ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከ7 ዓመት በፊት ወደ ላምፔዱሳ ያደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት፤ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከ7 ዓመት በፊት ወደ ላምፔዱሳ ያደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት፤  

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ወደ ላምፔዱሳ ያደረጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት 7ኛ ዓመት በጸሎት ያስታውሱታል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ስልጣን ከተቀበሉ በኋላ ወደ ደቡብ ጣሊያን የወደብ ከተማ ወደ ሆነው ላምፔዱስን ያደረጉት የመጀመሪያ የአገር ውስጥ ሐዋርያዊ ጉብኝት ሰባተኛ ዓመት ሐምሌ 1/2012 ዓ. ም. በጸሎት የሚታወስ መሆኑ ታውቋል። ቅዱስነታቸው ይህን ቀን የሚያከብሩት በቫቲካን በሚገኘው ቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት በሚያሳርጉ የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ ሥርዓት መሆኑ ታውቋል። የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግላጫ ክፍል እንዳስታወቀው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ረቡዕ ሐምሌ 1/2012 ዓ. ም. የሚመሩትን የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት የሚካፈሉት በቅድስት መንበር የስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ጳጳሳዊ መምሪያ ክፍል አስተባባሪዎች መሆናቸው ታውቋል።

የቫቲካን ዜና፤

በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በመስዋዕተ ቅዳሴው ጸሎት ላይ በቁጥር የተወሰኑ የምዕመና የሚካፈሉ መሆኑ ታውቋል። ከሰባት ዓመት በፊት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወደ ደቡብ ጣሊያን የወደብ ከተማ ላምፔዱሳ ያደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ዋና ዓላማ ወደ አውሮፓ ለመድረስ ብለው የሜዲቴራኒያን ባሕር ሲያቋርጡ ሕይወታቸውን ያጡ በብዙ ሺህዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችን ለማስታወስ መሆኑ ይታወሳል። የደቡብ ጣሊያን ከተማ ላምፔዱሳ፣ በጣሊያን በኩል ወደ አውሮፓ የሚጓዙት ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች መጀመሪያ የሚረግጧት ከተማ መሆኗ ይታወቃል። ይህች የወደብ ከተማ በሽህዎች ለሚቆጠሩት ስደተኞች የተስፋ መንገድ ከመሆን ይልቅ እጅግ አደገኛ የሆነ የሜዲቴራኒያን ባሕር ሲጓዙ በድንገተኛ አደጋ፣ በረሃብ እና በውሃ ጥም ሕይወታቸውን ያጡት በርካታ እናቶች፣ ሕጻናት እና ወጣቶች የሚታወሱባት ከተማ መሆኗ ታውቋል።

የ2019 ዓ. ም. መስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ተካሂዶ ነበር፤

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወደ ደቡብ ጣሊያን የወደብ ከተማ ላምፔዱስን ያደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ስድስተኛ ዓመት መታሰቢያ መስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ መካሄዱ ሲታወስ፣ በዚህ መስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሥነ ሥርዓት ላይ ስደተኞችን፣ ጥገኝነት ጠያቂዎችን እና የስደተኞችን ነፍስ አድን ሠራተኞችን ጨምሮ በቁጥር ሁለት መቶ ሃምሳ ምዕመናን መገኘታቸው ይታወሳል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ከሰባት ዓመት በፊት ለመጀመሪያ ጊዜ ከቫቲካን ወጥተው ወደ ደቡብ ጣሊያን የወደብ ከተማ ላምፔዱስ ያደረጉት ሐዋርያዊ ጉዞ፣ ዓለም ችላ ያለውን የስደተኞች የስቃይ ድምጽ ለማሰማት መሆኑ ይታወሳል። ቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ ስልጣን ከተቀበሉ በኋላ ከቫቲካን ክልል ለመጀመሪያ ጊዜ በመውጣት ያደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት በእርግጥም የተረሱትን፣ ከማኅበረሰቡ የተገለሉትን እና በልዩ ልዩ ማኅበራዊ ችግሮች ወስጥ ሆነው የመከራ ሕይወት ለሚኖሩት ያላቸውን ርህራሄ የገለጹበት ሐዋርያዊ ጉብኝት መሆኑ ይታወሳል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከቫቲካን ኒውስ ባልደረባ አቶ አንድሬያ ቶርኔሊ ጋር ያደረጉትን ቃለ መጠይቅ ይዞ በወጣው “ኢል ቪያጆ” ወይም “ጉዞ” በተሰኘ መጽሐፍ ላይ፣ በሜዲቴራኒያን ባሕር ላይ ጉዞ ሕይወታቸውን ያጡ የበርካታ ስደተኞች፣ ሕጻናት፣ ሴቶች እና እስከ ዛሬ ድረስ የሚሞቱ ሰዎች ሕይወት ቅዱስነታቸውን እጅግ እንዳሳዘናቸው መናገራቸው ይታወሳል።

ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን ካደረጉ ከሦስት ወራት በኋላ ሌላ አሳዛኝ አደጋ መከሰቱ፣

ወደ ደቡብ ጣሊያን የወደብ ከተማ ሐዋርያዊ ጉብኝት እንዲያደርጉ ግብዣ ባይደረግላቸውም በግል ፍላጎት ተነሳስተው መሄዳቸውን የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ወደ ሥፍራው ደርሰው አበባ ሲያስቀምጡ ከአደጋው የተረፉ ስደተኞች፣ ከአካባቢው ምዕመና፣ ከብጹዓን ጳጳሳት፣ ከካህናት፣ ከመንፈሳዊ ማኅበራት ተወካዮችን እና ከስደተኞች ነፍስ አድን ሠራተኞችን ጋር ለመገናኘት መቻላቸውን ገልጸዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከሰባት ዓመት በፊት ወደ ሥፍራው ያደረጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት በማስታወስ ሲናገሩ፣ በጉብኝታቸው ዕለት ለአሥር ሺህ ምዕመናን የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ማሳረጋቸውን አስታውሰው፣ ምዕመናኑ የተስተናገዱበት አደባባይ በርካታ ስደተኞች ሕይወታቸውን ባጡባቸው ጀልባዎች ስባሪ መገንባቱን አስታውሰዋል። ወደ ላምፔዱሳ ወደብ ያደረጉት ሐዋርያዊ ጉዞ ሕሊናችንን በመውቀስ በዚያ አካባቢ በስደተኞች ላይ የተከሰተው አደጋ እንዳይደገም የሚያደርግ መሆኑንም አስታውሰዋል። የስደተኞች ባሕር ላይ ሞት እስከ ዛሬ የቀጠለ መሆኑ ሲታወቅ፣ ከሰባት ዓመት በፊት ቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን ፈጽመው ከተመለሱ ከሦስት ወራት በኋላ፣ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር 2013 ዓ. ም. የጣሊያን የወደብ ከተማ በሆነች ላምፔዱሳ አቅራቢያ 366 ስደተኞች ሕይወት የጠፋበት የባሕር ላይ አደጋ መከሰቱ ይታወሳል። በቀጣዩ ዓመት ከአደጋው የተረፉ ስደተኞች ወደ ቫቲካን መጥተው ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር መገናኘታቸው ይታወሳል።

ግድ የለሽነት ባጠቃው የግሎባላይዜሽን ሥርዓት ወድቀናል፥

በሜዲቴራኒያን ባሕር ላይ ስደተኞችን የሚደረስ ስቃይ በሚታወስባት የላምፔዱሳ ወደብ የተገኙት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በንግግራቸው “ግድ የለሽነት ስሜት ባጠቃው የግሎባላይዜሽን ሥርዓት ውስጥ ወድቀናል፣ የሌሎችን ስቃይ በዝምታ መመልከትን ለምደናል፣ የርህራሄ ልብም ተወስዶብናል” በማለት መናገራቸው ይታወሳል። ስለዚህ ወደ እግዚአብሔር ዘንድ የምናቀርበው ጸሎት “በወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ላይ ላሳየነው የግድ የለሽነት ተግባር፣ የሌላውን ስቃይ ሳይሆን የራሳችንን ምቾት ብቻ በመመልከታችን፣ የራስ ወዳድነት ባሕል እንዲስፋፋ አስተዋጽዖ ያደረጉት በሙሉ ይቅርታን የሚለምኑበት እንዲሆን ያስፈልጋል” በማለት ቅዱስነታቸው አሳስበው፣ ዓለማችን በስደት ሕይወት የሚሰቃዩትን ተቀብሎ የተሻለ ሕይወት እንዲኖራቸው ለማድረግ የሚያስችል ድፍረት እንዲያገኝ መጸለይ ያስፈልጋል በማለት አሳስበዋል።

07 July 2020, 08:18