ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “ነፃ ሊያወጣን የሚችለው የእግዚአብሔር ቃል ብቻ ነው” አሉ!
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በሐምሌ 05/2012 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ እርሳቸው ዘወትር እሁድ በእለቱ ቅዱስ ወንጌል ላይ ተንተርሰው የሚያደርጉትን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ለመከታተል በስፍራው ለተገኙ ምዕመናን ቅዱስነታቸው በወቅቱ ያደርጉት አስተንትኖ “አንድ ገበሬ ዘር ሊዘራ ወጣ። ሲዘራም ሳለ፣ አንዳንዱ ዘር መንገድ ዳር ወደቀ፤ ወፎችም መጥተው ለቅመው በሉት። አንዳንዱ ዘር ዐፈሩ ስስ በሆነ፣ ድንጋያማ መሬት ላይ ወደቀ፤ ዐፈሩ ስስ ስለ ሆነም ፈጥኖ በቀለ። ነገር ግን ፀሓይ ሲመታው ጠወለገ፤ ሥር ባለ መስደዱም ደረቀ። አንዳንዱም ዘር በእሾኽ መካከል ወደቀ፤ እሾኹም አደገና ቡቃያውን አንቆ አስቀረው፤ ሌላው ዘር ደግሞ በጥሩ መሬት ላይ ወደቀ፤ ፍሬም አፈራ፤ አንዱ መቶ፣ አንዱ ሥልሳ፣ አንዱም ሠላሳ ፍሬ ሰጠ። ሰሚ ጆሮ ያለው ይስማ!” (ማቴ 13፡1-23) በተሰኘው ኢየሱስ በተናገረው የዘሪው ምሳሌ ላይ መሰረቱን ያደረገ አስተንትኖ እንደ ነበረ የተገለጸ ሲሆን “ነፃ ሊያወጣን የሚችለው የእግዚአብሔር ቃል ብቻ ነው” ማለታቸው ተገልጿል።
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን
ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በእለቱ ያደረጉትን አስተንትኖ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል፣ ተከታተሉን።
የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳቹ!
በዛሬው እለተ ሰንበት የተነበበልን ቅዱስ ወንጌል (ማቴ 13፡1-23) ኢየሱስ እኛ ሁላችን በደንብ የምናውቀውን ምሳሌ ማለትም የተለያየ የአፈር ዓይንት ያላቸው ስፍራዎች ላይ የወደቁትን ዘሮች የሚገልጸውን የዘሪውን ምሳሌ በስፍራው ለተሰበሰቡ እጅግ ብዙ ሰዎች ሲናገር እንሰማለን።፡ በዘሮቹ የተወከለው የእግዚአብሔር ቃል ሲሆን ይህ የእግዚአብሔር ቃል ደግሞ ረቂቅ ቃል አይደለም ፣ ነገር ግን በማርያም ማህፀን ውስጥ የተጸነሰ ሥጋ ለብሶ ሰው ሆኖ የተወለደው የአብ ቃል ክርስቶስ ራሱ ነው። ስለዚህ የእግዚአብሔርን ቃል መቀበል ማለት የክርስቶስን ስብዕና መቀበል ክርስቶስ ራሱን መቀበል ማለት ነው።
የእግዚአብሔርን ቃል የምንቀበልበት የተለያዩ መንገዶች አሉ። በአፋጣኝ ሁኔታ በመንገድ ላይ የተዘራውን እና ወፎች ወዲያው መጥተው ዘሩን ከመንገድ ላይ ወስደው የተመገቡትን ዓይነት ሰው ልንሆን እንችላለን። ይህ ሊሆን የሚችለው ደግሞ ትኩረታችንን ሊስብ በሚችለው በተደቀኑብን የዘመናችን ትልቅ አደጋ የተነሳ ነው። በብዙ ወሬዎች የተነሳ በደረሰባቸው በደል ተበሳጭተው ፣ በብዙ ርዕዮተ-ዓለም ፣ በቤት ውስጥም ሆነ ከቤት ውጭ ትኩረትን ሊከፋፍሉ በሚችሉ አጋጣሚዎች የተነሳ የጸጥታ ፣ የማስታወስ ፣ ከጌታ ጋር የመነጋገር ፍላጎቶቻችንን ልናጣ እንችላለን፣ ይህም እምነት እንድናጣ እና የእግዚአብሔርን ቃል እንዳንቀበል ሊያደርገን ይችላል። እኛ ሁሉንም ነገር እየተመለከትን ፣ በዓለም ነገሮች ትኩረታችን እየተወሰደ እንረበሻለን።
