ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በድሆች፣ በሽተኞች እና በስደተኞች ፊት ላይ የእግዚአብሔርን ፊት ፈልጉ አሉ!

እንደ ጎሮጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር በሐምሌ 08/2013 ዓ.ም  ላፓዱዛ በመባል በሚታወቀው አንድ የጣሊያን የወደብ ከተማ አቅራቢያ የዛሬ ሰባት አመት ገደማ በተለየያዩ አስገዳጅ ምክንያቶች የተነሳ ቤት ንብረታቸውን ጥለው በመሰደድ እጅግ በጣም አስከፊ የሆኑ መንገዶችን በማለፍ በሊቢያ በኩል ወደ ጣሊያን በጀልባ ለመግባት ሲሞክሩ በነበረበት ወቅት በጀልባው ላይ በደርሰው አደጋ ከ3000 ሺህ በላይ ሰዎች መሞታቸው የሚታወስ ሲሆን በወቅቱ ይህ አደጋ በዓለም ዙሪያ የመነጋገሪያ አርእስት ሆኖ ማለፉ ይታወሳል። በወቅቱ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ አደጋው በደርሰበት ላፓዱዛ በመባል በሚታወቀው የጣሊያን የወደብ ከተማ ተገኝተው በአደጋው ሕይወታቸውን ላጡ ሰዎች ጸሎት ማደርጋቸው እና እንዲሁም ከእዚህ አስከፊ አደጋ በተዐምር የተረፉ ስድተኞች በተገኙበት መስዋዕተ ቅዳሴ ማሳረጋቸው የሚታወስ ሲሆን ከእዚያን ጊዜ አንስቶ በእዚህ አሰቃቂ አደጋ ሕይወታቸውን ያጡ ስደተኞችን በማስታወስ በእየአመቱ መስዋተ ቅዳሴ እንደ ሚያሳርጉ ይታወቃል። በእዚህም መሰረት በሊቢያ በኩል አድርገው ወደ ጣሊያን ለመሻገር በሚሞክሩበት ወቅት እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር በሐምሌ 08/2013 ዓ.ም የዛሬ 7 ዓመት ገደማ ላፓዱዛ በመባል በሚታወቀው የጣሊያን የወደብ ከተማ አከባቢ ሕይወታችውን ላጡ ሰዎች ሰባተኛ አመት መታሰቢያ በቫቲካን በሚገኘው በቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት ውስጥ በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ መሪነት በሐምሌ 01/2012 ዓ.ም መስዋዕተ ቅዳሴ መደረጉ የተገለጸ ሲሆን ቅዱስነታቸው በወቅቱ ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ባሰሙት ስብከት እንደ ገለጹት “በድሆች፣ በሽተኞች እና በስደተኞች ላይ የእግዚአብሔርን ፊት ፈልጉ”  ማለታቸው ተገልጿል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በእለቱ ያደርጉትን ስብከት ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰንድተነዋል ተከታተሉን።

ዛሬ ከመዝሙረ ዳዊት ተወስዶ የተነበበልን የእግዚአብሔር ቃል የጌታን ፊት ያላማቋረጥ እንድንፈልግ የሚጋብዘን ሲሆን እንዲህም ይላል “እግዚአብሔርንና ብርታቱን ፈልጉ፤ ፊቱንም ዘወትር ፈልጉ” (መዝሙር 105፡ 4) በማለት ይናገራል። ይህ ፍለጋ የአንድ ሰው ሕልውና የመጨረሻ ግብ ከእግዚአብሄር ጋር መገናኘት መሆኑን በተረዳ አማኝ ሕይወት ውስጥ መሠረታዊ አመለካከት ይመሰርታል።

የእግዚአብሔር ፊት ፍለጋ ወደ እውነተኛው ተስፋይቱ ምድር ፣ ወደ ሰማያዊው አገር በምናደርገው ጉዞ የመውጫ መንገድ ነው፣ በዚህ ዓለም ውስጥ ለምናደርገው ጉዞ ስኬት ዋስትና ነው። የእግዚአብሔር ፊት ግባችን ነው፣ እናም ትክክለኛ መንገዱን እንዳናጣ ያስችለናል።

