ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በቫቲካን በሚገኘው በቅድስት ማርታ ሕንጻ ውስጥ በሚገኘው ቤተ መጽሐፍት ውስጥ ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በቫቲካን በሚገኘው በቅድስት ማርታ ሕንጻ ውስጥ በሚገኘው ቤተ መጽሐፍት ውስጥ  

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ ዓለም ሊፈወስ የሚችለው በወንድማማችነት መንፈስ ነው እንጂ በራስ ወዳድነት አይደለም አሉ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዘወትር ረቡዕ እለት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እንደ ሚያደርጉ የሚታወቅ ሲሆን በዛሬው እለት ማለትም በነሐሴ 06/2012 ዓ.ም ያደረጉት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ በአሁኑ ወቅት ዓለማችንን እጅግ በጣም እያስጨነቃት በሚገኘው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት እጅግ በጣም ጉዳት የደረሰባቸውን ሕዝቦች ለማጽናናት ይረዳ ዘንድ በማሰብ “ዓለምን መፈወስ” በሚል ዐብይ አርዕስት ባልፈው ሳምንት ከጀመሩት አስተምህሮ ቀጣይ ክፍል እንደ ነበረ የተገለጸ ሲሆን “ዐለምን ለመፈወስ የሚቻለው በወንድማማችነት መንፈስ ነው እንጂ በራስ ወዳድነት ወይም በግድዬለሽነት መንፈስ አይደለም” ማለታቸው ተግልጿል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በወቅቱ ያደረጉትን የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል ተከታተሉን።

    የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

ወረርሽኙ እኛ ሁላችንም ምን ያህል ተጋላጭ እና ተያያዥነት እንዳለን አጉልቶ ያሳያል። እርስ በእርሳችን አንዱ ለአንዱ እንክብካቤ ካላደረገ፣ እጅግ በጣም አቅመ ደካማ ከሆኑ ሰዎች ጀመረን፣ ተፈጥሮን ጨምሮ እንክብካቤ ማደረግ ካልቻልን ዓለምን መፈወስ አንችልም።

ከቅርብ ወራት ወዲህ ለባልነጃራዎቻቸው ሰብአዊ እና ክርስቲያናዊ ፍቅር ማረጋገጫ የሰጡ ብዙ ሰዎች ቁርጠኝነት ፣ ለታመሙ ሰዎች ጭምር ራሳቸውን የሰጡ ሰዎች ተግባር ተመልክተናል የሚመሰገን ተግባር ነው። ሆኖም ኮሮና ቫይረስ ልንዋጋው የሚገባው ብቸኛው በሽታ አይደለም፣ ነገር ግን ወረርሽኙ ሰፋ ያሉ ማህበራዊ በሽታዎችን ወደ ብርሃን በማምጣት ግልጽ አድርጎ አሳይቷል። ከነዚህ ውስጥ አንዱ ግለሰባዊ የሆነ የተዛባ ራዕይ ነው ፣ ክብሩን እና ግንኙነቱን የሚያሳጣ እይታ። አንዳንድ ጊዜ ሌሎችን እንደ መጠቀሚያ እናደርጋለን፣ እናም ተጠቀምን ለመጣል እንፈጥናለን። እንደ እውነቱ ከሆነ የዚህ ዓይነቱ እይታ ዓይነ ስውር የሆንን ግለሰቦች እንድንሆን በማደረግ ቁሳቁሶችን የማጋበስ መንፈስ ውስጥ እንድንገባ በማደረግ ግለሰባዊ እና የሽመታ ባህልን ያበረታታል።

ሆኖም በእምነት ብርሃን አማካይነት እግዚአብሔር ወንድ እና ሴትን በሌላ መንገድ እንደሚመለከት እንረዳለን።እሱ እኛን እንደ ቁሳቁሶች አልፈጠረንም ፣ ነገር ግን ሰውን በራሱ መልክ እና አምሳል ፈጥሮ የመውደድ እና የመወደድ ችሎታ ያላቸው ሰዎች አድርጎ ፈጠረ (ዘፍ 1፡27)። ከእዚህ ጋር ከእህቶቻችን እና ከወንድሞቻችን ጋር፣ ለፍጥረታት ሁሉ አክብሮት እንዲኖረን በመጋበዝ ልዩ ክብር ሰጠን። እናም በዚህ ህብረት ውስጥ እግዚአብሔር ትውልድን የማስቀጠል እና ምድርንም ፍጥረታትንም የመንከባከብ ችሎታ ይሰጠናል (ዘፍ 1፡28-29) እንድንሰራ እና ምድርን እንድንከባከብ ኃላፊነት ሰጠን (ዘፍ 2፡15)። በወንጌል ውስጥ የተጠቀሰው የደቀመዛሙርቱ ያዕቆብ እና ዮሐንስ እናት ለኢየሱስ ያቀረበችው ልመና የእያንዳንዱ ግለሰባዊ እይታ ምሳሌ ይገልጽልናል (ማቴ 20፡20 - 28)። የእነዚህ ደቀመዛሙርት እናት ልጆቿ በአዲሱ ንጉሥ በቀኝ እና በግራ መቀመጥ እንዲችሉ ትፈልጋለች። ነገር ግን ኢየሱስ ሌላ ዓይነት ራዕይን ያቀርባል፣ ይህም የአገልግሎት እና ሕይወትን ለሌሎች መስጠትን እና እንዲሁም ወዲያውኑ የሁለት ዓይነ ስውራንን ዓይን በማብራት እርሱ የመጣው ለአገልግሎት እንደ ሆነ ለደቀመዛሙርቱ ያረጋግጣል (ማቴ. 20፣29-34)።

