ፈልግ

ለተራቡት የዕለት ምግብን መስጠት፤ ለተራቡት የዕለት ምግብን መስጠት፤ 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ለዓለም የምግብ እና እርሻ ድርጅት ዕርዳታ ማድረጋቸው ተገለጸ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በችግር ውስጥ የወደቁትን ለመርዳት በጀመሩት የዕርዳታ መስጠት ተግባር፣ በተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና እርሻ ድርጅት “FAO” በኩል ለተቸገሩ ማኅበረሰቦች የገንዘብ መርዳታ ማድረጋቸው ታውቋል።

የቫቲካን ዜና፤

ቅዱስነታቸው ከዚህ በፊትም በተለያዩ ችግሮች ውስጥ ለሚገኙ የዓለማችን ሕዝቦች ሰብዓዊ ዕርዳታን ሲያቀርቡ መቆየታቸው ሲታወስ በተለይም ከቅርብ ወራት ወዲህ ዓለማችንን በማስጨነቅ ላይ በሚገኝ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በከፍተኛ የጤና እና የኤኮኖሚያዊ ቀውስ ወስጥ ለሚገኙት ቤተሰቦች ሰብዓዊ ዕርዳታ ሲያደርጉ መቆየታቸው ይታወሳል። ከዚህም በተጨማሪ በተለያዩ ማኅበራዊ ችግሮች ውስጥ ወድቀው በመከራ ውስጥ የሚገኙትን በዘወትር ጸሎታቸውም ጭምር የሚያስታውሷቸው መሆኑ ይታወቃል።

ቅዱስነታቸው ዓርብ ሰኔ 26/2012 ዓ. ም. በተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና እርሻ ድርጅት  የ25,000 ዩሮ ዕርዳታ ማድረጋቸው ታውቋል። በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት እንዳስታወቀው፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በተባበሩት መንግሥታት ለምግብ እና እርሻ ድርጅት የሰጡት የ25,000 ዩሮ እርዳታ፣ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ከፍተኛ ጉዳት ለደረሰባቸው ድሃ ለሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች፣ መሠረታዊ የሆኑ አስቸኳይ የዕርዳታ አገልግሎቶችን ለማዳረስ መሆኑን አስታውቋል።

ቅዱስነታቸው የገንዘብ ዕርዳታቸውን በተባበሩት መንግሥታት ለምግብ እና እርሻ ድርጅት (FAO)፣ ዓለም አቀፍ የእርሻ ልማት ፈንድ (IFAD) እና የዓለም የምግብ ፕሮግራም (WFP) እንዲደርስ ያደረጉት፣ በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት አማካይነት ፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቅድስት መንበር ቋሚ ተወካይ በኩል መሆኑ ታውቋል።

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ ለዓለም የምግብ ፕሮግራም እና ለአንዳንድ በማደግ ላይ ላሉት አገሮች ያደረጉት የገንዘብ እና የሕክምና አገልግሎት መስጫ መሣሪያዎች ዕርዳታ፣ በጦርነት እና በአመጽ ምክንያት የሚነሱ አለመረጋጋቶችን ለማርገብ፣ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ እያደገ የመጣውን የሥራ አጥ ቁጥር ለመቀነስ እና በማደግ ላይ ባሉት አገሮች የሚታየውን የኤኮኖሚ ሥርዓት መዳከም ለማስተካከል የተደረገ አባታዊ ዕርዳታ መሆኑ ታውቋል።  

04 July 2020, 11:11