በመጀመሪያው ንባብ በነብዩ ሆሴዕ እንደ ተገለጸው (ትንቢተ ሆሴዕ 10፡1-3.7-8.12) የእስራኤል ሕዝብ በዚያን ጊዜ ተስፋይቱን ምድር በማጣት በኃይለኛ ምድረ በዳ እየተቅበዘበዘ የጠፋ ሕዝብ እንደ ሆነ ይናገራል። ብልጽግና እና የተትረፈረፈ ሀብት እስራኤላውያን ልባቸውን ከእግዚአብሔር ዘንድ እንዲያዞሩ እና  በሐሰት እና በግፍ እንዲሞሉ አድርጎ ነበር።

እኛ በዛሬ ዘመን የምንኖር ክርስቲያኖች እየገጠመን የሚገኝ የኃጢአት ዓይነት ነው። ስለራሳችን ሕይወት ብቻ እንድናስብ የሚያደርገን ባህል የሌሎችን ጩኸት ቸል እንድንል ያደርገናል ፣ የሳሙና አረፋ በሚምሰል ሕይወት ውስጥ ገብተን እንድንኖር ያደርገናል፣ እነሱ ምቾት ይሰጡናል፣ ነገር ግን ዘላቂ አይደለም፣ እነሱ ከንቱ ፣ጊዜያዊ የሆኑ ነገሮች ሲሆኑ ስለ ሌሎች ጉዳይ ግድየለሽ እንድንሆን ያደርጉናል፣ በእርግጥ ዓለም አቀፋዊ ወደ ሆነ ግድየለሽነት ይመራናል ።

የነቢዩ ሆሴዕ ምልጃ ዛሬ ዓይናችንን ወደ ጌታ በማዞር በአዲስ መልክ መንፈሳዊ ለውጥ እንድናመጣ ወደ ጌታ እንድንመለስ የቀረበልን ግብዣ ነው። ነብዩ ሆሴዕ እንዲህ ይላል “ለራሳችሁ ጽድቅን ዝሩ፤ የጽኑ ፍቅርን ፍሬ ዕጨዱ፤ ዕዳሪውንም መሬት ዕረሱ፤ እርሱም መጥቶ፣ ጽድቅን በላያችሁ እስኪያዘንብ ድረስ፣ እግዚአብሔርን የምትፈልጉበት ጊዜ ነውና” (ሆሴዕ 10፡ 12) በማለት ያናገራል።

የእግዚአብሄርን ፊት ፍለጋን የእርሱን ታላቅ ፍቅር እና የማዳን ኃይሉን በመፈለግ  ከጌታ ጋር በግል የመገናኘት ጉጉት የተነሳሳ ነው። የዛሬው ቅዱስ ወንጌል ለእኛ የሚናገረን  ነገር አሥራ ሁለቱ ሐዋሪያት (ማቴ 10፡1-7) ሥጋ የለበሰው የእግዚአብሔር ልጅ በሆነው ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ሐዋርያቱ በአካል በተገናኙበት ወቅት ስላገኙት ፀጋ ይናገራል። እርሱ እያንዳንዱን በዓይኑ እየተምነለከተ በስማቸው ይጠራቸዋል፣ እነርሱም በፊቱ ቆመው ነበር ፤ ቃሉንም አዳመጡ፥ ተአምራቶቹንም አዩ። ከጌታ ጋር በግል መገናኘት ፣ የችሮታ እና የመዳን ጊዜ ተልእኮውን የሚያካትት ነው  “ሄዳችሁም፣ ‘መንግሥተ ሰማያት ቀርባለች’ ብላችሁ ስበኩ” (ማቴ 10፡7) በማለት እንዲሰብኩ ይልካቸዋል።ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ሐዋርያቱ የነበራቸው ይህ የግል ግንኙነት ከሦስት ምዕተ አመታት በኋላ ለምንገኝ የእርሱ ደቀመዛሙርት ለሆንን እኛ ገቢራዊ ለማደረግ እንችላለን። የጌታን ፊት ለመፈለግ ስንነሳ እግዚአብሔር በመንገዳችን ላይ በሚያስቀምጣቸው ድሆች፣ በሽተኞች፣ የተዘነጉ ሰዎች እና ባዕዳን ፊት ላይ ሳይቀር የጌታን ፊት ልንመለከት እንችላለን። ደግሞም ይህ ግንኙነት እና የጌታ ፊት ፍለጋ ለሐዋሪያት በተሰጡት ተመሳሳይ ተልዕኮዎች ላይ እንድንሳተፍ በማድረግ ለእኛም ይህ የጸጋ እና የድህንነት ጊዜ ሊያመጣልን ይችላል።

