ፈልግ

የወንጌል ደስታ የወንጌል ደስታ  

የወንጌል ደስታ

የወንጌል ደስታ በሚል አርእስት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ እ.አ.አ በነሐሴ 24/2013 ዓ.ም በዛሬው ዓለም ወንጌልን ስለ መስበክ ለጳጳሳት፣ ለካህናት፣ ለደናግልና ለምእመናን ያስተላለፉት ሐዋርያዊ ምክር

1.     የወንጌል ደስታ ከክርስቶስ ጋር የሚገናኙ ሰዎችን ሁሉ ልብና ሕይወት ይሞላል፡፡ የእርሱን የደኅንነት ስጦታ የሚቀበሉ ከኃጢአት፣ ከሃዘን፣ ከውስጣዊ ባዶነትና ብቸኝነት ነጻ ናቸው፡፡ እነኚህ ሰዎች በክርስቶስ ደስታ ያለማቋረጥ ይታደሳሉ፣ ይወለዳሉ፡፡ ስለዚህ በዚህ ሐዋርያዊ ምክር መልእክቴ አማካይነት በዚህ ደስታ የተሟላ አዲስ የስብከተ ወንጌል ምዕራፍ እንዲከፍቱ ክርስቲያን ምእመናንን አደራ እላለሁ፤ ለመጪዎቹ ዓመታት የቤተ ክርስቲያን ጉዞም የሚያገለግል አዲስ መንገድ ለማሳየት እፈልጋለሁ፡፡

I.ሁሌም የሚጋሩት አዲስ የሆነ ደስታ

2.     በሸቀጦች የፍጆታ አምልኮ በተበከለው በዛሬው ዓለም የሚታየው ትልቁ አደጋ፣ ዘወትር በምኞት ከተሞላ ልብ የሚመነጭ ብቸኝነትና ጭንቀት፣ ብርቱ የሆነ ከንቱ ደስታ ፍለጋና የደነዘ ህሊና ነው፡፡ ውስጣዊ ሕይወታችን በራሱ ጥቅምና ፍላጎት ላይ ብቻ በሚጠመድበት ጊዜ ለሌሎች ምንም ክፍተት፣ ለድሆች ምንም ቦታ አይኖረውም፡፡ የእግዚአብሔር ድምፅ አይደመጥም፣ የእርሱ ፍቅር እና ሰላማዊ ደስታ አይሰማም፣ መልካም የማድረግ ምኞት ይደበዝዛል፡፡ ይህ አማንያንንም የሚያጋጥም ተጨባጭ አደጋ ነው፡፡ ብዙዎች የዚህ አደጋ ሰለባ ይሆናሉ፣ መጨረሻቸውም ቁጭት፣ ቁጣና ግድ የለሽነት ይሆናል፡፡ ይህ ክቡርና ስኬታማ ሕይወት የመኖር መንገድ አይደለም፡፡ ይህ እግዚአብሔር ለእኛ ካለው ፈቃድ ወይም ከሞት ከተነሣው ከክርስቶስ ሃሳብ ጋር የሚጣረስ ነው፡፡

3.  ስለዚህ፣ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር አዲስ ግላዊ ግንኙነት እንዲመሠርቱ፣ አሊያም እርሱ እንዲገናኛቸው ልባቸውን እንዲከፍቱለት በዚህ አጋጣሚ በሁሉም ስፍራ ለሚገኙ ክርስቲያኖች በሙሉ ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡ ይህንንም በየቀኑ ያለማቋረጥ እንድታደርጉ ሁላችሁንም እጠይቃለሁ፡፡ ‹‹ጌታ ካመጣው ደስታ የተገለለ ማንም የለምና››፡፡ አንድም ሰው ይህ ጥሪ እኔን አይመለከተኝም ብሎ ማሰብ አይኖርበትም፡፡ ይህን ስጋት የሚቋቋሙትን ጌታ ከቶ አያሳፍራቸውም፡፡ ወደ ኢየሱስ አንድ እርምጃ በተራመድን ቁጥር እርሱ አስቀድሞ በዚያ ሆኖ ሊቀበለን እጁን ዘርግቶ ይጠብቀናል፡፡ ስለዚህ፣ ለኢየሱስ ‹‹ጌታ ሆይ፣ ለራሴ ተሞኝቼአለሁ፤ በሺህ መንገድ ከፍቅርህ ብርቅም እነሆ አሁን ደግሞ ካንተ ጋር ቃል ኪዳኔን ላድስ መጥቻለሁ፡፡ ጌታ ሆይ፣ አሁንም አድነኝ፣ አሁንም በአዳኝ ክንዶችህ እቀፈኝ›› የምንልበት ጊዜ አሁን ነው፡፡ በጠፋን ቁጥር ወደ እርሱ መመለስ ምንኛ ያስደስታል! ይህንን ደግሜ ልበለው፤ እግዚአብሔር እኛን ለመማር አይታክትም፤ የእርሱን ምሕረት ከመሻት የምንታክት እኛ ነን፡፡ ‹‹ሰባ ጊዜ ሰባት›› ይቅር እንድንባባል የነገረን ክርስቶስ (ማቴ.18፡22) የራሱን ምሳሌ ሰጥቶናል፤ ሰባ ጊዜ ሰባት ይቅር ብሎናል፡፡ መላልሶ በትከሻው ላይ ይሸከመናል፡፡ ከዚህ ወሰን የለሽ ከማያልቅ ፍቅሩና ክብር ሊለየን የሚችል ማንም የለም፡፡ ከቶውንም በማያሳፍር ይልቁንም ሁልጊዜ ደስታችንን የማደስ ኃይል ባለው ፍቅሩ አማካይነት ራሳችንን ቀና አድርገን እንደ አዲስ ጉዞአችንን እንድንጀምር ያደርገናል፡፡ ስለዚህ፣ ከኢየሱስ ትንሣኤ አንሸሽም፤ ምንም ነገር ቢሆን ከቶ ተስፋ አንቆርጥም፡፡ ወደፊት እንድንጓዝ ከሚያደፋፍረን ከእርሱ ሕይወት በቀር ሊያነቃቃን የሚችል አይኖርም፡፡

 

 

 

27 July 2020, 10:46