ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ  

ር.ሊ. ጳ ፍራንቸስኮስ "የክርስቶስ ተከታይ መሆን ከፈለግን ክርስቶስን መምሰል ይኖርብናል" አሉ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በነሐሴ 24/2012 ዓ.ም፣ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ፣ ዘወትር እሁድ በእለቱ ቅዱስ ወንጌል ላይ ተንተርሰው የሚያደርጉትን የቅዱስ ወንጌልን አስተንትኖ ለመከታተል በስፍራው ለተገኙ ምዕመናን በወቅቱ ያደርጉት አስተንትኖ (በማቴዎስ ወንጌል 16፡21-27)  ላይ በተጠቀሰው  ኢየሱስ “የሚወደኝ ቢኖር እራሱን ይካድ መስቀሉን ተሸክሞ ይከተለኝ" የሚለው ላይ ያጠነጠነ ነው።ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም በሚጓዝበት ጊዜም ለሐዋሪያቱ በቅድስቷ ከተማ እየሩሳሌም በስተ መጨረሻ ስለሚጠብቀው መከራ፣ሞት እንዲሁም ስለትንሳዔው ክብር አስቀድሞ በግልጥ ነገራቸው፡፡ነገር ግን ሐዋሪያቱ እምነታቸው የጠነከረ ስላልነበር እና እንዲሁም አስተሳሰባቸው ከዚህዓለም ጋር የተቆራኘ በመሆኑ ሊረዱት አልቻሉም፡፡በመሆኑም ሐዋሪያው ጴጥሮስም የክርስቶስ በመስቀል ላይ መሞት ስላልተዋጠለት "አይሁንብህ ጌታ ሆይ!ይህ ከቶ አይደርስብህም ብሎ ሊገስጸው ጀመር፡፡ክርስቶስ ግን ዘወር ብሎ ጴጥሮስን ወደ ኋላዬ ሂድ አንተ ሰይጣን! የሰውን እንጂ የእግዚአብሔርን አታስብምና ዕንቅፋት ሆነህብኛል አለው፡፡ለጴጥሮስ፣ለሌሎች ሐዋሪያቶች እና እንዲሁም ለእኛም የክርስቶስ የመስቀል ሞት የሚያሳዝን እና መከራ የበዛት ነው፡፡ነገር ግን የመዳናችን ምሥጢር የታየበት ነው፡፡በመሆኑም ያለምንም ማንገራገርም ሕይወታችንን ለእግዚአብሔር እንዲሁም ለሌሎች እንድንሰጥ ተጠርተናል በሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ መሰረት ያደረገ አስተንትኖ እንደ ነበረ የተገለጸ ሲሆን “­­"የክርስቶስ ተከታይ መሆን ከፈለግን ክርስቶስን መምሰል ይኖርብናል" ማለታቸው ተገልጿል።

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በእለቱ ያደረጉትን አስተንትኖ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል፣ ተከታተሉን።

የተወደዳችሁ ወንድቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ! የዛሬው የወንጌል አስተምህሮ ከማቴ. ወን.ም.16፡ ከ21-27 ላይ ያጠነጠነ ይሆናል፡፡ይህ የወንጌል ክፍል ከባለፈው ሳምንት ካስተነተንበት የወንጌል ሐሳብ፣ እሱም የማቴ.ወን.ም.16፡ ከ13-20 ካለው ጋር የጠበቀ ግኑኝነት ያለው ነው፡፡ሐዋሪያው ቅዱስ ጴጥሮስ ሌሎቹን ሐወዋሪያት ወክሎ የክርስቶስን መሲህነት እና የሕያው የእግዚአብሔር ልጅነትን ከመሠከረ በኋላ፣ክርስቶስ ስለ መስቀል ጉዞው ይነግራቸው ጀመረ፡፡ወደ ኢየሩሳሌም በሚጓዝበት ጊዜም ለሐዋሪያቱ በቅድስቷ ከተማ እየሩሳሌም በስተ መጨረሻ ስለሚጠብቀው መከራ፣ሞት እንዲሁም ስለትንሳዔው ክብር አስቀድሞ በግልጥ ነገራቸው፡፡ከሽማግሌዎች እና ከካህናት አለቆች፤ከጻፎችም ብዙ መከራ ይቀበልና ይገደል ዘንድ እንዲሁም በሶስተኛውም ቀን ይነሳ ዘንድ እንዲገባው ፤ለደቀመዛሙርቱ ይገልጥላቸው ጀመር፡፡ነገር ግን ሐዋሪያቱ እምነታቸው የጠነከረ ስላልነበር እና እንዲሁም አስተሳሰባቸው ከዚህዓለም ጋር የተቆራኘ ስለነበር ሊረዱት አልቻሉም፡፡

