ፈልግ

(ከማኅደር የተወሰደ) (ከማኅደር የተወሰደ) 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ ማኅበራዊ ሚዲያ አንድነት በማሳደግ ለጋራ ጥቅም እንዲቆም አሳሰቡ።

ዘረኝነት እና ልዩነት በሚታይበት ዘመናችን ማኅበራዊ ሚዲያ በሕዝቦች መካከል ኅብረትን ማሳደግ እንዳለበት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አሳሰቡ። ቅዱስነታቸው ይህን ያሳሰቡት ከሰኔ 23-25/2012 ዓ. ም. ዓመታዊ ዓመታዊ ስብሰባቸውን ላካሄዱት የሰሜን አሜሪካ እና የካናዳ ካቶሊክ ሚዲያ ባለሞያዎች በላኩት መልዕክታቸው መሆኑ ታውቋል።

የቫቲካን ዜና፤

በሕዝቦች መካከል መከፋፈል እና ልዩነት በሚታይበት ዘመናችን፣ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ሕዝብን በማቀራረብ የራሳቸውን ሚና እንዲጫወቱ፣ በማኅበረሰብ መካከል ግንኙነት እንዲኖር የሚያደርግ ድልድይ በመገንባት በወንድማማችንት ፍቅር አብረው በመኖር ሕይወትን ከጉዳት መከላከል እንደሚያስፈልግ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አሳስበዋል። ቅዱስነታቸው ይህን ጠንካራ መልዕክታቸውን የላኩት፣ ከሰኔ 23-25/2012 ዓ. ም. የካቶሊክ ሚዲያ ዓመታዊ ኮንፈረንስ ለሚያካሂዱ የሰሜን አሜሪካ እና የካናዳ ካቶሊክ ጋዜጠኞች ማኅበራት መሆኑ ታውቋል። የሁለቱ አገራት ካቶሊካዊ ሚዲያ ማኅበራት በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የዘንድሮ ስብሰባቸውን በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካይነት በየአገራቸው ሆነው ማከሄዳቸው ታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዓለም አቀፍ ማኅበራዊ መገናኛ ቀንን ምክንያት በማድረግ ባለፈው ዓመት ባስተላለፉት መልዕክት፣ በሕዝቦች መካከል አንድነትን በመፍጠር፣ በማቀራረብ፣ አስፈላጊ መረጃዎችን በማዳረስ እና ልብን እና አዕምሮን ለእውነት በመክፈት ረገድ የማኅበራዊ መገናኛዎች ሚና ከፍተኛ እንደሆነ መናገራቸው ይታወሳል።

በሰሜን አሜሪካ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የመጀመሪያዎቹ ጋዜጦች መታተም የጀመሩት እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር 1822 ዓ. ም. በቻርልስተን ሀገረ ስብከት ውስጥ በብጹዕ አቡነ ጆን ኢንግላንድ መሆኑ ሲታወስ ቀጥሎም ሌሎች በርካታ ጋዜጦች እና መጽሔቶች በቤተክርስቲያኒቱ ስም መታተም መጀመራቸውን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በዘመናችንም ሕዝብን ለማቀራረብ፣ እውነተኛ መረጃን ወደ ሕዝቡ ለማድረስ የማኅበራዊ መገናኛዎች መኖር እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ አስረድተዋል።

ክፉን እና ደጉን እንዲለዩ ማገዝ ያስፈልጋል፣

እንደ ሰሜን አሜሪካ መሪ ቃል “በልዩነት መካከል አንድነትን ማሳደግ” ማለት ለጋራ ጥቅም የሚውሉ አገልግሎቶችን ማበርከት መሆኑን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ግጭቶች እና ልዩነቶች እያደጉ በመጡበት ዘመናችን በሕዝቦች መካከል አንድነት እና ወንድማማችነትን ማሳደግ አስፈላጊ መሆኑን በማኅበራዊ ሚዲያ ዘርፍ ለተሰማሩት የብዙሃን መገናኛ ባለሞያዎች አስረድተዋል። ልዩነትን የሚያጠቡ፣ በሰዎች መካከል የእርስ በእርስ ግንኙነቶችን የሚያሳድጉ፣ ውይይቶች እንዲካሄድ በማድረግ እውነተኛ ግንኙነቶች እንዲፈጠሩ የሚያደርጉ የብዝሃን መገናኛዎች እንደሚያስፈልጉ ቅዱስነታቸው አሳስበዋል። ማኅበራዊ ሚዲያዎች ከዚህም በተጨማሪ ወጣቶች ክፉን እና ደጉን ለይተው እንዲያውቁ፣ የመረጃዎች ትክክለኛነት ለይተው ፍርድን መስጠት እንዲችሉ ማገዝ እንደሚገባ አሳስበዋል። ማኅበራዊ ፍትህን የሚያረጋግጡ እና ለጋራ መኖሪያ ምድራችን ደኅንነት የቆመ ማኅበራዊ ሚዲያ መኖር አስፈላጊ መሆኑን የገለጹት ቅዱስነታቸው፣ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ከዚህ ባሻገር የሕዝቦችን አንድነት እና ሰላም ለሚያናጉ ዓላማዎች ተገዥ እንዳይሆኑ ማኅበረሰቡ ነቅቶ መጠበቅ እንዳለበት ቅዱስነታቸው አሳስበዋል።

