ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ 

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ አሳዛኝ የሆኑ ታሪኮቻችን ሁሉ ይፈወሱ ዘንድ በኢየሱስ እግር ስር እናስቀምጥ አሉ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በነሐሴ 10/2012 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ እርሳቸው ዘወትር እሁድ በእለቱ ቅዱስ ወንጌል ላይ ተንተርሰው የሚያደርጉትን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ለመከታተል በስፍራው ለተገኙ ምዕመናን ቅዱስነታቸው በወቅቱ ያደርጉት አስተንትኖ (በማቴዎስ ወንጌል 15፡21-28)  ላይ በተጠቀሰው የከነዓናዊቷ ሴት እምነት በሚገልጸው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ መሰረቱን ያደረገ ሲሆን ታሪካችንን በኢየሱስ እግር ስር እናስቀምጥ ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በእለቱ ያደረጉትን አስተንትኖ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል፣ ተከታተሉን።

የተወደዳችሁ ወንድሞች እና እህቶች እንደምን አረፈዳችሁ!

የዛሬው እለተ ሰንበት ቅዱስ ወንጌል (ማቴ. 15: 21-28 ተመልከት) በኢየሱስ እና በከነዓናዊት ሴት መካከል የተደረገውን ግንኙነት ይገልጻል። በወቅቱ ኢየሱስ በገሊላ በስተ ሰሜን አቅጣጫ በባዕድ አገር ክልል ውስጥ ይገኝ ነበር። ሴትዮዋ አይሁዳዊ አይደለችም ከነዓናዊ ነበረች። ኢየሱስ በእዚያ ስፍራ የተገኘው ቁጥራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ከመጣው ሕዝብ ተልይቶ ለተወሰነ ጊዜ ከደቀመዛሙርቱ ጋር በእዚያ ሊቆይ ወስኖ ነበር ወደ እዚያ የተጓዘው። እነሆም አንዲት ሴት የታመመች ልጇን ይዛ መጥታ እርዳታ እየፈለገች ወደ እርሱ ቀርባ: - “ጌታ ሆይ ማረኝ!” (ማቴ 15፡ 22) አለችው። የዚህች ሴት ልጅ መዳን በማይችል በእርኩስ መንፈስ ተይዛ ስትሰቃይ እያየች ከእናትነት ረዳትነት ስሜት በመነሳት ከስቃይ በመነጨ መልኩ የተወለደ ጩኸት ናው ፣ እሷ ልትፈውሳት አትችልም። ኢየሱስ በመጀመሪያ እርሷን ችላ ብሎ ነበር ፣ ነገር ግን ይህች እናት ኢየሱስን አጥብቃ ያዘች፣ ጌታ ለደቀመዛሙርቱ እርሱ የተሰጠው ተልእኮው “ከእስራኤል ቤት ለጠፉት በጎች ብቻ” (ማቴ 15፡24) እንደ ሆነ  እንጂ ለአረማዊያን እንዳልሆነ ይናገራል። እሷ እሱን መማጸኗን ቀጠለች ፣ እናም በዚያ ነጥብ ላይ እርሷን ሊፈትን ፈልጎ አንድ ምሳሌ በመናገር ትንሽ ጭካኔ የተሞላ በሚመስል መልኩ እርሷን ሊፈትናት ፈለጎ እርሱም መልሶ፣ “የልጆችን እንጀራ ወስዶ ለውሾች መወርወር አይገባም” (ማቴ 15፡26) አላት። እናም ወዲያውኑ ሴትየዋ በፍጥነት “አዎን ጌታ ሆይ ፣ ውሾችም እንኳ ከጌቶቻቸው ማዕድ የወደቀውን ፍርፋሪ ይበላሉ” (ማቴ 15፡27) በማለት ትመልሳለች።

እናም በእነዚህ ቃላት ያቺ እናት ለፍጥረታቱ ፍላጎቶች ሁሉ ክፍት በሆነው በኢየሱስ ውስጥ የሚገኘውን የልዑሉን አምላክ በጎነት እንደተገነዘበች ያሳያል። በመተማመን የተሞላው ይህ ጥበብ የኢየሱስን ልብ ይነካል እናም የአድናቆትን ቃላት ያነሳሳል: - “አንቺ ሴት እምነትሽ ታላቅ ነው! እንደፈለግሽው ይሁንልሽ” (ማቴ 15፡ 28) አላት። ምን ዓይነት እምነት ነው? ታላቅ እምነት የራሱን ታሪክ የሚያመጣ ፣ በቁስሎች እንኳን ምልክት የተደረገበት እና እነሱን እንዲፈውሳቸው እና ትርጉም እንዲሰጥ ወደ ጌታ እግር ሥር የሚያመጣ የእምነት ዓይነት ነው።

