ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስት ማርታ ሕንጻ ውስጥ በሚገኘው ቤተመጽሐፍት ውስጥ ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስት ማርታ ሕንጻ ውስጥ በሚገኘው ቤተመጽሐፍት ውስጥ  

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ ዓለምን መፈወስ የተሻለ ነገር ለመገንባት እድሉን ይከፍትልናል አሉ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዘወትር ረቡዕ እለት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እንደ ሚያደርጉ የሚታወቅ ሲሆን በዛሬው እለት ማለትም በነሐሴ 13/2012 ዓ.ም ያደረጉት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ በአሁኑ ወቅት ዓለማችንን እጅግ በጣም እያስጨነቃት በሚገኘው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት እጅግ በጣም ጉዳት የደረሰባቸውን ሕዝቦች ለማጽናናት ይረዳ ዘንድ በማሰብ “ዓለምን መፈወስ” በሚል ዐብይ አርዕስት ከጀመሩት አስተምህሮ ቀጣይ ክፍል እንደ ነበረ የተገለጸ ሲሆን በዛሬው እለት ባደረጉት የክፍል ሦስት አስተምህሮ “ዓለምን መፈወስ የተሻለ ነገር ለመገንባት እድሉን ይከፍትልናል” ማለታቸው ተገልጿል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በወቅቱ ያደረጉትን የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል ተከታተሉን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

ወረርሽኙ የድሆችን እና በዓለም ላይ እጅግ ከፍተኛ በሆነ መልኩ ሰፍኖ የሚገኘውን ያልተመጣጠነ ሕይወት አጋልጧል። ቫይረሱ ምንም እንኳን ሰዎችን እና በሰዎች መካከል ልዩነት ፈጥሮ የሚያጠቃ ባይሆንም ቅሉ በአሰቃቂ ሁኔታ በዓለማችን ውስጥ የሚገኘውን ታላቅ የሆነ ያልተመጣጠነ ሕይወት እና ምድሎ እንዳለ አጋልጧል። ስፋቱም እንዲጨምር አድርጓል።

ስለሆነም ለወረርሽኙ የሚሰጠው ምላሽ ሁለት ነው። በአንድ በኩል  መላውን ዓለም ያንበረከከው ትንሽዬ የሚመስል ግን አጅግ በጣም አስፈሪ ለሆነው ለዚህ ቫይረስ የሚሆን የመፈወሻ መድኅኒት ማግኘቱ የግድ አስፈላጊ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ በማህበራዊ ኢፍትሃዊነት ፣ በእኩልነት አለመኖር ፣ በማግለል እና ለጥቃት ተጋላጭ የሆኑ ሰዎችን ከጥቃት አለመጠበቅ. . . እነዚህን ትላልቅ ቫይረሶች መፈወስ ይኖርብናል። በእዚህ ድርብ የፈውስ ምላሽ ውስጥ  በወንጌሉ መሠረት ሊጎድል የማይችል ምርጫ አለ ፣ እሱ ለድሆች ቅድመ አማራጭ መስጠት ነው።

እግዚአብሔር የሆነው ክርስቶስ የሰዎችን መልክ ለብሶ ተገለጠ፣ የመጣውም ሊገለገል ሳይሆን ሊያገለግል ነው (ፊል 2 6-7)። እሱ የተወለደው ትሁት ቤተሰብ ውስጥ ሲሆን የእጅ ባለሙያ ነበር። በስብከቱ መጀመሪያ ላይ በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ ድሆች የተባረኩ መሆናቸውን ተናግሯል (ማቴ 5፡3 ፣ ሉቃ 6፡20)። እርሱ በታመሙ፣ በድሆች እና በተገለሉ ሰዎች መካከል በመሆን የእግዚአብሔርን ፍቅር ገልጿል (የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ ቁ. 2444)።

በዚህ ምክንያት የኢየሱስ ተከታዮች ለድሆች ፣ ለታናናሾች ፣ ለታመሙ እና ለታሰሩ ፣ ለተገለሉ  እና ለተረሱ ፣ ምግብ እና አልባሳት ለሌላቸው ሰዎች ቅርብ የሚሆኑት በዚሁ ምክንያት ነው (ማቴ. 25: 31-36፣ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ ቁ. 2443)። ይህ የአንድ ክርስቲያን ቁልፍ የሆነ መመዘኛ ነው (ገላ. 2፡10)። አንዳንዶች በስህተት ይህ ለድሀው ማሕበረሰብ የሚሰጠው ፍቅር የጥቂቶች ስራ ነው ብለው ያስባሉ ፣ ነገር ግን በእውነቱ እሱ የሁሉም የቤተክርስቲያኗ አባላት ተልዕኮ ነው። “እያንዳንዱ ክርስቲያንና እያንዳንዱ ማኅበረሰብ ለድሆች ነጻነትና ዕድገት እንዲሁም ሙሉ የኅብረተሰብ አካል እንዲሆኑ የእግዚአብሔር መሣሪያ መሆን ይጠበቅበታል” (የወንጌል ደስታ ቁ. 187) ።