ሐዋሪያው ጴጥሮስም የክርስቶስ በመስቀል ላይ መሞት ስለከበደው እና ስላልተዋጠለት "አይሁንብህ ጌታ ሆይ!ይህ ከቶ አይደርስብህም ብሎ ሊገስጸው ጀመር፡፡" ሐዋሪያው ጴጥሮስ በክርስቶስ ያምናል፣ሊከተለውም ወዷል ነገር ግን ክርስቶስ ስለሁላችን በመስቀል ሞት ስቃይ እንዲያልፍ ሐዋሪያው ጴጥሮስ አልፈለገም፡፡ለጴጥሮስ፣ለሌሎች ሐዋሪያቶች እና እንዲሁም ለእኛም የክርስቶስ የመስቀል ሞት የሚያሳዝን እና መከራ የበዛት ነው፡፡ነገር ግን እኛን ለማዳን እና የአባቱን ፈቃድ ለመፈጸም የተከፈለ መሥዋትነት በመሆኑ ክርስቶስ ከመጣበት ዓላማ ፈቀቅ ሊል አልሆነም፡፡ለዚህም ነው ክርስቶስ ዘወር ብሎ ጴጥሮስን ወደ ኋላዬ ሂድ አንተ ሰይጣን የሰውን እንጂ የእግዚአብሔርን አታስብምና ዕንቅፋት ሆነህብኛል አለው፡፡

ከዚህም በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሁላችንንም በሚመለከት መልኩ እንዲህ አለ፤ይኸውም፦ እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር ራሱን ይካድ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ አለ፡፡በዚህም መንገድ ሁለት እውነተኛ ሐዋሪያ የመሆኛ መንገዶችን አስታወቀ፡፡የመጀመሪያው ራስን መካድ ነው፤ይህም የሚሆነው ደግሞ በማስመሰል አይደለም፤በእውነተኛ መለወጥ የሚሆን ነው፡፡ሁለተኛው እውነተኛ ሐዋሪያ የመሆኛ መንገድ ደግሞ መስቀሉን ተሸክሞ ይከተለኝ እንዳለው ማድረግ ነው፡፡ይህም ማለት የየለት ተለት የሕይወት ጥቄዎቻችንን በትግስት መመለስን ብቻ ሳይሆን በእምነት እና በሃላፊነት ድካምን እና መከራን መሻገር ነው፡፡

ስለዚህም መስቀላችንን ተሸክመን ክርስቶስን የመከተል መሰጠታችን በክርስቶስ የዓለም አዳኝነት ተሳታፊ ያደርገናል፡፡ይህንን በምናስብበት ጊዜ እርግጠኛ መሆን ያለብን፥በየቤታችን ግርግዳ እና አንገታችንም ላይ የምናደርገው መስቀል፤ወንድሞቻችን እና እህቶቻችንን በፍቅር በማገልገል ከክርስቶስ ጋር ሕብረትን የምንፈጥርበት የአንድነት ምልክት ነው፡፡መስቀል የእግዚአብሐር ፍቅር እና የክርስቶስ መሥዋትነት የታየበት የተቀደሰ የድነታችን መሳሪያ ነው፡፡በመሆኑም እንደ ጌጥ በማድረግ ፋይዳውን ማሳነስ አይገባም፡፡ሁል ጊዜም የተሰቀለውን የክርስቶስን ምስል በምንመለከትበት ወቅት፤እርሱ እንደ እውነተኛው የእግዚአብሔር አገልጋይ፣እራሱን ስለሌሎች አሳልፎ በመስጠት ዓላማውን እንደፈጸመ እና ሐጥያታችንን በደሙ ያጠበ ስለመሆኑ እናስባለን፡፡በመሆኑም የክርስቶስ ተከታይ መሆን ከፈለግን፥እርሱን እንድንመስል እና ያለምንም ማንገራገርም ሕይወታችንን ለእግዚአብሔር እንዲሁም ለሌሎች እንድንሰጥ ተጠርተናል፡፡

እስከ መስቀል ሞቱ ድረስ የተጓዘችው ድንግል ማሪያም የክርስቶስን አዳኝነት ከመመስከር የሚመጣ መከራ እንዳንሸሽ ትርዳን፡፡

30 August 2020, 15:17