ስለሆነም ለወንድሞቻችን እና ለእህቶቻችን በተለይም ለተሰቃዩ ሰዎች ትኩረት እንድንሰጥ ጌታ ዓይናችንን እንዲከፍትልን እንለምነው። የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እንደመሆናችን መጠን ግድየለሾች ወይም ግለሰባዊ ሰዎች መሆን አንፈልግም። ዘራቸው ፣ ቋንቋቸው ወይም ሁኔታቸው ምንም ይሁን ምን የእያንዳንዱ ሰው ክብር መገንዘብ እንፈልጋለን።

ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ አጽኖት የሚሰጠው ይህ ክብር “በእግዚአብሔር አምሳል ስለተፈጠረ ነው” በማለት ይናገራል። እሱ የሁሉም ማህበራዊ ሕይወት መሠረት ነው፣ ስለሆነም የስራ አፈፃፀም መርሆዎቹን ይወስናል። በዘመናዊ ባህል ውስጥ የሰው ልጆችን ሰብዓዊ ክብር የማያስከብር መርህ በጣም የሚያመለክተው ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እንደ ተናገሩት “በሰው ልጅ ረጅም እና አስቸጋሪ ጉዞ ላይ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ” የሰው ንቃተ-ህሊና ከፍተኛ መግለጫ የሆነ ዓለማቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌ ነው ማለታቸው ይታወሳል። መብቶች የግለሰቦች ብቻ ሳይሆኑ የሰዎች እና የብሔሮችም የማሕበረሰቡ እና የአገራትም ጭምር ናቸው። በእርግጥ የሰው ልጅ በግላዊ ክብሩ በሦስቱ ሥላሴ እና በአንዱ በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረ ማህበራዊ ፍጡር ነው።

ይህ አስተሳሰብ ስለማንኛውም ሰብዓዊ ፍጡር ክብር ግንዛቤ አዲስ ማህበራዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ አንድምታዎች አሉት። ወንድሞቻችን እና ፍጥረት ሁሉ በአብ ፍቅር የተሰጡን ስጦታ አድርጎ መመልከቱ የመተሳሰብ ፣ የእንክብካቤ እና የመደነቅ ባህሪን ያነሳሳል። ስለሆነም አማኙ ባልንጀራውን እንደ እንግዳ ሳይሆን እንደ ወንድም አድርጎ በመቁጠር በንቀት ወይም በጠላትነት አይመለከትም። እናም በእምነት ብርሃን ዓለምን በማሰላሰል ፣ በታላቅ እፎይታ ፣ በታላቅ ችሎታ እና በታታሪነት የታሪክን አሳዛኝ ችግሮች ለመፍታት በማተኮር ላይ ይሠራል። እንደ እግዚአብሔር ስጦታዎች ሰዎች እና ፍጥረትን ለማገልገል ከእምነት በፈለቀ መልኩ ስጦታዎች መጠቀም ይችል ዘንድ የኃላፊነት መንፈስ እንዲፀነስ እና እንዲያድግ ያደርጋል።

ሁሉንም በተዘዋዋሪ የሚጎዳ ቫይረስን ለመቋቋም በምንሰራበት በአሁኑ ወቅት ​​እምነት በሰው ልጆች ክብር ላይ የሚደርሱትን ጥሰቶች እና ግዴለሽነትን ለመቋቋም እራሳችን በቁርጠኝነት እና በንቃት እንድንሰራ ያሳስበናል፣ እምነት ከራስ ወዳድነት መንፈስ እንድንፈወስ እና እንድንለወጥ ይረዳናል።

የሰብአዊው ቤተሰብ አባላት መሆን ማለት ምን ማለት እንደሆነ እንድንረዳ ጌታ “ዓይናችንን ይክፈትልን”። እናም ይህ እይታ ለእያንዳንዱ ሰው ርህራሄ እና አክብሮት እንድናሳይ፣ የጋራ የመኖሪያ ቤታችንን እንድንከባከብ እና ወደ ተጨባጭ ተግባራት እንድንተረጉም ሊረዳን ይችላል።

 

12 August 2020, 10:42