ፈልግ

ምድራችንን በመንከባከብ ጥራት ያለውን የግብርና ምርት ማሳደግ፤ ምድራችንን በመንከባከብ ጥራት ያለውን የግብርና ምርት ማሳደግ፤ 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ ታዳሽ ኃይልን በመጠቀም ምድራችንን ከጥፋት ማዳን ይገባል አሉ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ይህን ያሳሰቡት፣ የአየር ለውጥን ለማሻሻል ጥረት በማድረግ ላይ በሚገኙት ማኅበራት ዘንድ ቅዳሜ ሰኔ 27/2012 ዓ. ም. በተከበረው ዓለም አቀፍ የአየር ለውጥ ቀን መሆኑ ታውቋል። ቅዱስነታቸው “ውዳሴ ላንተ ይሁን” የሚለውን ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸውን መሠረት በማድረግ ባስተላለፉት የቲውተር መገናኛ መልዕክታችው፣ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ማኅበራት በዓለማችን የሚታየውን የአየር ለውጥ ለማስተካከል በማለት የሚያደርጉት ጥረት ለማኅበረሰባቸው እና ለሚኖሩበት ምድራቸው ያላቸውን ከፍተኛ ፍቅር የሚገልጹበት መሆኑን አስታውቀዋል።

የቫቲካን ዜና፤

በየዓመቱ የሚከበረው ዓለም አቀፍ የማኅበራት ቀን ለ96 ዓመታት ሲከበር የቆየ ሲሆን፣ የሚከበረውም በሐምሌ ወር መጀመሪያ ቅዳሜ መሆኑ ይታወቃል። ቅዱስነታቸው በዕለቱ ባስተላለፉት መልዕክታቸው እንደገለጹት በዓለማችን የተከሰተውን የአየር ለውጥ ለማስተካከል ጥረት የሚያደርጉ ማኅበራት ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን አስታውሰው፣ የአየር ለውጥን ለማስተካከል ከሚረዱ መንገዶች አንዱ በአካባቢያችን የሚገኙ ታዳሽ ኃይልን በመጠቀም መሆኑን አስረድተው ማኅበራቱ ጥረታቸውን በማጠናከር ከፍተኛ ለውጥን ማምጣት የሚችሉ መሆኑን ገልጸዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም እነዚህ ማኅበራዊ ድርጅቶች ለማኅበራዊ ሕይወት እና ለጋራ መኖሪያ ምድራችን ላሳዩት ፍቅር ምስጋናቨውን አቅርበውላቸዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከዚህ በፊት ባስተላለፉት መልዕክታቸው፣ የብቸኝነትን እና የራስ ወዳድነትን መንፈስ በማስወገድ ለጋራ ጥቅም የቆመ ማኅበረሰብን ማደራጀት እንደሚያስፈልግ ማሳሰባቸው ይታወሳል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር መጋቢት 16/2019 ዓ. ም. ለጣሊያን የኅብረት ሥራ ማኅበራት ፌደሬሽን ባስተላለፉት መልዕክት፣ ማኅበራቱ የበጎ አድራጎት ሥራን የሚያከናውኑ፣ በገንዘብ ወይም በሃብት ለሚመካ ማኅበረሰብ ዕድል መስጠት እንደማይገባ ማሳሰባቸው ይታወሳል። ቅዱስነታቸው በማከልም በገንዘብ የሚመካ ማኅበረሰብ በሕዝቦች መካከል ተስፋን ወደሚያስቆርጥ ኢሰብዓዊ እና ኢፍትሃዊ ሥርዓት የሚመራ መሆኑን አስረድተዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም የሕዝባዊ ማኅበራት መኖር ወይም መበራከት ኢፍትሃዊ የኤኮኖሚ ሥርዓትን እና ማኅበራዊ ኢፍትሃዊነትን ለማዳከም ዋና መሣሪያ መሆኑን አስረድተዋል። የማግለል፣ የራስ ወዳድነት እና ብቻዬን ልደግ የሚል አስተሳሰብ ማዳከም የሚቻለው ሳያማርሩ በኅብረት ጠንክሮ በመሥራት ነው ያሉት ቅዱስነታቸው ይህን ተግባራዊ ማድረግ የሚቻለው በራሱ የሚተማመን፣ ልዩ የሥራ ባሕልን በመከተል፣ ልዩ የምርት ውጤቶችን ማቅረብ የሚችል፣ በኅብረተሰብ መካከል መልካም ምሳሌነቱን በተግባር እየገለጸ የሚኖር  ማኅበርን በመመስረት መሆኑን አስረድተዋል። የኅብረት ሥራ ማኅበርን ለመመስረት የሚነሳ ሁሉ ከእነዚህ ከላይ ከተጠቀሱት ባሕሪያት መካከል ጥቂቱም ቢሆን የሚታይበት ሊሆን ይገባል ብለዋል።

የቸርነት ተግባር ያለበት ማኅበር፣

“ውዳሴ ላንተ ይሁን” በሚለው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸው በቁጥር 179 ላይ እንደ ተገለጸው፣ ተፈጥሮን ለመንከባከብ እና ጥበቃን ለማድረግ የተቋቋሙ ማኅበራት መኖራቸውን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በእነዚህ መንግሥታዊ ባልሆኑ ማኅበራት አማካይነት መንግሥት ተፈጥሮን ለመንከባከብ እና ጥበቃን ለማድረግ የሚያወጣቸውን ደንቦች ከጊዜ ወደ ጊዜ በማሳደግ ተግባራዊነቱንም እንዲከታተል ማስገደድ ይቻላል ብለው፣ ዜጎች ብሔራዊ እና ክልላዊ የፖለቲካ ሃይላትን መቆጣጠር ካልቻሉ አካባቢያዊ ጥበቃንም በአግባቡ ተግባራዊ ማድረግ አይቻልም ብለዋል።

ይህ ቀላል ምሳሌ፣ የዓለም ሃያላን መንግሥታት የአካባቢ ጥበቃ እና እንክብካቤን ተግባራዊ ማድረግ ባይችል እና ሃላፊነቱን በትክክ መወጣት ሳይችል ሲቀር፣ በየአገራቱ የተቋቋሙ የኅብረት ሥራ ማኅበራት በበኩላቸው ትልቅ ለውጥ ማሳየት የሚችሉ መሆናቸውን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አስረድተዋል። ከፍተኛ ሃላፊነት ሊኖር የሚችለው፣ በርካታ የቸርነት ተግባራትን ሊያከናወኑ የሚችሉት፣ ማንንም ወደ ጎን የማያደርግ የጋራ ሕይወት ሊመሠረት የሚቻለው፣ ለጋራ መኖሪያ ምድራችንም ጥልቅ ፍቅር ሊኖር የሚችለው እና ከውድመት የተረፈች ምድራችንን ለመጭው ትውልድ ማስረከብ የሚቻለው በእነዚህ ማኅበራት ብርቱ ጥረት እንደሆነ ቅዱስነታቸው አስረድተዋል።     

06 July 2020, 12:28