ላምፓዱዛን የጎበኘሁበት ሰባተኛ ዓመት ዛሬ እያስታወስን እንገኛለን። በእግዚአብሄር ቃል ብርሃን በመመራት ባለፈው ዓመት የካቲት ወር ላይ “ከፍርሃት ነፃ” በሚል መሪ ቃል ተደርጎ በነበረው ስብሰባ ላይ ለተሳተፉ ሰዎች የተናገርኩትን ነገር በድጋሜ ለመናገር እፈልጋለሁ “ከሌላው ጋር የሚደረግ ግንኙነት ከክርስቶስ ጋር የሚደረግ ግንኙነት ነው ፡፡ እሱ ራሱ ነው ይህንን የተናገረው። እርሱ ራሱ ነው የእኛን በሮች በማንኳኳት የተራበውን፣ የተጠማውን፣ እንግዳ የሆነውን፣ የታረዘውን፣ የታመመውን፣ የታሰረውን፣ እንግዳ የሆነውን   እንድንገናኝ እና እንድንረዳ የሚጠይቀው እርሱ ነው። አሁንም ቢሆን ጥርጣሬ ካደረብን ግልጽ የሆነው ቃሉ እነሆ “እውነት እላችኋለሁ፣ ከእነዚህ አነስተኛ ከሆኑት ወንድሞቼ ለአንዱ ያደረጋችሁት፣ ለእኔ እንዳደረጋችሁት ነው’ ይላቸዋል። (ማቴ 25፡40)።

«የምታደርጉት ሁሉ ...» ለበጎ ይሁን ለክፋት! ይህ ማስጠንቀቂያ የዛሬን ርዕሰ-ጉዳይ የሚመለከት ነው።ሁላችንም የሕሊናችንን የዕለት ተዕለት ሕይወት ለመመርመር የምንጠቀምበት መሠረታዊ ነጥብ ሊሆን ይገባል። በሊቢያ የስደተኞ ማጎሪያ ካምፖች ውስጥ በእስር ላይ የሚገኙትን ስደተኞች አስባለሁ፣ እነዚህ ስደተኞች እየደረሰባቸው የሚገኘውን ግፍ እና ችግር እንዲሁም በተስፋ ጉዞዋቸውን ለመቀጠል የሚያደርጉትን ተስፋ ለመደገፍ የሚደረጉ ጥሮቶችን መደገፍ ይገባል። “ከእነዚህ አነስተኛ ከሆኑት ወንድሞቼ ለአንዱ ያደረጋችሁት፣ ለእኔ እንዳደረጋችሁት ነው” የሚለውን ቃል ዘወትር ማሰብ ያስፈልጋል።

ዓለማችን አሁንም በተለያዩ አስቸጋሪ ሁኔታዎች እና በብዙ ኢፍትሐዊ ድርጊቶች ምክንያት አገራቸውን ጥለው ለመሸሽ ለተገደዱ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ፊት ላይ ልጇን ኢየሱስን መመልከት እንችል ዘንድ የስደተኞች አጽናኝ የሆነቺው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትርዳን።

08 July 2020, 14:14