙትን ሲፈውስ (ማርቆስ 1፡40-45) ፣ ሽባውን ሲፈውስ (ማርቆስ 2፡1-12)፣ የታወረው ሰው ብርሃኑን መልሶ እንዲያገኝ ሲያደርግ (ማርቆስ 8፡22-26 ፤ ዮሐ 9፡1-7) ፣ የንግግር ወይም የመስማት ችግር የነበራቸውን ሰዎች ሲፈውስ (ማርቆስ 7፡31-37) ፣ በእውነቱ እርሱ አካላዊ ህመም ብቻ ሳይሆን አጠቃላዩን የሰው ልጅ ስጋዊ እና መንፈሳዊ ችግሮችን ይፈውሳል፣ የእርሱ ትኩረት ያው የሰው ልጅ ላይ ነው። በዚህ መንገድ ተገልለው የነበሩትን ሰዎች እርሱ ወደ ማህበረሰቡ ይመልሳቸዋል፣ ከመገለል ነጻ ያወጣቸዋል።

በቅፍርናሆም ይኖር የነበረ ሽባ ሰው መፈወሱን የሚገልጸውን የሚያምር ታሪክ አስቡ (ማርቆስ 2፡ 1-12)። ኢየሱስ በቤቱ መግቢያ ላይ እየሰበከ እያለ አራት ሰዎች ሽባውን ወዳጃቸውን ወደ ኢየሱስ አመጡት። ወደ ውስጥም ለመግባት ስላልቻሉ ወደ ጣሪያው ላይ ወጥተው ጣሪያውን ሸንቁረው በከፈቱት ቀዳዳ ሽባውብ ወዳጃቸውን ከላይ ወደ ታች አስገብተው በኢየሱስ ፊት አቀረቡት። “ኢየሱስም እምነታቸውን በማየት ሽባውን ልጄ ኃጢአትህ ተሰርዮልሃል”(ማርቆስ 2፡5) አለው። ከዚያም በኋላ አንድ ተጨባጭ የሆነ ምልክት ለማሳየት ፈልጎ “ተነስ  አልጋህን ተሸክመህ ወደ ቤትህ ሂድ” (ማርቆስ 2፡11) አለው።

ይህ የፈውስ ታሪክ እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ነው! የኢየሱስ ተግባር ለእነዚያ በእርሱ ላመኑ ሰዎች፣ በእርሱ ተስፋ ላደረጉ ሰዎች እና ለሌላው ወዳጃቸው ላሳዩት ፍቅር ቀጥተኛ የሆነ ምላሽ ነው። እናም ኢየሱስ ፈውሷል ፣ ነገር ግን ሽባውን ከአካላዊ በሽታው ብቻ ሳይሆን የፈወሰው ነገር ግን ኃጢአቱን ይቅር በማለት ሽባ የነበረውን ሰው እና የጓደኞቹን ሕይወት ያድሳል። አካላዊ እና መንፈሳዊ ፈውስ ፣ የግላዊ እና የማህበራዊ ስብስብ ውጤት ነው። ይህ ወዳጅነት እና በዚያ ቤት ያሉት ሰዎች ሁሉ እምነት ለኢየሱስ መገለጥ ምስጋናውን እንደሰጠ እንገምት።

ስለዚህ እራሳችንን እንጠይቃለን - ዛሬ የእኛን ዓለም ለመፈወስ እንዴት ማገዝ እንችላለን? የጌታ ኢየሱስ ደቀመዝሙሮች እንደመሆናችን መጠን የነፍስ እና የአካል ሐኪሞች ነን፣ በአካላዊ ፣ በማህበራዊ እና በመንፈሳዊ መልኩ “የፈውስ እና የመዳን ስራውን” (የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ 1421) እንድንቀላቀል ተጠርተናል።

ምንም እንኳን ቤተክርስቲያኗ በቅዱስ ቁርባን በኩል የክርስቶስን የፈውስ ጸጋ የምታከናውን ብትሆን እና እጅግ በጣም ርቀው በሚገኙ የምድራችን ማእዘኖች ውስጥ የጤና አገልግሎቶችን የምትሰጥ ብትሆንም ወረርሽኙን መከላከል ወይም የማከም አቅም ያላት ባለሙያ አይደለችም። ቤተክርስቲያን የተወሰነ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ አመላካች አቅጣጫዎችን አትሰጥም። ይህ የፖለቲካ እና ማህበራዊ መሪዎች ሥራ ነው። ሆኖም  ባለፉት ምዕተ ዓመታት ውስጥ ከቅዱስ ወንጌል አንፃር ቤተክርስቲያን አንዳንድ መሠረታዊ እና ማህበራዊ መርሆዎችን ታዘጋጃለች (የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ማሕበራዊ አስተምህሮ ቁ. ከ2015-208)፣ ወደፊት ለመራመድ እንድንችል ፣ በወደፊት ሁኔታ ውስጥ የሚገጥሙንን ችግሮች መወጣት የሚያስችሉንን እና የሚረዱን መርሆዎች ታዘጋጃለች። ዋናው እና ከሁሉም በላይ የሆነው ደግሞ እርስ በእርሳቸው  የተዛመዱትን  የግለሰቡ ክብር ፣ የጋራ ተጠቃሚነት፣ ለድሆች ከድህነታቸው እንዲላቀቁ አማራጭ መንገዶችን መቀየስ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሐብት ለሁሉም ሰው ተደራሽ እንዲሆን፣ አንድነት፣ መደጋገፍ ወይም መደጓገም፣ የጋራ መኖሪያ ቤታችንን መንከባከብ የመሳሰሉ ተግባራት ግባቸውን ይመቱ ዘንድ የሚያስችሉ ተግባራትን ታከናውናለች። እነዚህ ሁሉ መሰረታዊ መርሆች በእምነት፣ በተስፋ፣ በፍቅር እና በጎነትን ይገልጣሉ።

በሚቀጥሉት ሳምንታት ወረርሽኙ የጎላባቸው አሳሳቢ ጉዳዮችን በተለይም ማህበራዊ በሽታዎችን አንድ ላይ እንድንመለከት እጋብዛችኋለሁ። እናም እኛ በቅዱስ ወንጌል፣ በሥነ-መለኮታዊ በጎነት እና በቤተክርስቲያኗ ማህበራዊ ትምህርቶች መሰረታዊ መርሆዎች መሠረት አስተምህሮዋችንን እንቀጥላለን። የካቶሊክ ማህበራዊ አስተምህሮ ባህላችን የሰው ልጅ በከባድ በሽታዎች የሚሠቃይበት ይህን ዓለም ለመፈወስ እንዴት እንደሚረዳ እንመረምራለን። የኢየሱስ ተከታዮች እንደመሆናችን መጠን ፣ ለወደፊቱ ትውልድ በተስፋ የተሞላ የተሻለ ዓለም ለመገንባት እና ለማንፀባረቅ እንደ ምንችል ተስፋዬ እና ምኞቴ ነው።

05 August 2020, 12:06