ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ለቤተሰብ ፍቅር፣ ክብር እና አስፈላጊው መመሪያ ሊሰጠው ይገባል ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለሐምሌ ወር እንዲሆን ብለው ባቀረቡት የጸሎት ሃሳብ፣ በተለያዩ ማኅበራዊ ችግሮች ውስጥ ለሚገኝ የቤተሰብ ተቋም ፍቅር፣ አክብሮት እና አስፈላጊው መመሪያ ሊሰጠው ይገባል ብለዋል። ቅዱስነታቸው የሐምሌ ወር የጸሎት ሃሳባቸውን መሠረት በማድረግ ምዕመናን በጸሎት እንዲተባበሯቸው በማለት በዓለም አቀፍ የጸሎት ጥሪ አስተባባሪ ጽ/ቤት በኩል ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

የቫቲካን ዜና፤

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችክሶስ ባስተላለፉት የቪዲዮ መልዕክታቸው፣ በተለያዩ ማኅበራዊ ችግሮች ውስጥ ለሚገኙ ቤተሰቦች መንግሥታት አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ፍቅርን እና አክብሮትን በማሳየት፣ ችግራቸውን ሊቀንስ የሚችሉ መመሪያዎችን በመስጠት ቤተሰቦችን ሊያበረታቱ ይገባል ብለዋል።

“የዘመናችን የቤተሰቦች ተጨባጭ ሁኔታ ካለፉት ጊዜያት የተለየ ነው” ያሉት ቅዱስነታቸው፣ በዘመናችን ቤተሰቦች መካከል የሚታይ የሥራ ጫና እና የጊዜ እጥረት ለቤተሰባዊ ግንኙነት መዳከም ምክንያት መሆኑን አስረድተው፣ በተጨማሪም የዲጂታል ማኅበራዊ መገናኛ መንገዶች በርካታ ቤተሰቦችን በብቸኝነት ስሜት ውስጥ እንዲገቡ ማድረጉን አስረድተዋል። ማኅበራዊ ቀውስ ሲያጋጥም፣ በተለይም የኮሮርና ቫይረስ ወረርሽኝ የቤተሰብን ማኅበራዊ እና ኤኮኖሚያዊ ሕይወትን በግልጽ እየጎዳ ባለበት ባሁኑ ጊዜ፣ ከሥራ በመገለል እና ቤተሰብን ማስተዳደር ካለመቻል የተነሳ ግለ ሰቦችም ሆነ መላው ማኅበረሰብ የሚገኝበትን አስቸጋሪ ሕይወት በመረዳት፣ ቤተሰቦች ከችግራቸው እንዲወጡ የሚያስችሉ ፖሊሲዎችን በማዘጋጀት መንግሥታት ጥረት እንዲያደርጉ ቅዱስነታቸው በመልዕክታቸውን አደራ ብለዋል።

ቤተሰቦችን ያጋጠሟቸው ማኅበራዊ ችግሮች፣ አስቀድሞም ቢሆን ካጋጠሙት በርካታ አደጋዎች መካከል አንዱ መሆኑን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ የቤተሰብን ዕለታዊ ሕይወት በማስመልከት እንደተናገሩት፥ “ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር የመሆን አስፈላጊነት ስለሚዘነጉ፣ ቤተሰብ በመካከላቸው የሚፈጠሩ ችግሮችን ተገንዝበው መፍትሄን እንዲያገኙ ቤተክርስቲያን በቤተሰቦች ጎን በመሆን ማበረታታት ያስፈልጋል” በማለት አሳስበዋል።

የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ዓለም አቀፍ የጸሎት ጥሪ እና የቅዱስ ቁርባን ወጣቶች እንቅስቃሴ ጽ/ቤት አስተባባሪ የሆኑት ክቡር አባ ፍሬደሪክ ፎርኖስ ባቀረቡት አስተያየት፣ በብዙ የዓለማችን ክፍሎች የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ያስከተለው ቀውስ በገሃድ የሚታይ መሆኑን አስታውሰዋል። ዕርዳታን የሚሹ በርካታ ቤተሰቦች የወደ ፊት ዕጣ ፈንታቸው ምን ሊሆን እንደሚችል እርግጠኛ አለ መሆናቸውን እና ወደ ሥራ ገበታቸው ስለ መመለሳቸው እርግጠኞች አለመሆናቸውን ገልጸዋል። ማኅበራዊ ችግሮች እና በሽታ እያሰቃየው በሚገኝ ዓለማችን ቤተሰብ ያለ ደጋፊ ሊቀር አይገባውም ብለው፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የቤተሰብን አስፈላጊነት በማስመልከት፥ “ቤተሰብ የኅብረተሰብ መሠረት እና ቀጣይነት ያለውን ሁሉ አቀፍ ማኅበራዊ ዕድገትን የሚያረጋገጥ ቋሚ ተቋም ነው” ማለታቸውን አስታውሰዋል። በማከልም ለቤተሰብ የሚሰጥ እንክብካቤ ግላዊ ሳይሆን ማኅበራዊ ሃላፊነት ያለው በመሆኑ መንግሥታት፣ ቤተሰቦች ከችግሮቻቸው እንዲወጡ ፖሊሲዎችን በማርቀቅ ሊያግዟቸው፣ ሊያበረታቷቸው፣ ሊወዷቸው እና መመሪያን ሊሰጧቸው ያስፈልጋል ማለታቸውን አስታውሰዋል። ይህን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የጸሎት ሃሳብ መሠረት በማድረግ የምናቀርበው ጸሎት በችግር ውስጥ የሚገኙ ቤተሰቦችን ብቻ ለማገዝ ሳይሆን ለቤተሰብ ዕድገት የበኩላቸውን ጥረት በማድረግ ላይ የሚገኙ ማኅበራትንም የሚረዳ መሆኑን ክቡር አባ ፍሬደሪክ ፎርኖስ አስረድተው፣ እያንዳንዳችን የጸሎትን ጥቅም በመገንዘብ በሚኖረን ነጻ ጊዜ በችግር ውስጥ የሚገኙ ቤተሰቦችን በጸሎታችን ለማገዝ እንተባበር በማለት የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ዓለም አቀፍ የጸሎት ጥሪ አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት መሪ የሆኑት ክቡር አባ ፍሬደሪክ ፎርኖስ አሳስበዋል።  

10 July 2020, 12:53