እምነት ፣ ተስፋ እና ፍቅር አስፈላጊ የሆኑት እርዳታዎችን እንድናደርግ እና አልፎም ተርፎም ወደ አዚህ ምርጫ ውስጥ እንድንገባ ይገፋፉናል። በእውነቱ ይህ የሚያመለክተው በአንድነት አብሮ መጓዝን ፣ እነርሱ በስቃይ ውስጥ ያለፈውን ክርስቶስን እጅግ አድርገው ስለሚያውቁት፣ እነርሱ እኛን እንዲሰብኩን መፍቀድ እና በደህንነት ልምዳቸው ፣ በጥበባቸው እና በፈጠራቸው እኛንም በእነዚህ መልካም ነገሮች እንዲበክሉን ልንፈቅድ ይገባል። ለድሆች ካለን ማጋራት ማለት አንደኛው ሌላውን ማበልጸግ ማለት ነው። ለወደፊቱ ምቹ ጊዜ እንዳይመጣ የሚያግዱ የታመሙ ማህበራዊ መዋቅሮች ካሉ ፣ እነሱን ለመፈወስ ፣ ለመቀየር አብረን መሥራት አለብን። ይህ ወደር በሌለው ፍቅሩ ወደ ወደደን ወደ ክርስቶስ ፍቅር የሚያደርስ ብቸኛው መንገድ ነው (ዮሐ 13፡1) እናም ወደ ድንበሮች ፣ ወደ ተገለሉ፣ ወደ ዳርቻዎች ድረስ በመሄድ ራሳችንን ተደራሽ እንድናደር ይረዳናል። በዳርቻዎች ላይ የሚገኙትን ወደ ማእከሉ ማምጣት ማለት “በድሃነቱ” ሊያበለጽገን ራሱን “ድሃ” በማድረግ ለእኛ ያቀረበውን ክርስቶስ በሕይወታችን ውስጥ መካተት ማለት ነው (2 ቆሮ 8፡9)።

ሁላችንም ወረርሽኙ የሚያስከትለው ማህበራዊ ቀውስ አሳስቦናል። ብዙዎች ወደ ተለመደው መመለስ እና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎችን መቀጠል ይፈልጋሉ። በእርግጥ ግን ይህ “መደበኛነት” ማህበራዊ ኢፍትሃዊነትን እና በአካባቢ ላይ እየደረሰ የሚገኘውን ብክለት ማካተት የለበትም። ዛሬ የተለየ ነገር ለመገንባት እድል አለን። ለምሳሌ ድሆችን ሁል ጊዜ መርዳት ብቻ ሳይሆን ነገር ግን ድሆችን ማዕከል ያደረገ የኢኮኖሚ ልማት ማከናወን እንችላለን። ይሁን እንጂ፣ ኢኮኖሚው አዲስ መርዝ ወደሆኑ መፍትሔዎች ለምሳሌ፣ የሰው ኃይልን በመቀነስ ትርፍ ማጋበስን ብሎም ከሥራ የተገለሉ ሠራተኞች ማብዛትን ወደ መሰለ ሁኔታ ሊቀየር አይገባም፡፡ ይህ ዓይነቱ ትርፍ ተራውን ህዝብ ሊጠቅም ከሚችለው ከእውነተኛው ኢኮኖሚ እጅግ የተለየ ነው፣ እንዲሁም አንዳንድ ጊዜ በጋራ መኖሪያ ቤታችን ላይ ለሚደርሰው ጉዳት ግድየለሽ እንድንሆን ያደርገናል። ለድሀው ቅድሚያ ያለው ምርጫ ማቅረብ ከእግዚአብሔር ፍቅር የሚመጣው ሥነ ምግባር እና ማህበራዊ ፍላጎት ነው፣ ሰዎች በተለይም ድሃዎችን ያማከለ ኢኮኖሚያዊ አስተሳሰብ እና የፈጠራን ክህሎት ይሰጠናል፣ ድሆች መዕከል እንዲሆኑ ያደርጋል። እንዲሁም በጣም ተጋላጭ ለሆኑ ሰዎች ሁሉ ቅድሚያ በመስጠት ቫይረሱን ለማከም የሚያስችሉ እንክብካቤዎችን እንድናደርግ ያበረታታናል። እጅግ ባለጸጋ ለሆኑ ሰዎች የኮቪድ -19 ክትባት ቅድሚያ በመሰጠቱ እጅግ የሚያሳዝን ነው! እናም የምንመለከታቸው ሁሉም ኢኮኖሚያዊ ዕርዳታዎች - አብዛኛው ከሕዝብ ገንዘብ የተሰበሰቡ ሲሆን ነገር ግን ለተገለሉ ፣ አቅመ ደካማ ለሆኑ፣ ለጋራ ጥቅም የማይውሉ ከሆነ ይህ እንዴት የሚያሳዝን ነው!

ቫይረሱ ለድሆቹ እና በጣም ተጋላጭ ወደሆነው ዓለም ተቀጣጥሎ የሚቀጥል ከሆነ ይህንን ዓለም መለወጥ አለብን። የአካላዊ ፣ ማህበራዊ እና መንፈሳዊ ፈውስን የሆነውን የኢየሱስን ፍቅር ምሳሌ  በመከተል (ዮሐ 5: 6-9)  አሁን በዓይን በማይታዩ ቫይረሶች የተፈጠሩ ወረርሽኞችን ለመፈወስ እና ለማዳን  የሚረዱ እርምጃዎችን አሁን መውሰድ አለብን። እነዚህ በታላቁ እና በሚታዩ ማህበራዊ ኢፍትሃዊ ድርጊቶች የተፈጠሩ ናቸው። ይህ ከእግዚአብሔር ፍቅር በመጀመር ፣የተገለሉ ሰዎችን ወደ መሃል በማምጣት እና የመጨረሻዎቹን በመጀመሪያ ስፍራ ላይ በማስቀመጥ እንዲደረግ ሀሳብ አቀርባለሁ። ከዚህ ፍቅር በመነሳት በእምነት ላይ የተመሰረተ ተስፋ ላይ በመመስረት ጤናማ የሆነ ዓለም መመስረት እንችላለን።

19 August 2020, 11:17