የአንድነት ምልክት ናችሁ፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለሰሜን አሜሪካ እና ለካናዳ ካቶሊካዊ ሚዲያ ማኅበራት በላኩት መልዕክታቸው፣ የቤተክስቲያን ሚዲያዎች በአቅም እና በአወቃቀር ከትላልቅ የሚዲያ ተቋማት ጋር የሚወዳደሩ ባይሆንም በቤተክርስቲያን ትልቅ ሥፍራ እንዳላቸው ገልጸው በቤተክርስቲያን ውስጥ ሁሉም የአንድ ቤተሰብ አባላት መሆናቸውን አስረድተዋል።

ለእያንዳንዱ ማኅበራዊ መገናኛ ግቡ እግዚአብሔር ነው፣

የማኅበራዊ መገናኛ ሥራ የሞያ ብቃት ብቻ እንዳልሆነ የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ የማኅበራዊ መገናኛዎች ብቃት የሚለካው በሚያቀርቡት እውነት መሆኑን ገልጸው ለእያንዳንዱ ማኅበራዊ ግንኙነት መነሻ እና ግቡ እግዚአብሔር መሆኑን አስረድተው፣ የምስጢረ ስላሴ ባሕርይ ያለውን ይህን መለኮታዊ ሃብት በመቀበል በኅብረት እውነትን ማገልገል እንደሚያስፈልግ አደራ ብለዋል።

ክርስቲያናዊ መገናኛዎች ለእውነት እና ለሰብዓዊ ክብር ሊቆሙ ይገባል፣

በርትቶ በመሥራት ዘረኝነትን፣ ኢፍትሃዊነትን እና ክፍፍልን ማሸነፍ እንደሚቻል የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ሰዎች የጊዜውን ሁኔታ ማገናዘብ እንዲችሉ መርዳት እንደሚያስፈልግ አሳስበው፣ ክርስቲያናዊ መገናኛዎች ብዙን ጊዜ ለክስተቶች ግልጽ እና የማያሻማ ትርጉም ለማይሰጥ ዓለማችን፣ ሰብዓዊ ክብርን የሚያበረታቱ እውነተኛ መልዕክቶችን ማድረስ እንደሚገባ ጠይቀው፣ በሕዝቦች መካከል አመጽ እና ልዩነት ተስፋፍቶ በሚታይበት ዓለማችን የችግረኞችን ጥያቄ በመመለስ፣ ለድሆች ድምጽ በመሆን ምህረትን እና ርህራሄን ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

በኅብረት በመቆም አንድነትን ማሳደግ፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ዓመታዊ ስብሰባቸውን ለሚያካሂዱት የሰሜን አሜሪካ እና የካናዳ ካቶሊክ ሚዲያ ባለሞያዎች በላኩት መልዕክታቸው የእምነት አንድነታቸውን በማሳደግ እና ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ያላቸውን ታማኝነት በመጠበቅ ወንጌላዊ እውነትነት ለሚጎድለው ባሕል እውነትን እንዲመሰክሩ አሳስበዋል። ቅዱስነታቸው መልዕክታቸውን ባጠቃለሉበት ጊዜ እንደገለጹት፣ ሰኔ 22/2012 ዓ. ም. የተከበረውን የቅዱሳን ጴጥሮስ እና ጳውሎስ ክብረ በዓል አስታውሰው የሁለቱም አገራት ካቶሊካዊ ሚዲያ ባለሞያዎች ለዓለም ሰላም በጋራ መእንዲጸልዩ አሳስበዋል።         

02 July 2020, 07:51