እያንዳንዳችን የራሳችን የሆነ ታሪክ አለን፣ እናም ይህ ታሪክ ሁልጊዜ “ወደ ውጭ የሚወጣ” ታሪክ ብቻ አይደለም ፣ እሱ ሁል ጊዜ ንፁህ የሆነ ታሪክ ብቻ አይደለም… ብዙ ጊዜ ከባድ ታሪክ ፣ በብዙ ሥቃዮች እና በብዙ ኃጢአቶች የተሞላ ከባድ ታሪክ ነው። የእኔን ታሪክ ምን አደርጋለሁ? ደብቄዋለሁ ወይ? አይ በፍጽም እንድህ ማድረግ አይኖርብንም! እኛ በጌታ ፊት ማቅረብ አለብን። “ጌታ ሆይ ከፈለግህ ልትፈውሰኝ ትችላለህ!” ብለን በፊቱ ልናቀርብ ይገባል። ይህች ሴት፣ ይህች ግሩም እናት የምታስተምረን-የራሳችንን አሳዛኝ ታሪኮችን በእግዚአብሔር ፊት ለማምጣት ድፍረቱ እንዲኖረን ፣ በእግዚአብሔር ፊት ፣ በኢየሱስ ፊት በማቅረብ የእርሱ ፍቅር እና የኢየሱስ ርህራሄ ታሪካችንን እንዲዳሥ ማድረግ ይኖርብናል። እስቲ ይህንን ታሪክ እንሞክረው፣ ይህ ጸሎት ነው-እያንዳንዳችን ስለራሳችን ታሪክ እናስብ። በታሪክ ውስጥ ሁል ጊዜም አስቀያሚ ነገሮች አሉ። ወደ ኢየሱስ እንሂድ ፣ የኢየሱስን ልብ አናንኳኳና “ጌታ ሆይ ፣ ከፈለግህ ልትፈውሰኝ ትችላለህ!” እንበል። እናም የኢየሱስ ፊት ሁልጊዜ ከፊት ለፊታችን የሚታየን ከሆነ ይህንን ማድረግ እንችላለን፣ የክርስቶስ ልብ ምን እንደ ሆነ፣ የኢየሱስ ልብ ምን እንደሚመስል ከተረዳን ይህንን ማድረግ እንችላለን፣ - ሥቃያችንን የሚሸከም ፣ ሀጢያታችንን የሚሸከም ፣ ስህተታችንን፣ ውድቀቶቻችንን በርህራሄ የሚመለከት ልብ እንዳለው እንገነዘባለን። የኢየሱስ ልብ ሁሌም ይወደናል። “ጌታ ሆይ ፣ ከፈለግህ ልትፈውሰኝ ትችላለህ!” እንበለው። ለዚህም ነው ኢየሱስን ማወቅ ፣ ከኢየሱስ ጋር መተዋወቅ አስፈላጊ የሆነው። እኔ ከእዚህ በፊት ለእናነት ተናግሬ ወደ ነበረው ምክር ሁሌም የምመለሰው ለዚሁ ነው፣ ሁል ጊዜ ትንሽዬ በኪሳችን ልትገባ የምትችል መጽሐፍ ቅዱስ ይዘን እንጓዝ፣ በእየቀኑ አንድ የቅዱስ ወንጌል ክፍል እናንብ የምለው ለዚህ ነው። በወንጌል ውስጥ እየሱስን ራሱን እናገኘዋለን፣ በዚያም እርሱ ራሱን ለእኛ ይቀርባል፣ እዚያም ይገኛል፣ እኛን የሚወደን ኢየሱስ፣ እጅግ በጣም የሚወደን ደህንነታችንን የሚሻውን ኢየሱስ በእዚያ ታገኙታላችሁ። “ጌታ ሆይ ፣ ከፈለግህ ልትፈውሰኝ ትችላለህ!” የሚለውን ጸሎት እናስታውስ። መልካም የሆነ ጸሎት ነው። መጽሐፍ ቅዱስን ሁልጊዜ ይዛችሁ ለመጓዝ ሞክሩ፣ በኪሳችሁ በቦርሳችሁ ያዙት፣ በተንቀሳቃሽ ስልክዎ ላይም ቢሆንም እንኳን መጽሐፍ ቅዱስን ጫኑ። ያቺ ክርስቲያን ያልነበረች፣ ያቺ አይሁዳዊ ያልነበረች ነገር ግን አረማዊ የነበረቺው ሴት ያስተማረችንን ይህንን ግሩም የሆነ ጸሎት ሁላችንም እንድንጸልይ ጌታ ይርዳን።

በእያንዳንዱ የተጠመቀ ሰው ሁሉ ላይ እምነት ደስታ እንዲጨምር እንዲሁም በተከታታይ የህይወት ምስክርነት በኩል የመገናኘት ፍላጎት እንዲያድግ ድንግል ማርያም በጸሎቷ እንድትረዳን፣ “ጌታ ሆይ ፣ ከፈለግህ ልትፈውሰኝ ትችላለህ!” በማለት መጸለይ እንችል ዘንድ እንድትረዳን አማላጅነቷን እንማጸን።

16 August 2020, 10:34