ሌላ አማራጭ: - አነስተኛ የአፈር ይዘት እንዳለው ድንጋያማ መሬት በመሆን የእግዚአብሔርን ቃል መቀበል እንችላለን። እዚያም ዘሩ ቀደም ብሎ ይበቅላል፣ ግን ወዲያውም ይደርቃል ፣ ምክንያቱም መሬቱ ድንጋያማ ስለሆነ ሥሩን ወደ ጥልቁ መላክ ስለማይችል ነው። የእግዚአብሔር ቃል በቅንዓት መንፈስ ወዲያውኑ የሚቀበሉ ሰዎች ምስል ነው ፣ ሆኖም ቃሉ በልብ ውስጥ ጠልቆ ስላልገባ ትክክለኛውን የእግዚአብሔር ቃል አይመስልም። እናም በቅድሚያ አንድ ችግር ወይም መከራ ሲያጋጥመን፣ የህይወት መረበሽ ሲያጋጥመን የዚህ ዓይነቱ እመንት በጣም ጠንካራ ባለመሆኑ የተነሳ በድናጋያማ መሬት ላይ እንደ ተዘራው ዘር ወዲያውኑ ይድከምና ይደርቃል።
እንደገና እኛ በምሳሌው ውስጥ ኢየሱስ የተናገረውን ሦስተኛ ዕድል በእሾሃማ ቁጥቋጦዎች በሚበቅሉበት ስፍራ እንደ ወደቀው ዓይነት ዘር የእግዚአብሔርን ቃል እንቀበላለን። እሾህ እኛን ብዙ ጊዜ የሚያሳስቱንን ሀብት፣ ስኬት ፣ ስለዓለም ጉዳዮች ማሰብ የመሳሰሉትን ይወክላል። እዚያም ቃሉ ትንሽ ያድጋል ፣ ነገር ግን እሾሁ አንቆ ይይዘዋል፣ ጠንካራ ስላልሆነ ይሞታል ወይም ፍሬ አያፈራም።
በመጨረሻም - አራተኛው ዕድል - እኛ የእግዚአብሔርን ቃል እንደ እንደ ጥሩ መሬት አድርገን እንቀበላለን። እዚህ እና እዚህ ጋር ብቻ ነው ዘሩ ሥሩን ወደ ጥልቁ መሬት መዘርጋት የሚችለው፣ ከዚያም ፍሬ ያፈራል። በዚህ ለም መሬት ላይ የወደቀው ዘር ቃሉን የሚሰሙ ፣ የሚቀበሉትን ፣ በልባቸው ውስጥ የሚጠብቁትን እና በዕለት ተዕለት ኑሮው ውስጥ ተግባራዊ የሚያደርጉትን ሰዎች ይወክላል ፡፡
ይህ የዘሪው ምሳሌ በተወሰነ ደረጃ የሁሉም ምሳሌዎች “እናት” ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፣ ምክንያቱም ቃሉን ማዳመጥ እንደ ሚገባን ስለሚነግረን ነው። ይህ ምሳሌ ፍሬያማ እና ውጤታማ ዘር መሆን እንደ ሚገባን ያስታውሰናል ። ያለምንም ብክነት እና በጥንቃቄ እግዚአብሔር በልግስና በሁሉም ስፍራ ዘሩን ይበትነዋል። የእግዚአብሔር ልብ እንዲሁ ነው! እያንዳንዳችን የቃሉ ዘር የሚወድቅበት መሬት ነን፣ ማንም አይገለልም። ቃሉ ለሁላችን ተሰጥቷል። “ምን ዓይነት መሬት ነኝ?” ብለን ራሳችንን መጠየቅ እንችላለን። እኔ በመንገድ፣ በድንጋያማ፣ በቁጥቋጦ ስር የወደቀውን ዘር ነው የምመስለው? ከፈለግን ግን በእግዚአብሔር ጸጋ መልካም የሆንን ፣ የቃሉ ዘርን ለማሳደግ በጥሩ ሁኔታ የታረሰ በጥንቃቄ ዘሩን የምናበቅል እና ቃሉን የምናበቅል መልካም መሬት ለመሆን እንችላለን። ቀድሞውኑ በልባችን ውስጥ ይገኛል፣ ነገር ግን ፍሬ እንዲያፈራ ማድረጉ የእኛ ተግባር ነው፣ ይህም ለዘሩ በምናደርገው ጥንቃቄ እና አቀባበል ላይ መሰረቱን ያደረገ ነው። ብዙውን ጊዜ አንድ ሰው በብዙ ፍላጎቶች ፣ በብዙ ጥሪዎች በመዘናጋት ነፃ በሚያደርገን በጌታ ቃል እና በብዙ ድምጾች መካከል ያለውን ልዩነት ለመለየት እንቸገራለን። የእግዚአብሔርን ቃል በማዳመጥ እና ማንበብ ጠቃሚ የሆነው በዚሁ ምክንያት ነው። እኔ እንደገና ከዚህ ቀደም የመከርኩዋችሁን ምክር እንደ ገና ለመናገር እሻለሁ፣ አንዲት ትንሽዬ መጽሐፍ ቅዱስ፣ በኪስ ልትገባ የምትችል መጽሐፍ ቅዱስ ሁልጊዜ በምትሄዱበት ስፍራ ሁሉ ይዛችሁ እንድትጓዙ በድጋሚ እመክራችኋለሁ። እናም በእየለቱ ትንሽዬ የመጽሀፍ ቅዱስ ክፍል በማንበብ ከመጸሐፍ ቅዱስ ጋር ያላችሁን ልምድ አዳብሩ፣ እግዚአብሔር የሚሰጥህን ዘር ተረዳ እናም በየትኛው ምድር ላይ እንደምትቀበል አስብ።
እኛ ለራሳችን እና ለወንድሞቻችን መልካም ፍሬን ማፍራት እንድንችል እሾሃማ ወይም ድንጋያማ የሆንን መሬት ሳንሆን ዘሩ የሚወድቅበት እና ብዙ ፍሬ የሚፋራበት መልካም መሬት መሆን እንችል ዘንድ የመልካም እና ለም መሬት ተምሳሌት የሆነችሁ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በአማላጅነቷ እንድትረዳን ልንማጸናት ይገባል።